2010–2019 (እ.አ.አ)
የግል ጥንካሬ በክርስቶስ ኢየሱስ ቤዛነት አማካኝነት
ኦክተውበር 2013


የግል ጥንካሬ በክርስቶስ ኢየሱስ ቤዛነት አማካኝነት

በኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛነት አማካኝነት እያንዳንዳችን ንፁህ መሆን እንችላለን እናም የአመፃችን ሸክም ይወገድልናል።

በቅርቡ በጣም አስገራሚ ከሆኑ የአይደሆ ወጣቶች ጋር በመገናኘቴ ተባርኬ ነበር። አንድ መልካም ወጣት ሴት አሁን በህይወታቸው ከምንም በላይ ምን ቢያደርጉ የተሻለ እንደሆነ ጠየቀችኝ። የክርስቶስን የቤዛነት ሃይል በህይወታቸው ማስተዋልን እንዲማሩ ምክሬን ለገስኩ። ዛሬ ታዲያ የዚያን ሀይል፥ በክርስቶስ ቤዛነት አማካኝነት ስለምንቀበለው የግል ጥንካሬ አንዱን ጎን እገልፃለሁ።

ከመፀሃፈ ሞርሞን ስለ አሞንና ስለ ወንድሞቹ ስለ ክርስቶስ ወንጌል “አረመኔ ፥ ልበ ጠጣሮች እና አስፈሪ“ ለሆኑ ህዝቦች ሲያስተምሩ እናነባለን። አብዛኛዎቹ ተለወጡ እና የሀጢያተኝነት ባህሪያቸውን ለመተው መረጡ።”1 ስለዚህ መለወጣቸው ሙሉ ከመሆኑ የተነሳ የጦር መሳሪያዎቻቸውን ቀብረው ዳግም ላለመጠቀም ከጌታ ጋር ቃል ገቡ።2

በሗላ ላይ ያልተለወጡት ብዙ ወገኖቻቸው መተው እነሱን መግደል ጀመሩ። በዚህን ጊዜ ታማኝ የነበሩት ህዝብ የጦር መሳሪያቸውን ዳግም አንስተው መንፈሳዊ ህይወታቸውን አደጋ ላይ ከመጣል ይልቅ ለጎራዴ እራሳቸውን አሳልፈው ለመስጠት ወሰኑ። ፃድቅ የሆነ ምሳሌያቸው ብዙ ሰዎች እንዲለወጡ እና የፀብ መሳሪያቸውን እንዲጥሉ አደረገ።3

በአሞን ምክንያት ጥገኝነት እንዲያገኙ ጌታ ወደ ኔፋውያን መራቸው፥ እናም የአመን ህዝብ ተብለው ተጠሩ።4 ኔፋውያን ለብዙ አመታት ጠበቁአቸው ነገር ግን መጨረሻ ላይ የኔፋውያን ወታደሮች ተሸንፈው ማለቅ ሲጀምሩ ተጨማሪ ጦር በጣም አስፈለጋቸው።5

የአመን ህዝብ መንፈሳዊ ህይወታቸው አስጊ ሁኔታ ላይ ሆነ። የጦር መሳሪያን ዳግም ላለማንሳት ለገቡት ቃል ታማኝ ነበሩ።6 ነገር ግን አባቶች ለልጆች ጥበቃን የመስጠት ሃላፊነት እንዳለባቸው ተረዱ። ይህም ሃላፊነት የገቡትን ቃል ለመስበር ምክንያተኛ መሰለ።7

ጠቢቡ የክህነት መሪያቸው ሄለማን የገቡትን ቃል መስበር በጌታ ዘንድ ተቀባይ እንዳልሆነ ያውቃል። ከመንፈስ የተቀበለውን አማራጭ አቀረበ። ልጆቻቸው ተመሳሳይ ሃጢያት ስለሌለባቸው ቃል ኪዳን መግባት አላስፈለጋቸውም።8 ልጆቹም ትንንሽ ቢሆኑም እንኳ አካላዊ ጥንካሬ ነበራቸው፥ እናም ከሁሉም በላይ መልካም እና ንፁህ ነበሩ። በናቶቻቸው እምነት ተበረታቱ።9 ነብይ በነበረው መሪያቸው፥ ምሪት እነዚህ ወጣቶች አባቶቻቸውን ተክተው ቤተሰባቸውንና እቤታቸውን ለመከላከል ወጡ።10

በዚህ አስቸጋሪ ውሳኔ ዙሪያ ያሉት ክስተቶች፥ በእግዚያብሄር ልጆች ላይ የኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛነት እንዴት የግል ጥንካሬን እንደሚያመጣ ያሳያል። የነዚያን አባቶች ለስላሳ ስሜትን ገምቱ። በዚያ አስፈላጊ ጊዜ ያለፈ የአመፅ ተግባራቸው እንዴት ሚስቶቻቸውንና ልጆቻቸውን ከአደጋ መከላከል ባለመቻላቸው ምን ያህል ይሰማቸዋል። ልጆቻቸው የሚጋፈጡትን ግፍ በማወቃቸው ራሱ ተደብቀው ሳያለቅሱ አይቀሩም።11 ልጆች ሳይሆኑ አባቶች ናቸው የቤተሰብ መከታ መሆን ያለባቸው።

ለምንድነው በመንፈስ የተመሩ የክህነት መሪዎቻቸው የመዋጊያ ጦሮቻቸውን ከንደገና የማውጣት ሃሳባቸውን የፈሩት። “ነፍሳቸውን እንዳያጡ ነው።“12 ጌታ እንዳወጀው “ለሃጢያቱ ንስሃ ለገባው ይቅር ይባላል። እናም እኔ ጌታ ሁጢያቱን ደግሜ አላስታውሰውም።”13 እነዚህ ታማኝ አባቶች ንስሃ ከገቡ እና በኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛነት ከነፁ ቆይቷል፥ ስለዚህ ለቤተሰቦቻቸው ከለላ እንዳይሆኑ ለምንድነው የተመከሩት?

በኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛነት አማካኝነት መንፃት እንደምንችል መሰረታዊ ሀቅ ነው። መንፃትና መቀደስ እንችላለን። ሆኖም ግን ደካማ ምርጫዎቻችን ዘላቂ መዘዝ ይተዉልናል። ንስሃን ለሟሟላት ከሚያስፈልገው ደረጃ መካከል ዋናው ያጭር ጊዜ እና የረጅም ጊዜ መዘዞችን መሸከም ነው። ያለፈው ምርጫዎቻቸው እነዚህን የአሞናውያን አባቶች ለምድራዊ ፍላጎት እንዲጋለጡና እንዲሁም ደግሞ ሴጣን በደካማ ጎን ለመበዝበዝ እንዲሞክር አደረገ።

ሰይጣን ያለፈውን የጥፋተኝነት ትውስታ ተጠቅሞ፥ ወደሱ ተፅእኖ አባብሎ ሊወስደን ይሞክራል። የሱን ማባበያ ለማራቅ ሁልጊዜ ንቁ መሆን አለብን። የታማኞቹ የአሞናውያን አባቶችም ሁኔታ ይሄው ነው። ከብዙ የታማኝነት ህይወት በሗላ እንኳ እራሳቸውን ካለፈ የሃጥያት ትውስታ መጠበቅ አስፈላጊ ነበር።

በብዙ ጦርነቶች መካከል የጦር አለቃ ሞሮኒ የደከሙ ከተማዎችን ስለማጠናከር ተናገረ። “ ለከተማዋ ቅርብ በሆነው ወንዝ ዳርቻ በጉድጓዱ በኩል ከእንጨት አጥር እንዲሰሩ አደረገ። እናም ከእንጨት በተሰራው አጥር ላይም ከጉድጓዱ አፈር በማውጣትም አስቀመጡ። ዙሪያውንም በጠንካራ እንጨት ትልቅ ከፍታም እንዲኖረው እስከሚያደርጉ ድረስ እንዲሰሩ አደረገ።”14 ጥንካሬን ለመገንባት የጦር አለቃ ሞሮኒ ደካማ የሆኑትን ከተማዎቸ መገንባት አስፈላጊ እንደሆነ ገብቶታል።15

እነዚህ የአሞናውያን አባቶችም ተመሰሰይ ነበሩ። በታማኝ ህይወታቸውና ባለፈው ፃድቅ ያልሆነ ባህሪያቸው መካከል ረጅምና ሰፊ ማጠናከሪያ አስፈልጓቸው ነበር። በፅድቅ ባህል የተባረኩት ልጆቻቸው ግን ለተመሳሳይ ፈተና ተጋላጭ አልነበሩም። መንፈሳዊ ህይወታቸውንም ሳይጎዱ ቤተሰቦቻቸውን በታማኝነት ሊከላከሉ ቻሉ።

ለማንም ሰው ባለፈ ደካማ ምርጫ ምክንያት የሚመጡ መዘዞችን ለማስወገድ መሻት ካለው አስደሳቹ ዜና ታዲያ፥ ጌታ ድክመትን እና አመፀኝነትን በተለየ መልኩ ነው የሚመለከተው። ጌታም ንስሃ ያለመግባት አመፀኝነት ቅጣትን እንደሚያስከትል አስጠንቅቋል።16 ጌታ ስለ ድክመቶች ሲናገር ከምህረት ጋር አዛምዶ ነው።17

ያለ ጥርጥር፥ እነዚህ የአሞናውያን አባቶች፥ ካባቶቻቸው የስህተት ባህል የተማሩበት ሁኔታ አለ። ነገር ግን ሁሉም የሰማይ አባታችን ልጆች ወደ ሟች ህይወት ሲመጡ የክርስቶስ ብርሃንን ይዘው ነው፥ ከሃጢያታዊ ተግባራቸው መንስኤ ባሻገር ጉዳቱ ሰይጣን ለመበዝበዝ የሚሞክረውን መንፈሳዊ ደካማ ጎንን ማሳደግ ነው።

ደግነቱ ወንጌልን ተምረዋል፥ ንስሃም ገብተዋል እናም በክርስቶስ ቤዛነት ምክንያት ከሴጣን ፈተና ይልቅ የተሻለ ጠንካራዎች ሆነዋል። ወደ ከባዱ ላለፈው ህይወታቸው ለመዞር ምንም አልተፈተኑም፥ ይልቁኑ ወደመሪያቸው በመዞር “ነፍሳቸውን ሴጣን እንዳያጭበረብረው እና በጥንቃቄ ወደ ሲኦል እንዳይመራቸው እድሉን አልሰጡትም።” 18የአዳኛችን ቤዛነት ከሃጢያት ብቻ ሳይሆን ያነፃቸው፥ ለክህነት መሪያቸው ምክር ታዛዥ በመሆናቸው አዳኛችን ከድክመታቸው ጠብቆ አጠነከራቸው። ሃፅያታቸውን ለመተው ባሳዩት ትህትናና ዘላቂ ቁርጠኝነት በጦር ሜዳ ላይ ሊያደርጉት ከሚችሉት በላይ ቤተሰቦቻቸውን ጠብቆላቸዋል። እጅ መስጠታቸው ከበረከታቸው አላገዳቸውም። እነሱን አጠንክሮአል እናም ብዙ መጪ ትውልዶችንም ባርኮአል።

የታሪኩ መዝጊያ የጌታ ምህረት እንዴት “ደካማ ነገሮችን ጥንካሬ እንዳደረጋቸው“ ያሳያል።19 እነዚያ አባቶች ልጆቻቸውን በሄለማን ጥበቃ ስር አድርገው ላኳቸው። ልጆቹ ባደገኛ ውጊያ ውስጥ ተዋግተው እንኳ የተወሰነ ጉዳት ቢደርስባቸውም አንዲት ህይወት እንኳ አልጠፋም።20 ለተመናመነው የኔፋውያን ጦር፥ ወጣት ወንዶቹ አስፈላጊ ድጋፍ መሆናቸውን አሳዩ። ወደቤት ሲመለሱ ታማኝና የመንፈስ ጥንካሬን ተቀበሉ። ቤተሰቦቻቸው ተባርከዋል፥ ተጠብቀዋል እናም ተጠናክረዋል።21 በጊዜያችን ከቁጥር በላይ የሆኑ የመፅሃፈ ሞርሞን ተማሪዎች በነዚህ ንፁህ እና ፃድቅ በሆኑ ወጣት ወንድ ልጆች ምሳሌነት ተባርከዋል።

እያንዳንዳችን በህይወታችን ደካማ ምርጫዎችን ያደረግንበት ወቅት ሊኖር ይችላል። ሁላችንም ታዲያ የማዳን ሃይል ያለውን የኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛነት በደንብ ያስፈልገናል። ሁላችንም ስለማንኛውም አመፃችን ንስሃ መግባት አለብን። “እኔ ጌታ ማንኛውንም ሃጢያት ቢሆን በትንሹ መዝኜ አላይም።“22 ይህንን ማድረግ አይችልም ምክንያቱም እንደሱ ለመሆን ምን እንደሚያስፈልግ ያውቃልና።

አብዛኛዎቻችን ድክመት በባህሪያችን እንዲያድግ ፈቅደናል። በኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛነት አማካኝነት እኛም ልክ እንደ አሞናውያን መንፈሳዊ ምሽግ በኛና ሴጣን ሊበዘብዝ በሚሞክረው ባለፉት ሃጢያቶቻችን መካከል መገንባት እንችላለን። በአሞናውያን አባቶች ዙሪያ የተገነባው መንፈሳዊ ከለላ እራሳቸውን፥ ቤተሰባቸውን፥ አገራቸውን፥ ቀጣይ ዘሮቻቸውን ሁሉ ባርኳል እንዲሁም አጠናክሯል። ለኛም ይህ እውን መሆን ይችላል።

ስለዚህ እነዚህን የዘላለም ምሽጎች እንዴት አድርገን ነው የምንገነባው? የመጀመሪያ ደረጃ መሆን ያለበት፥ ከልብ የሆነ፥ ሙሉ ንስሃ ነው። በኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛነት አማካኝነት እያንዳንዳችን ንፁህ መሆን እንችላለን እናም የአመፃችን ሸክም ይወገድልናል። አስታውሱ ንስሃ ቅጣት አይደለም። ክብር ላለው ወደፊት በተስፋ የተሞላ መንገድ እንጂ።

የሰማይ አባት በደካማ ጎናችንና በታማኝነታችን መካከል ምሽግ የምንገነባበትን መሳሪያዎች አዘጋጅቶልናል። የሚቀጥሉትን ሃሳቦች ተመልከቱ።

  • ቃል ኪዳን በመግባት የራሳችሁን የቤተከርስቲያን ስርቶችን ተቀበሉ። ከዚያም ያለማቋረጥ በፅናት ላለፉት ዘመዶቻችሁ የቤተ መቅደስን ስርአቶችን ፈፅሙላቸው።

  • ወንጌልን ከቤተክርስቲያን ለቀሩ ወይም አባል ላልሆኑ የቤተሰብ አባላት ወይም ጓደኟዎች አካፍሉ። ይህንን እውነት ማካፈል በህይወታችሁ የታደሰ ጉጉትን ያመጣል።

  • በሁሉም የቤተክርስቲያን ያገልግሎት ጥሪ በታማኝነት ተወጡ። በተለይ ደግሞ የቤት ለቤት ትምህርት እና የጉብኝት ትምህርት። በወር የ15 ደቂቃ ብቻ የቤት ወይም የጉብኝት አስተማሪዎች አንሁን። ይልቁንም፥ ለያንዳንዱ የቤተሰብ አባላት ድረሱ። በግል እወቁዋቸው። እውነተኛ ጓደኞች ሁኑ። ለእያንዳንዱ ምን ያህል እንደምትቆረቆሩ በደግነት ተግባር አሳዩ።

  • ከሁሉም በላይ የቤተሰብ አባሎቻችሁን አገልግሉ። የባለቤታችሁንና የልጆቻችሁን መንፈሳዊ እድገት ከፍተኛ ቅድሚያ ስጡ። እርስ በርስ ለመረዳዳት ምን ማድረግ እንደምትችሉ ትኩረትን ስጡ። ጊዜያችሁንና ትኩረታችሁን በነፃ አበርክቱ።

በእያንዳንዱ በነዚህ ሃሳቦች አንድ የጋራ መልእክት አለ። ህይወታችሁን በሌሎች አገልግሎት ሙሉ። ህይወታችሁን የሰማይ አባት ልጆችን23 በማገልገል ስታጡ የሴጣን ፈተና ከህይወታችሁ ሃይልን ያጣል።

የሰማይ አባታችሁ አጥብቆ ከማፍቀሩ የተነሳ የኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛነት ያንን ጥንካሬ ያመቻቻል። ይህ ድንቅ አይደለምን? አብዛኛዎቻችሁ የደካማ ምርጫዎቻችሁን ሸክም ተሰምቶቻችሁ ይሆናል፥ እናም እያንዳንዳችሁ ከፍ የሚያድርገውን የጌታን የይቅርታን፥ የምህረትን እና የጥንካሬን ሀይል ሊሰማችሁ ይችላል። እኔ ተሰምቶኛል። ለእያንዳንዳችሁም ይህ እንደሚገኝ በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እመሰክርላችሗለሁ አሜን።