2010–2019 (እ.አ.አ)
ሀብታችሁ ባለበት ቦታ
ሚያዝያ 2014


ሀብታችሁ ባለበት ቦታ

ካልተጠነቀቅን፣ አለማዊውን ከመንፈሳዊ ይልቅ ለማግኘት መጣር እንጀምራለን።

ከጥቅምት 2007 (እ.አ.አ) አጠቃላይ ጉባኤ ከትንሽ ጌዜ በኋላ፣ ይህን አስቸጋሪ አጋጣሚ እንደገና እስከማገኘው ድረስ ሰባት አመታት እንደሚያልፉ ከወንድሞቼ አንዱ ነግሮኝ ነበር። ደስ ብሎኝ ነበር እናም እንደ “እጅግ ጥጋብ የሚሆንባቸው ሰባት ዓመታት” እንዲሆንልኝ እቆጥረዋለው አልኩት። አሁን በዚህ እገኛለሁ፤ እጅግ ጥጋብ የሆኑት የእኔ ሰባት ዓመታ ተፈጽመዋል።

ባለፈው ጥር ውዷ ባለቤቴ ግሬስ እና እኔ በምድር መንቀጥቀጥ እና በአውሎ ንፋስ መአት የነበረባቸውን የፍሊፒንስ ህዝቦችን እንድንጎበኝ ተመደብን። ይህ የስራ ምድብ የጸሎታችን መልስ እና የአፍቃሪ ሰማይ አባት ምህረት እና መልካምነት ምስክር ስለነበረ ተደሰትን። ለእነርሱ ያለንን የግል ፍቅር እና ሀሳብ የምናሳይበት ያለን ጉጉት የሚሟላበት ነበር።

አብዛኛዎቹ ያገኘናቸው አባላት በድንኳን፣ በህብረተሰብ መሰብሰቢያ፣ እና በቤተክርስቲያን ስብሰባ ቤቶች ውስጥ እየኖሩ ነበር። የጎበኘናቸው ቤቶች ጣራዎቻቸው በግማሽ የተሸፈኑ ወይም ጣሪያ የሌላቸው ነበሩ። ህብዙ ብዙም አልነበራቸውም ነበር እናም የነበራቸውም ተጠርጎ ጠፍቶ ነበር። በሁሉም ቦታ ጭቃ እና ቆሻሻ ነበር። ነገር ግን፣ ለተቀበሉት ትንሽም እርዳታ ምስጋና ነበራቸው እናም በአስቸጋሪ ሁኔታ ላይ መሆን ቢቀጥሉም ደስተኛና መልካም መንፈስ ያላቸው ነበሩ። እንዴት እየቻሉት እንደሆነ ስንጠይቃቸው፣ እያንዳንዱም በግልጽ መልስ፣ “ደህና ነን።” ብለው መለሱ። በግልጽም፣ በኢየሱስ ክርስቶስ ያላቸው እምነት ሁሉም ነገሮች በመጨረሻ ደህና እንደሚሆኑ ተስፋ ሰጥቷቸዋል። ከቤት ቤት፣ ከድንኳን ድንኳን፣ እኔ እና እህት ቴ በእነዚህ አማኝ ቅዱሳን ተምረን ነበር።

በመዓት ወይም አደጋ ጊዜ፣ ጌታ እኛን እና ቀዳሚ ማድረግ የሚያስፈልገው ላይ ትኩረት እንድናደርግ ያደርገናል። በድንገትም፣ ለማጠራቀም በሀይል እንሰራበት የነበሩ አለማዊ ነገሮችም ትርጉም አይኖራቸውም። ትርጉም ያለቸው ቤተሰባችን እና ከሌሎች ጋር ያሉን ግንኙነቶች ናቸው። መልካም እህት እንዲህ አስቀመጠችው “ጎርፉ ከቀነሰ በኋላ እና መጽዳት ሲጀምር፣ በቤቴ ዙሪያ ተመለከትኩኝና ‘አስደናቂ ነው፣ ይህንን ሁሉ አመታት ብዙ ቆሻሻዎችን አጠራቅሜአለሁ’ አልኩኝ።”

ይህች እህት የተሻለ አስተያየት እንዳገኘች እናም ከዚህም በኋላ የትኞቹ አስፈላጊ እንደሆኑ እና የትኞቹንበእርግጥ ካለነሱ መኖር እንደምትችል ጥሩ አመለካከት እንዳገኘች እገምታለው።

ከብዙ አባላት ጋር አብረን ለአመታት በመስራት፣ የበዙ መንፈሳዊ ጥንካሬዎችን መመልከት በመቻላችን ተደስተናል። በእነዚህ ታማኝ አባላት መካከል የሀብት ብዛትን እና ማጣትን ተመልክተናል።

በግዴታ፣ አብዛኛዎቻችን ቤተሰባችንን ለመደገፍ ገንዘብ በማግኘት እና አንዳንድ አለማዊ ነገሮችን በማከማቸት ላይ ነን። አብዛኛውን ጊዜአችንን እና ትኩረታችንን እንድንሰጥ ይጠይቃል። አለም ለምታቀርባት ምንም መጨረሻ የለም፣ ስለዚህ “የሚበቃ” ሲኖረን ማወቃችን በጣም አስፈላጊ ነው። ካልተጠነቀቅን፣ አለማዊውን ከመንፈሳዊ ይልቅ ለማግኘት መጣር እንጀምራለን።የተገላቢጦሹ መሆን ሲገባው፣ ለመንፈሳዊ እና ለዘለአለማዊ ነገሮች ያለን ፍላጎትም የቀነሰ ትኩረት ይኖረዋል። በሚያሳዝን ሁኔታም፣ብዙና ብዙ ለማግኘት እና አዲሱን እና በቴክኖሎጂ ታላቅ የሆነውን ለማግኘት ጠንካራ ፍላጎት ያለ ይመስላል።

ወደዚህ መንገድ እንዳልተጎተትን እንዴት ማረጋገጥ እንችላለን? ያዕቆብ ይህን ምክር ይሰጣል፥ “ስለዚህ፣ ዋጋ በሌለው ነገር ገንዘብ አታባክኑ፣ ወይንም አጥጋቢ ለማይሆን ጉልበታችሁን አታባክኑ፣ እናም አድምጡኝ፣ የተናገርኳቸውንም ቃል አስታውሱ፤ ወደ እስራኤሉ ቅዱስ ኑ፣ እናም የማይጠፋውን ሊበላሽ የማይቻለውን ተመገቡና፣ ነፍሳችሁ በመፋፋት ትደሰት።”1

ማንኛችንም ዋጋ ለሌለው ገንዘባችንን እና ጉልበታችንንም ለማያጠግብ ነገር እንደማናጠፋ ተስፋ አድርጋለው።

አዳኝ ለአይሁዶች እና ለኔፊያውያን የሚቀጥለውን አስተማረ፥

“ብልና ዝገት በሚያጠፉት፣ ሌቦችም ቆፍረው በሚሰርቁት፣ ለራሳችሁ በምድር ላይ ሀብትን አታከማቹ፤

“ነገር ግን ብልና ዝገት የማያጠፋውን፣ እናም ሌቦች ቆፍረው የማይሰርቁትን፣ ለራሳችሁ የሚሆን ሀብትን በሰማይ አከማቹ።

“ሀብታችሁ ባለበት ልባችሁ ደግሞ በዚያ ይሆናልና።”2

በሌላም አጋጣሚ፣ አዳኝ ይህን ምሳሌ ሰጠ፥

“አንድ ባለ ጠጋ ሰው እርሻ እጅግ ፍሬያም ሆነችለት።

“እርሱም። ፍሬዬን የማከማችበት ስፍራ አጥቻለሁና ምን ላድርግ? ብሎ በልቡ አሰበ።

“እንዲህ አደርጋለሁ፤ ጐተራዬን አፍርሼ ሌላ የሚበልጥ እሠራለሁ፥ በዚያም ፍሬዬንና በረከቴን ሁሉ አከማቻለሁ፤

“ነፍሴንም። አንቺ ነፍሴ፥ ለብዙ ዘመን የሚቀር ብዙ በረከት አለሽ፤ ዕረፊ፥ ብዪ፥ ጠጪ፥ ደስ ይበልሽ እላታለሁ አለ።

“እግዚአብሔር ግን። አንተ ሰነፍ፥ በዚች ሌሊት ነፍስህን ከአንተ ሊወስዱአት ይፈልጓታል፤ ይህስ የሰበሰብኸው ለማን ይሆናል? አለው።

“ለራሱ ገንዘብ የሚያከማች፥ በእግዚአብሔር ዘንድም ባለ ጠጋ ያልሆነ እንዲህ ነው።”3

ፕሬዘደንት ዲየትር ኤፍ. ኡክዶርፍ ብዙ ጊዜ ሳያልፍ ይህን ምክር ሰጥተው ነበር፥

“የሰማይ አባታችንትክክለኛ ችሎታችንን ያያል። ስለእኛ ራሳችን የማናውቃቸውን ነገሮች ያውቃል። በህይወታችን የተፈጠርንበትን አላማ እንድናሟላ፣ መልካም ህይወት እንዲኖረን፣ እና ወደ እርሱ ፊት እንድንመለስ ያነሳሳናል።

“ብዙውን ጊዜአችንን እና ሀይላችንን ለጊዜአዊ፣ ምንም ዋጋ ለሌላቸው፣ እና በውጪ መታየት ብቻ ለሚቻሉ ነገሮች እናጠፋለን? ዋጋ የሌለውን እና ጊዜአዊ ነገሮችን ማከናወን ሞኝነት እንደሆነ ለማየት እንቃወማለን?”4

የምድር ሀብቶቻችን ዝርዝር በተጨማሪ ኩራት፣ ሀብት፣ ምድራዊ ነገሮች፣ ሀይል፣ እና የሰዎች ክብር እንደሆኑ ሁላችንም እናውቃለን። ምንም ያህል ጊዜና ትኩረት አያስፈልጋቸውም፣ ስለዚህ የሰማይ ሀብታችንን በሚያካትቱት ላይ አተኩራለሁ።

ለራሳችን ማከማቸት የምንችላቸው አንዳንድ የሰማይ ሀብቶች ምን ናቸው? ለመጀመሪያ፣ክርስቶሳዊ እምነት፣ ተስፋ፣ ትህትና፣ እና ልግስና ጸባዮችን ማግኘት ለእኛ ጠቃሚ ነው። በተደጋጋሚ ሁኔታ የተፈጥሮ ሰው ፍላጎታችንን እንድናስወግድ፣ እና እንደ ትትንሽ ልጆች እንድንሆን ተመክረናል።5 የአዳኝ ግሰጻም እኛ እንደ እርሱ እና እንደ ሰማይ አባታችን ፍጹም እንድንሆን ነው።6

ሁለተኛ፣ የቤተሰብ ግንኙነቶችን ለማጠናከር ተጨማሪ ጥሩ ጊዜዎችን እና ጥረቶችን ማድረግ ያስፈልገናል። “ቤተሰብ በእግዚአብሔር የተሾመ ነው። ለጊዜ እና ለዘለአለም ከሁሉም በላይ አስፈላጊ የሆነ ነው።”7

ሶስተኛ፣ ሌሎችን ማገልገል የክርስቶስ ተከታዮች ዋና ጸባይ ነው። እንዲህም አለ፣ “ከሁሉ ከሚያንሱ ከእነዚህ ወንድሞቼ ለአንዱ እንኳን ብታደርጉ ለኔ ነው ያደረጋችሁት” ይላቸዋል።8

አራተኛ፣ የክርስቶስ ትምህርትን መረዳት እና ምስክራችንን ማጠናከር እውነተኛ ደስታ እና እርካታ የሚያመጣ ስራ ነው። በየጊዜው በቅዱሳት መጽሐፍት እና በህያው ነቢያት ቃላት ውስጥ የሚገኙትን የክርስቶስን ቃላት ማጥናት ያስፈልገናል። “እነሆ የክርስቶስ ቃል ማድረግ ያለባችሁን ነገሮች በሙሉ ይነግራችኋልና።”9

ወደ ፊሊፒንስ በተጓዝንበት ጊዜ በተገናኘናቸው የ73 አመት እድሜ አሮጊት ታሪክ ልጨርስ፥

የምድር መንቀጥቀጥ የቦሆል ደሴትን ሲመታ፣ እርሳቸው እና የሞቱት ባላቸው በታላቅ ጥረት የሰሩበት ቤት፣ ልጃቸውን እና የልጅ ልጃቸውን በመግደል ወደቀ። እርሳቸው ከትንሽ ቁስሎች በስተቀር አልተጎዱም ነበር። አሁን ብቻቸውን ሆነው እራሳቸውን ለመርዳት መስራት ነበረባቸው፣ እራሳቸውን ለመደገፍ መስራት ነበረባቸው። (በእጅ የሚያጥቡትን) ልብሶች ይቀበላሉ እናም ትልቅ ኮረብታንም ውሀ ለማምጣት በየቀኑ በተደጋጋሚ ይጓዛሉ። እርሳቸውን ስንጎበኝ፣ በድንኳን ውስጥ እየኖሩ ነበር።

እነዚህ የእርሳሸው ቃል ነበሩ፥ “ሽማግሌ፣ ጌታ እንዳልፍባቸው የሚጠይቀኝን ነገሮች በሙሉ እቀበላለሁ። የቤተመቅደስ መግቢያ ፈቃዴ ሀብቴ ነው እናም ይህን ከትራሴ ስር አስቀምጠዋለው። ልብስ ከማጥብበት ከማገኘው ትንሽ ገንዘብ አስራትን እንደምከፍል እባክዎ ይወቁ። ምንም ቢደርስ፣ አስራቴን ሁልጊዜ እከፍላለሁ።”

ለእኛ ቀዳሚ ነገሮች፣ ዝንባሌዎች፣ ጸባዮች፣ ፍላጎቶች፣ እና ጥልቅ ስሜት በሚቀጥለው ህይወታችን ላይ ተፅዕኖ እንዳላቸው እመሰክራለሁ። የአዳኝን ቃላት ሁልጊዜ እናስታውስ፣ “ሀብታችሁ ባለበት ልባችሁ ደግሞ በዚያ ይሆናልና።” ልባችን በትክክለኛው ቦታ እንዲገኝ የምጸልየው፣ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ነው፣ አሜን።