2010–2019 (እ.አ.አ)
የምንታመንበትን ማስታወስ
ኦክተውበር 2015


የምንታመንበትን ማስታወስ

ከአብ ጋር እንደገና የመኖር ተስፋችን በኢየሱስ ክርስቶስ የሀጢአት ክፍያ ላይ የሚወሰን ነው።

በዘጠኝ አመት እድሜ እያለሁ፣ 150 ሴንቲሜትር የሆነችው በእናቴ በኩል ያለች ነጭ ፀጉራማዋ አያቴ ከእኛ ጋር ጥቂት ሳምንታትን ለማሳለፍ ወደቤታችን መጣች። እዚያው በነበረችበት አንድ ከሰአት በኋላ፣ ከቤታችን መንገዱን ተሻግሮ ባለው ቦታ ጉድጓድ ለመቆፈር ሁለቱ ታላቅ ወንድሞቼ እና እኔ ወሰንን። ለምን ይህን እንደወሰንን አላውቅም። ወጣት ወንዶች ጉድጓድ መቆፈር ይወዳሉ። ወደ ብዙ አደጋ ውስጥ የሚከተን ባይሆንም፣ ትንሽ ቆሽሸን ነበር። በጎረቤት ዙሪያ የነበሩ ሌላ ወጣት ወንዶች ጉድጓድ መቆፈር እንዴት እንደሚያስደስት አዩ እና ማገዝ ጀመሩ። ከዛ ሁላችንም የባሰ ቆሸሽን። መሬቱ ጠንካራ ነበር፣ ስለዚያም የአትክልት ማጠጫ ጎማ ወሰድን እና መሬቱን ለማለስለስ ትንሽ ውሃ በጉድጓዱ ስር አደረግን። ስንቆፍር ትንሽ ጨቀየን፣ ነገር ግን ጉድጓዱ የበለጠ ጥልቅ ሆነ።

ከቡድናችን ውስጥ አንዱ ጉድጓዱን መዋኛ ገንዳ እንድናደርገው ወሰነ፣ ስለዚህ በውሃ ሞላነው። ታናሽ በመሆኔ እና አብሮነቴ እንዲሰማቸው በመፈለጌ ፣ ዘሎ ለመግባት እና ለመሞከር ተነሳሳሁ። አሁን በጣም ቆሸሽኩ። በጭቃ ለመሸፈን አቅጄ አልነበረም የጀመርኩት፣ ነገር ግን የደረስኩበት መጨረሻ እንደዚያ ሆነ።

መብረድ ሲጀምር፣ ወደቤቴ ውስጥ ለመግባት በማሰብ፣ መንገዱን አኳረጥኩ። አያቴ በውጪው በር ላይ አገኘቺኝ እና እንዳልገባ ከለከለችኝ። እንድገባ ከፈቀደችልኝ፣ በቅርብ ባፀዳችው ቤት ውስጥ ጭቃ እንደምነዛ ነገረችኝ። ስለዚህ ማንኛውም የዘጠኝ አመት ልጅ የሚያደርገውን አደረኩኝ እና ወደ ጓሮ በር እሮጥኩኝ፣ ነገር ግን ካሰብኩት በላይ ፈጣን ነበረች። ተናደድኩ፣ በእግሬ ድም ድም አደረኩ፣ እና በግድ ወደ ቤት እንድገባ ጠየኩ፣ ነገር ግን በሩ አሁንም እንደተዘጋ ነው።

እርጥብ፣ ጭቃማ፣ የቀዘቀዝኩ ነበርኩ እና በልጅነት አመለካከቴ በእራሴ የጓሮ ግቢ ውስጥ እሞት ይሆናል ብዬ አሰብኩ። በመጨረሻም፣ ወደቤት ውስጥ ለመግባት ምን ማድረግ እንዳለብኝ ጠየኳት። ከማወቄ በፊት፣ አያቴ እኔ በቆምኩበት በጎማ ውሃ ትረጨኝ ጀመረች። የዘለአለም ቆይታ ከሚመስል ጊዜ በኋላ፣ ንፁህ መሆኔን አያቴ ገለፀች እና ወደቤት እንድገባ አደረገች። እቤት ውስጥ ይሞቅ ነበር፣ እናም ደረቅ እና ንፁህ ልብስ መልበስ ቻልኩኝ።

ይሄ እውነተኛ የህይወት ምሳሌ በአእምሮ ውስጥ እንዳለ፣ እባካችሁ ተከታዩን የኢየሱስ ክርስቶስ ቃላቶችን አስቡ፤ “እናም በመንግስተ ሰማይ የረከሰ ነገር ሊገባ አይቻለውም፤ ስለዚህ በእምነታቸው እናም ለኃጠአታቸው ሁሉ ንስሃ በመግባታቸው እናም እስከመጨረሻው ባላቸው ታማኝነት በደሜ ልብሳቸውን ካፀዱት በስተቀር በእረፍቱ የሚገባ ማንም የለም።”1

ከቤቴ ውጪ ቆሜ በአያቴ ውሃ መረጨት አስደሳች አና ምቹ አልነበረም። እዛው ለመቆየት በመወሰን ወይም በጉድጓድ ሙሉ ሀጢአት በመጨቅየት ምክንያት ለመመለስ እና ከአባታችን ጋር በሰማይ የመኖር እድልን መነፈግ ዘለአለማዊ ሀዘን ይሆናል። ለመመለስ እና በሰማይ ከአባታችን ጋር ለመኖር ስለሚያስፈልገው ነገር እራሳችንን ማታለል የለብንም። ንፁህ መሆን አለብን።

ወደዚህ ምድር ከመምጣታችን በፊት፣ በታላቁ ሸንጎ ውስጥ እንደ እግዚአብሔር የመንፈስ ወንድ እና ሴት ልጆቹ ተሳትፈን ነበር።2 ሁላችንም በትኩረት እንከታተል ነበር፣ እና ማናችንም በእንቅልፍ አልተያዝንም ነበር። በዚያ ምክክር፣ የሰማይ አባታችን እቅድን አቀረበ። እቅዱ ነፃ ምርጫችንን ስለሚያካትት እና ከእርሱ ብቻ ሳይሆን ከእራሳችንም ተሞክሮዎች መማርን ስለሚያስፈልግ፣ እኛ ሀጢአት እንደምንሰራ ያውቅ ነበር። እርሱ የሚኖርበት በአያት ከተፀዳ ቤት በላይ ንፁህ በመሆኑ ምክንያት፣ ሀጢአትም እንድንቆሽሽ እና ወደእርሱ እይታ መመለስ እንዳንችል እንደሚያደርገንም ያውቅ ነበር።

በሰማይ ያለው አባታችን ስለሚወደን እና የእኛን “ሟች አለመሆን እና ዘለአለማዊ ህይወት ለማምጣት”3 አላማው ስለሆነ፣ ምንም ያህል ብንቆሽሽ ንፁህ እንድንሆን ሊረዳን የሚችል፣ የአዳኝን ሚና እቅዱ ያካተተ ነበር። የሰማይ አባታችን የአዳኝን አስፈላጊነት ሲያሳውቅ፣ በመንፈስ የበኩር ልጅ የሆነውን፣ እንደ አባቱ እስከመሆን ድረስ ያደገው፣ ኢየሱስ ክርስቶስን ሁላችንም ዞር ብለን እንደተመለከትን አምናለሁ።4 እርሱ መሆን እንዳለበት፣ ከእኛ ውስጥ ማናችንም ልናደርገው እንደማንችል፣ ግን እርሱ እንደሚችል እና እንደሚያደርገው ሁላችንም አውቀን እንደነበር አምናለሁ።

በጌተሰማኒ አትክልት ቦታ እና በጎልጎታ መስቀል ላይ፣ በአካል እና በመንፈስም ተሰቃየ፣ በህመሙ ምክንያት ተንቀጠቀጠ፣ ከሁሉም የቆዳ ቀዳዳው ደማ፣ መራራውን ፅዋ ከእርሱ እንዲወስድ አባቱን ተማፀነ፣5 ሆኖም ግን ከፅዋው ተካፈለ።6 ለምንድን ነው ያንን ያደረገው? በእራሱ ቃላት፣ አባቱን ለማክበር ፈልጎ ስለነበር እና “ለሰው ልጆች ዝግጅቱን” ለመጨረስ ነበር።7 ቃልኪዳኑን ለመጠበቅ እና የእኛን ወደቤት መመለስ የሚቻል ለማድረግ ፈልጎ ነበር። በምላሹ እኛ እንድናደርግ የጠየቀን ምንድን ነው? እርሱ እንደሆነው እኛ እንዳንሰቃይ በቀላሉ ሀጢአታችንን እንድንናዘዝ እና ንስሀ እንድንገባ ይማፀነናል።8 በሰማይ ባለው አባታችን ቤት ሳንገባ በውጪ እንዳንቀር ለማድረግ ንፁህ እንድንሆን እርሱ ይጋብዘናል።

ሀጢአትን የማስወገድ የህይወት ሂደት ተመራጭ ቢሆንም፣ የኢየሱስ ክርስቶስ የሀጢአት ክፍያ ፍቱህነትን በተመለከተ፣ ምን ሀጢአቶችን እንደፈፀማችሁ ወይም ወደ ምሳሌአዊው ጉድጓድ ምን ያህል መጥለቃችሁ ልዩነት አይፈጥርም። ሀጢአታችሁ ኔፊ እንዳለው “በጣም በቀላሉ የሚያስቸግሩ”9 በመሆናቸው ምክንያት ቢያሳፍሯችሁም ልዩነት አይኖረውም። በአንድ ወቅት የልደት መብታችሁን በሙቅ ቀይራችሁ ቢሆን እንኳን ልዩነት አይፈጥርም።10

ልዩነትን የሚፈጥረው ኢየሱስ ክርስቶስ፣ የእግዚአብሔር ልጅ፣ “በስጋ ህዝቦቹን እንዴት ማዳን እንዳለበት ለማወቅ ሁሉንም አይነት ህመም እና ስቃይ እናም ፈተናዎችን” መሰቃየቱ ነው።11 ልዩነትን የሚፈጥረው እርሱ ወደዚህ ምድር ለመምጣት እና “ከሁሉም ነገሮች በታች”12 ለመውረድ እናም “ማንም ሰው ከሚችለው በላይ ይበልጥ ሀያል ተቃርኖዎችን””13 ለመሰቃየት እራሱን ዝቅ ለማድረግ ፍቃደኛ መሆኑ ነው።14 ልዩነትን የሚፈጥረው ለእኛ ጉዳይ ክርስቶስ በአብ ዘንድ በተማፅኖ እንዲህ ማለቱ ነው፤ “አባት ሆይ፣ ኃጢአት ያልነሰራውን በእርሱም የተደሰትከውን ስቃይና ሞት ተመልከት…። ስለዚህ፣ አባት ሆይ፣ በስሜ የሚያምኑትን ወደ እኔም መጥተው ዘለአለማዊ ህይወት ይኖራቸው ዘንድ እነዚህ ወንድሞቼን አድናቸው።”15 ልዩነት የሚፈጥረው እና ለእያንዳንዳችን የታደሰ ተስፋና ለተጨማሪ አንድ ጊዜ እንድንሞክር እንድንወስን የሚያስደርገው ያም ነው፣ ምክንያቱ እርሱ አልተረሳንምና።16

ንስሀ ለመግባት እና በትህትና እርሱን ካሻን፣ አዳኝ እራሱን ከእኛ በፍፁም እንደማያዞር፤የጠፋን አድርጎ በፍፁም እንደማያስበን፤ “ውይ፣ እንደገና መጣህ(ሽ)” በፍፁም እንደማይል፤ ሀጢአትን ማስወገድ እንዴት እንደሚከብድ ለመረዳት ባለመቻል ምክንያት እኛን በፍፁም እንደማይክደን እመሰክራለሁ። የማይቀር የሀጢአት ውጤት የሆነውን ሀዘንን፣ ሀፍረትን፣ እና የመሰላቸትን ስሜት ጨምሮ ሁሉንም ፍፁም በሆነ መልኩ ይረዳል።

ንሰሀ እውነት ነው እናም ይሰራል። የልበወለድ ተሞክሮ ወይም “የአእምሮ መሳት” ውጤት አይደለም።17 ሸክምን የማንሳት እና በተስፋ የመተካት ሀይል አለው። “ከእንግዲህ ሀጢአት ለመፈፀም ምንም ፍላጎት የለንም፣ ነገር ግን ያለማቋረጥ መልካምን መስራት እንጂ” በማለት ወደ ታላቅ የልብ ለውጥ ያመራናል።18 የንስሀ መግባት አስፈላጊነት ቀላል አይደለም። ዘለአለማዊ አስፈላጊነት ያላቸው ነገሮች እምብዛም አይደሉም። ነገር ግን ውጤቱ ዋጋ አለው። ለቤተክርስቲያን ሰባዎች ፕሬዘዳንት ቦይድ ኬ ፓከር የመጨረሻ ንግግር ላይ እንዲህ መሰከሩ፤ “ሀሳቡ ይህ ነው፤ የሀጢአት ክፍያው መንገዶችን፣ ያለፉ ዱካዎችን አይተውም። የሚያስተካክለው ሁሉ ይስተካከላል።… የሀጢአት ክፍያው መንገዶችን፣ ያለፉ ዱካዎችን አይተውም። ይፈውሳል፣ እናም የሚፈውሰው እንደተፈወሰ ይቆያል።”19

እናም ከአብ ጋር እንደገና የመኖር ተስፋችን በኢየሱስ ክርስቶስ የሀጢአት ክፍያ ላይ የሚወሰን በመሆኑ፣ ከፍትህ ጥያቄ በተቃርኖ፣ የሰውን ዘር አጠቃላይ የሀጢአት ሸክም፣ አንዳንድ የእግዚአብሔር ወንድ እና ሴት ልጆች ያላስፈላጊ በራሳቸው ለመሰቃየት የመረጡትን ሀጢአቶች ጨምሮ፣ በላዩ ላይ ለመውሰድ በፈቀደው አንድ ከሀጢአት ነፃ በሆነው ላይ የተወሰነ ነው።

እንደ የኋለኛው ቀን ቅዱሳን የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን አባላት፣ ቃልኪዳኖችን ከገባን፣ ያለማቋረጥ ንሰሀ ከገባን፣ እና እስከመጨረሻው ከፀናን፣ ከእርሱ ጋር የጋራ ወራሾች እንደምንሆን20 እና ልክ እንደ እርሱ አብ ያለውን ሁሉ እንደምንቀበል ስለምናውቅ፣21 ከሌሎች አብዛኛው ሰዎች በተሸለ የአዳኝ የሀጢአት ክፍያው የበለጠ ሀይል እንዳለው እንረዳለን። የህ የሚያስደንቅ ትምህርት ቢሆንም እውነት ነው። የኢየሱስ ክርስቶስ የሀጢአት ክፍያ የአዳኝ ግብዣ የሆነውን፣ “በሰማይ ያለው አባታችሁ ፍፁም እንደሆነ፣ እንዲሁ እናንተም ፍፁማን ሁኑ”22 የሚለውን በሚያሰለች ሁኔታ የማይደረስበት ሳይሆን በደምብ የሚቻል ያደርገዋል።

ቅዱስ መጽሐፍት ሁሉም ሰው “እንደ እግዚአብሔር ቅዱስ ፍርድ መሰረት ይፈረድባቸዋል”23 በማለት ያስተምራሉ። በዚያ ቀን በብዙ ሰዎች ውስጥ ለመደበቅ ወይም ንፁህ ላለመሆናችን ምክንያት ወደሌላው ለመጠቆም እድል አይኖርም። በአመስጋኝነት፣ ቅዱሳን መጽሐፍት ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ለእኛ ሀጢአት የተሰቃየው፣ ከአብ ጋር የሚማልደን፣ ጓደኞቼ ብሎ የሚጠራን፣ እስከመጨረሻው የወደደን፣ የመጨረሻ ፈራጃችን እንደሚሆንም ያስተምራሉ። ከኢየሱስ ክርስቶስ የሀጢአት ክፍያው በረከቶች ውስጥ በብዛት ትኩረት የተነፈገው “አብ… ፍርድን ሁሉ ለወልድ ሰጠው” የሚለው ነው።24

ወንድሞች እና እህቶች፣ ብርታት ማጣት ከተሰማችሁ ወይም ከቆፈራችሁት የመንፈሳዊ ጉድጓድ ውስጥ መውጣት መቻላችሁ ካሳሰባችሁ፣ እባካችሁ “በፍርድ መሀል” የቆመውን እና “ለሰው ልጆች አንጀቱ በምህረት በመሞላት፣” እናም የእኛን ሀጢአቶች እና ስህተቶች በእራሱ ላይ የወሰደውን እና “የፍትህን ፍላጎት ያሟላውን” እርሱን አስታውሱ።25 በሌላ ቃላት፣ ኔፊ በግል ጥርጣሬው ወቅት እንዳደረገው፣ በቀላሉ “የታመናችሁበትን”፣26 ኢየሱስ ክርስቶስን አስታውሱ፣ እና ከዛ ንስሀ ግቡ እና አሁንም “ፍፁም የተስፋ ብርሀንን” ተለማመዱ።27 በኢየሱስ ክርስቶስ ስም፣ አሜን።