2010–2019 (እ.አ.አ)
ከእናንተ ውስጥ የሚበልጠው
ሚያዝያ 2017 (እ.አ.አ)


ከእናንተ ውስጥ የሚበልጠው

የእግዚአብሔር ሽልማት ያለምንም የሽልማት ጥበቃ ለሚያገለግሉት ይሆናል።

ውድ ወንድሞች፣ ውድ ጐደኞች፣ በዚህ በሚያነሳሳ የአለም አቀፍ የክህነት ስብሰባ ከእናንተ ጋር በመገኘቴ ታላቅ ምስጋና አለኝ። ፕሬዘደንት፣ ለመልእክትዎ እና በረከትዎ እናመሰግናለን። እኛ የመመሪያ ቃላትዎን፣ ምክርዎን፣ እና ጥበብዎን ሁልጊዜም በልብ እንቀበላለን። እንወድዎታለን እና እንደግፎታለን፣ እናም ለእርስዎ ዘወትር እንጸልያለን። በእርግጥም የጌታ ነቢይ ኖት። ፕሬዘደንታችንም ኖት። እንደግፍዎታለን፣ እንወድዎታለን።

ከሁለት አስርተ አመታት በፊት አከባባ፣ የማድሪድ ስፔን ቤተመቅደስ ተባርከ እና እንደ የጌታ ቅዱስ ቤት አገልግሎት መስጠት ጀመረ። ሀሪየት እና እኔ በደምብ ይህን እናስታውሰዋለን ምክንያተም በዛ ወቅት እኔ በአውሮፓ የክልል አመራር ውስጥ ሳገለግል ነበር። ከሌሎች ብዙ ሰዎች ጋር በመሆን፣ በእቅድ ዝርዝር ውስጥ እና ወደ መባረኩ በሚወስዱ ክስተቶችን በማዘጋጀት ብዙ ሰአታትን አጠፋን።

የቤተመቅደሱ መባረኪያ ቀን እየደረሰ ሲመጣ፣ እሰከዛ ድረስ እኔ እንድካፈል አለመጋበዜን አስተዋልኩ። ይሄ ትንሽ ያልተጠበቀ ነበር። ምንም ቢሆን፣ እኔ የክልል ፕሬዘዳንት በመሆኔ ባለኝ ሀላፊነት፣ በቤተመቅደስ ስራ ውስጥ በደምብ ተሳትፌያለሁ እና ትንሽም ቢሆን ባለቤትነት ተሰምቶኝ ነበር።

የተጋበዝነበትን እንዳየች ጠየኳት። አላየችም።

ቀናት አለፉ እና ጉጉቴ ጨመረ። የግብዣው ወረቀት ጠፍቶ ይሆን ብዬ አሰብኩ—ምናልባት ከሶፋችን ስር ተቀብሮ ይሆናል። ከማይፈለጉ ደብዳቤዎች ጋር ተቀላቅሎ እና ተጥሎ ይሆናል። ጎሮቤቶቻችን አስቸጋሪ ድመት አላቸው፣ እና ድመቱን በጥርጣሬ ማየት ሁላ ጀመርኩ።

በስተመጨረሻ እውነታውን ለመቀበል ተገደድኩ፤ እኔ አልተጋበዝኩም።

ግን ያ እንዴት ሊሆን ይችላል? የሚያናድ ነገር አድርጌ ይሆን? እኛ ለመጓዝ እሩቅ ይሆንብናል ብለው አስበው ይሆን? ተረስቼ ይሆን?

ቀስ በቀስ፣ ይሄ አይነት አስተሳሰቤ መሆን ወደማልፈልግበት ቦታ እየመራኝ እንደነበር አስተዋልኩ።

ሀሪየት እና እኔ የቤተመቅደሱ ምርቃት ስለ እኛ እንዳልነበር እራሳችንን አስታወስን። ስለ ተጋበዘ እና ስላልተጋበዘው ሰው አይደለም። በፍፁም ስለ እኛ ስሜት ወይም ስለ የባለቤትነት ስሜታችን አይደለም።

ስለ ቅዱሱ ቤት ምረቃ ነው፣ የሐያሉ አምላክ ቤተመቅደስ። በስፔን ላሉ የቤተክርስቲያን አባላት የደስታ ቀን ነበር።

እንድካፈል ተጋብዤ ቢሆን ኖሮ፣ በደስታ አደርገው ነበር። ነገር ግን ያልተጋበዝኩ ከሆነም፣ ደስታዬ ፍጹም ጥልቅ ከመሆኑ አይቀንስም ነበር። ሀሪያት እና እኔ ከጓደኞቻችን፣ ከተወዳጆቹ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ጋር እንደሰታለን። ለዚህ ታላቅ በረከት እኛም በፍራንክፈርት በቤታችን ውስጥ በማድሪድ በሚኖሩት የጋለ ስሜት አይነት እግዚአብሔርን እናመሰግነዋለን።

የነጎድጓድ ልጆች

ኢየሱስ ከጠራቸው እና ከሾማቸው ከአስራ ሁለቱ ውስ ሁለት ወንድማማቾች ነበሩ፣ ያዕቆብ እና ዮሐነስ። የሰጣቸውን የቅፅል ስም ታስታውሳላችሁ?

የነጎድጓድ ልጆች ((ቦአኔርጌስ)።1

ከጀርባው ድንቅ ታሪክ ከሌለ በስተቀር እንደዛ አይነት ቅፅል ስም አይሰጥም። እንደ እድል ሳይሆን ቅዱሳት መፅሐፍት ስለ ቅፅል ስሙ አመጣጥ ብዙ ማብራሪያ አያቀርቡም። ቢሆንም፣ ስለ ያቆብ እና ዮሐነስ ባህሪ በትንሹ እናውቃለን። እነርሱን ወደ ከተማው እንዲገቡ ስላልተጋበዙ እሳት ከሰማይ የሰማሪያው መንደር ላይ ማውረድን እንደ አማራጭ ያቀረቡት ወድማማቾች ናቸው።2

ያዕቆብ እና ዮሐነስ አሳ አጥማጆች ነበሩ—ብዙም ተሞክሮ ያላቸው ባይሆኑም—ነገር ግን የተፈጥሮን ምንነት በደምብ ያውቁ ነበር። በእርግጥም፣ የተግባር ሰዎች ነበሩ።

በአንድ አጋጣሚ፣ አዳኝ ወደ ኢየሩሳሌም የመጨረሻ ጉዞውን ለማድረግ ሲዘጋጅ፣ ያዕቆብ እና ዮሐነስ—ለቅፅል ስማቸው የሚመጥን አይነት አንድ ጥያቄ ይዘው ወደ እርሱ ቀረቡ።

“የምንለምንህን ሁሉ እንድታደርግልን እንፈልጋለን፣” አሉ።

“ምን እንዳደርግላችሁ ትወዳላችሁ?” ብሎ ሲመልስላቸው ኢየሱስ ፈገግ እንዳለ እገምታለሁ።

“በክብርህ ጊዜ አንዳችን በቀኝ አንዳችንም በግራህ መቀመጥን ስጠን።”

አዳኝም እየጠቁ ስለነበረው ነገር በደምብ እንዲያስቡበት አደረጋቸው፣ “በቀኝና በግራ መቀመጥ ግን ለተዘጋጀላቸው ነው እንጂ የምሰጥ እኔ አይደለሁም።”3

በሌላ አነጋገር፣ የመንግስተ ሰማይ ክብር የሚገኘው የድጋፍ ቅስቀሳ በማድረግ አይደልም። በግል ትውውቅ ወደ ዘለአለማዊ ክብር መጓዝ አይቻልም።

የነጎድጓድ ልጆች ስላቀረቡት ጥያቄ ሌሎቹ አስር ሐዋርያት ሲሰሙ፣ ብዙም ደስተኛ አልነበሩም። ኢየሱስ ጊዜው አናሳ መሆኑን ያውቅ ነበር፣ እናም ስራውን በሚያስቀጥሉት መካከል አለመግባባት ማየቱ ሳያሳስበው አልቀረም።

ስለ ሀይል ተፈጥሮ ነገራቸው እና የሚሹት እና የሚሸከሙት ላይ እንዴት ተፅእኖ እንዳለው ለአስራ ሁለቱ ነገራቸው። “በአለም ላይ ያሉ አለቆች” እንዲህ አለ፣ “በሌሎች ላይ እንዲሰለጥኑ ታውቃላችሁ።”

አዳኝ የእነዚያ ታማኝ እና አማኝ ደቀመዛሙርትን ፊት ማብቂያ በሌለው ፍቅር ሲመለከታቸው ይታየኛል። የልመና ድምጻፈውን እስከምሰማ ድረስ ነኝ፥ “በእናንተስ እንዲህ አይደለም። ነገር ግን፣ ማንም ከእናንተ ታላቅ ሊሆን የሚወድ የእናንተ አገልጋይ ይሁን፥ ከእናንተም ማንም ፊተኛ ሊሆን የሚወድ የሁሉ ባርያ ይሁን።”4

በእግዚአብሔር መንግስት ውስጥ፣ ታላቅነት እና መሪነት ማለት ሌሎችን በእውነተኛ ማንነታቸው ማየት—እግዚአብሔር እንደሚያያቸው ማየት—ማለት ነው እና ከዛም ለእነርሱ መድረስ እና ማገልገል ነው። ያም ማለት ደስተኛ ከሆኑት ጋር መደሰት፣ ካዘኑት ጋር ማንባት፣ ጭንቀት ውስጥ ያሊትን ከፍ ማድረግ፣ እናም ክርስቶስ እኛን እንደሚወደን እኛም ጎረቤቶቻችንን መውደድ ማለት ነው። አዳኝ በምንም የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳይ፣ ዘር፣ ቋንቋ፣ የፖለቲካ አመለካከት፣ ዜግነት ወይም ሌላ ምንም አይነት ቡድን ውስጥ ያሉ ሁሉንም የእግዚአብሔር ልጆችን ያፈቅራቸዋል። እኛም ማድረግ ይገባናል!

የእግዚአብሔር ሽልማት ያለምንም የሽልማት ጥበቃ ለሚያገለግሉት ይሆናል። ያለ ውዳሴ መሻት ለሚያገለግሉ፣ በምስጢር ሌሎችን ለመርዳት ለሚሹት፤ እግዚአብሔርን እና ልጆቹን ስለሚወዱ ብቻ ሌሎችን ለሚያገለግሉ ሁላ የእግዚአብሔር ታላቁ ሽልማት ይሆናል።5

በመጥፎ ጎኑ አትውሰደው

እንደ አዲስ የአጠቃላይ አመራር ከተጠራሁ ከጥቂት ጊዜ በኋላ አንድ ካስማን ዳግም ለማዋቀር ከፕሬዘዳንት ጀምስ ኢ. ፎስት ጋር ለመሆን እድሉን አግኝቼ ነበር። በሚያምረው የደቡባዊ ዩታህ ወደ ተመደብንበት ለመሄድ መኪና እየነዳሁ ሳለሁ፣ ፕሬዘዳንት ፎስት በመልካምነት እኔን ለመምራት እና ለማስተማር ጊዜውን ተጠቀሙበት። መቼም የማልረሳው ትምህርት ነበር። እንዲህ አሉኝ፣ “የቤተክርስቲያኑ አባላት ያሞግሱሀል። በደግነት ይንከባከቡሀል እና መልካም ነገር ስላንተ ያወራሉ።” ከዛም ትንሽ ዝም ብለው እንዲህ አሉ፣ “ዲይተር፣ ሁሌም ስለዚህ አመስጋኝ ሁን፣ ነገር ግን መቼም በመጥፎ ጎኑ አትውሰደው በመጥፎ ጎኑ አትውሰደው።”

ስለቤተክርስቲያን አገልግሎት የተሰጠው ይሄ ትምህርት በቤተክርስቲያን ውስጥ በሁሉም ክፍሎች ውስጥ ላሉ የክህነት ተሸካሚዎች ሁሉ የሚሆን ነው። በዚህ ቤተክርስቲያን ውስጥ ላለነው ሁሉ ይሆናል።

ፕሬዘዳንት ጄ. ሩበን ክላርክ በቤተክርስቲያን ውስጥ በሀላፊነት ድርሻ ላይ የተጠሩትን ሲመክሩ፣ ህግ ቁጥር ስድስትን እንዳይረሱ ይናሯቸው ነበር።

ያለጥርጥር፣ ሰው እንዲህ ብሎ ይጠይቃል፣ “ህግ ቁጥር ስድስት ምንድነው?”

“እራሳችሁን በሌሎች እይታ አጥብካችሁ አትውሰዱ፣” ነው ይላሉ።

በእርግጥ፣ ይሄ ጥያቄን ያስከትላል፥ “ሌሎቹ አምስት ህግጋት ምንድናቸው?”

በመገረም አይኖች፣ ፕሬዘዳንት ክላርክ እዲህ ይላሉ፥ “ሌላ ምንም የለም።”6

ውጤታማ የቤተክርስቲያን መሪ ለመሆን፣ ይሄንን ወሳኝ ትምህርት መማር ይኖርብናል፤ በቤተክርስቲያን ውስጥ መሪነት ማለት በእግዚአብሔር መመራትን ስለመሻት እንጂ ያን ያህል ሌሎችን ስለመምራት አይደለም።

ጥሪዎች እንደ አገልግሎት እድሎች

እንደ የሀያሉ አምላክ ቅዱሳን፣ “በሁሉም ሁኔታ ድሆችን እና እርዳታ የሚሹትን፣ የታመሙትን እና የታረዙትን አስታውሱ፣ እንዚህን ነገሮች የማያደርግ፣ ያ የእኔ ደቀመዝሙር አይደለም።”7 ሌሎችን የማገልገል እድሎች ውስን አይደሉም። በማህበረሰባችን ውስጥ፣ በአጥቢያ እና ቅርንጫፎቻችን ውስጥ፣ እና በእርግጠኝት በቤቶቻችን ውስጥ እናገኛቸዋለን።

በተጨማሪም፣ እያንዳንዱ የቤተክርስቲያን አባል ለማገልገል እድል ተሰጥቶታል። እነዚህ እድሎች “ጥሪዎች” በመባል ይታወቃሉ—ቃሉ እኛ እንድናገለግል የሚጠራን ማን እንደሆነ ሊያስታውሰን ይገባል። ጥሪዎቻችንን በእምነት እና ትህትና እግዚአብሔርን እና ሌሎችን ለማገልገል እንደተሰጠን እድል አድርገን ከወሰድናቸው፣ እያንዳንዱ የአገልግሎት ተግባር በደቀመዝሙርነት መንገድ ላይ ያለ ጉዞ ይሆናል። እዚህ መንገድ፣ እግዚአብሔር የእርሱን ቤተክርስቲያን እንዲሁም አገልጋዮቹን ይገነባል። ቤተክርስቲያኗ የተቀረፀችው እኛ እውነተኛ እና ታማኝ የክርስቶስ ተከታዮች፣ መልካም እና ድንቅ የእግዚአብሔር ወንድ እና ሴት ልጆች እድንሆን ለመርዳት ነው። ይሄ የሚሆነው ስብሰባዎችን ለመካፈል ስንሄድ እና ንግግሮችን ስናዳምጥ ብቻ አይደለም፣ ነገር ግን ከራሳችን ውጪ ሌሎችን ስናገለግልም ነው። ይሄ በእግዚአብሔር መንግስት ውስጥ “ታላቅ” የምንሆንበት መንገድ ነው።

ጥሪዎችን በፀጋ፣ በትህትና፣ እና በአመስጋኝነት እንቀበላለን። ከእነዚህ ጥሪዎች ስንለቅ፣ ለውጡን በተመሳሳይ ፀጋ፣ ትህትና እና አመስጋኝነት እንቀበላለን።

በእግዚአብሔር እይታ አንዱ ከሌላው የሚበልጥ በመንግስቱ ውስጥ ያለ ጥሪ የለም። የእኛ አገልግት—ታላቅም ይሁን አናሳ—መንፈሶቻችንን ይሞላል፣ የሰማይን መስኮት ይከፍታል፣ እናም በምናገለግላቸው ላይ ብቻ ሳይሆን በእኛም ላይ በረከቶችን ያመጣል። እና ለሌሎች ስደርስላቸው፣ እግዚአብሔር አገልግሎታችንን እንደሚያውቅ እና እንደሚያስደስተው በትሁት መተማመን ማወቅ እንችላለን። እነዚህን ልብ የሚነኩ የርህራሄ ድርጊቶችን፣ በተለይም በሌሎች የማይታዩ እና የማይስተዋሉትን ስናቀርብ፣ እርሱ ወደ እኛ ፈገግ ይላል።8

 ከእራሳችን ለሌሎች በምንሰጥበት እያንዳንዱ ጊዜ፣ ለእኛ ሁሉንም ለሰጠን መልካም እና እውነተኛ ደቀመዝሙሩ ወደ መሆን አንድ ደረጃ እንቀርባለን።

ከአመራርነት ወደ የመንገድ አፅጂነት

መስራቾች ወደ ሶልት ሌክ ቫሊ የደረሱበት 150ኛ አመት አከባበር ወቅት፣ ወንድም ማይሮን ሪቺንስ በሄነፈር፣ ዩታህ ውስጥ የካስማ ፕሬዘዳንት ሆኖ ያገለግል ነበር። ክብረበአሉ መስራቾች በእርሱ ከተማ ያለፉበትን ዳግም ማደስን የሚያካትት ነበር።

ፕሬዝዳንት ሪቺንስ የበአሉ እቅዶች ላይ በጣም እየተሳተፉ ነበር፣ እናም ከብዙ አጠቃላይ አመራሮች እና ሌሎችም ጋር ክስተቶቻቸውን ለመወያየት ብዙ ስብሰባዎችን ተካፈሉ። እርሱም በሙሉ ተሳታፊ ነበር።

ልክ ከበአሉ ቀደም ብሎ፣ የፕሬዘዳንት ሪቺንስ ካስማ ዳግም ተዋቀረ፣ እና ከፕሬዘዳንትነታቸው ተነሱ። በተከታዩ እሁድ፣ መሪዎች በበአሉ ላይ እንዲያግዙ ፍቃደኞችን ሲጠይቁ የአጥቢያ የክህነት ስብሰባውን እየተካፈሉ ነበሩ። ፕሬዘዳንት ሪቺንስ፣ ከሌሎች ጋር፣ እጃቸውን አወጡ እናም የስራ ልብስ እንዲለብሱ እና መኪናቸውን እና አካፋ እንዲያመጡ መመሪያ ተሰጣቸው።

በስተመጨረሻ፣ የታላቁ ክስተት ማለዳ ደረሰ፣ እና ፕሬዘዳንት ሪቺንስ የፍቃደኛነት ሀላፊነታቸውን ለመወጣት ሄዱ።

ከጥቂት ሳምንታት በፊት፣ ለዚህ ወሳኝ ክስተት እቅድ እና አመራር ላይ ተፅእኖ ያለው ተሳታፊ ነበር። ሆኖም፣ በእዚያ ቀን፣ ስራቸው በመንገዱ ላይ ፈረሶችን መከተል እና ከስራቸው ማፅዳት ነበር።

ፕሬዘዳንት ሪቺንስ በደስታ ነበር ያደረጉት።

አንድ የአገልግሎት አይነት ከሌላው እደማይበልጥ ተረድተው ነበር።

እንዲህ የሚለውን የአዳኝ ቃላትን ያውቁና ወደ ተግባር ለውጠው ነበር፥ “ከእናንተም የሚበልጠው አገልጋያችሁ ይሆናል።”9

ደቀመዝሙርነትን በትክክል ማድረግ

አንዳንዴ፣ ልክ እንደ ነጎድጓድ ልጆች፣ ከፍተኛ የስራ መደቦችን እንፈልጋለን። ለመታወቅ እንጥራለን። መምራት እና ለየሚታወስ መዋጮን ለማድረግ እንሻለን።

ጌታን ለማገልግል መፈለግ ምንም ስህተት የለውም፣ ነገር ግን ለእራሳችን ምክንያት በቤተክርስቲያን ውስጥ ተፅእኖ ለማግኘት—የሰውን አድናቆት እና ሙገሳ ለማግኘት—ስንሻ ሽልማታችንን አግኝተናል። የሌሎችን “ሙገሳ በሌላ ጎኑ” ስንወስድ፣ ያ የሌሎች ሙገሳ የእኛ ክፍያ ይሆናል።

በቤተክርስቲያን ውስጥ በጣም አስፈላጊው ጥሪ የቱ ነው? አሁን ያላችሁ ጥሪ ነው። ምንም ያህል ዝቅተኛ ወይም ታላቅ ቢመስልም፣ አሁን ያላችሁ ጥሪ ሌሎችን ከፍ እንድታደርጉ ብቻ ሳይሆን ነገር ግን ወደ ተፈጠራችሁለት የእግዚአብሔር ሰው ወደመሆን ያመጣችኋል።

ውድ ጓደኞቼ እና የክህነት ወንድሞች፣ ባላችሁበት ሁኔታ ከፍ አድርጉ!

ጳውሎስ የፊልጵስዮስ ሰዎችን እንዲህ አስተማረ፣ “በከንቱ ውዳሴ ምክንያት አንድ እንኳ አታድርጉ፣ ነገር ግን እያንዳንዱ ባለንጀራው ከራሱ ይልቅ እንዲሻል በትህትና ይቁጠር።”10

በክብር ማገልገል

በቤተክርስቲያኗ ውስጥ ክብር እና ታዋቂነትን እውነትን እና ወደ ሌሎች ያለንን ቱሁት አገልግሎት በመስዋዕት ማስቀመጥ መፈለግ የኢሳው ንግድ ነው።11 የምድር ሽልማት እናገኝ ይሆናል፣ ነገር ግን በታላቅ ዋጋ መከፈል ነው የሚመጣው—ይህም ይህም የሰማይ ደስታ ነው።

የዋህ እና ትሁት የነበረውን፣ የሰውን ሙገሳ ሳይሆን ነገር ግን የአባቱን ፍላጎት ለማድረግ የተጋውን፣ የአዳኛችንን ምሳሌ እንከተል።12

ሌሎችን በትህትና—በጥንካሬ፣ በአመሰጋኝነት፣ እና በክብር እናገልግል። ምንም ያህል አገልግሎታችን ትንሽ፣ የተለመደ፣ ወይም አነስተኛ ዋጋ ያለው ቢመስልም፣ ለሌሎች በደግነት እና እርህራሄ የሚደርሱ አንድ ቀን በዘለአለማዊ እና በተባረከ የሀያሉ እግዚአብሔር ፀጋ የአገልግሎታቸውን ዋጋ ያውቃሉ።13

ውድ ወንድሞች፣ ውድ ጓደኞች፣ እንዲህ የሚለውን ይሄን ታላቅ የቤተክርስቲያን መሪነት እና የክህነት አስተዳደራዊ ትምህርት እናሰላስል፣ እንረዳ እናም እንኑረው፥ “ከእናንተም የሚበልጠው አገልጋያችሁ ይሆናል።” ይህም ጸሎቴ እና በረከቴ የሚሆነው በመምህራችን፣ በቤዛችን፣ ቅዱስ ስም፣ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ነው፣ አሜን።