ቅዱሳት መጻህፍት
፩ ኔፊ ፲፩


ምዕራፍ ፲፩

ኔፊ የጌታን መንፈስ አየ እና የህይወት ዛፍ በራዕይ ታየው—እርሱም የእግዚአብሔርን ልጅ እናት አየ እናም ስለእግዚአብሔር ትህትና ተማረ—እርሱም የእግዚአብሔርን በግ ጥምቀት አገልግሎትና ስቅለት አየ—እናም ደግሞ የአስራ ሁለቱን የበጉን ሐዋርያት ጥሪና አገልግሎት አየ። ከ፮፻–፭፻፺፪ ም.ዓ. ገደማ።

እናም እንዲህ ሆነ አባቴ ያየውን ነገሮች ለማወቅ ከፈለግሁ በኋላ፣ እናም ጌታ ሊያሳውቀኝ እንደሚችል በማመን በልቤ እያሰላሰልኩ ተቀምጬ ሳለሁ በጌታ መንፈስ፣ አዎን፣ በፊት አይቼው ወደማላውቀውና ከዚህ በፊት በእግሮቼ ቆሜበት ወደማላውቀው እጅግ ከፍ ያለ ተራራ ተወሰድኩ

እነሆ መንፈስ፣ ምን ትፈልጋለህ? አለኝ።

እና እኔም አልሁ፥ አባቴ ያያቸውን ነገሮች ማየት እፈልጋለሁ።

እና መንፈስም አለኝ—አባትህ የተናገረውን ዛፍ እንዳየ ታምናለህን?

እናም እኔ አልኩ—አዎን፣ የአባቴን ቃላት በሙሉ እንደማምን አንተ ታውቃለህ።

እናም እነዚህን ቃላት ስናገር መንፈስ በታላቅ ድምፅ እንዲህ ሲል ጮኸ፥ ሆሳዕና ለጌታ ለልዑል እግዚአብሔር፤ እርሱ በምድር ሁሉ ላይ፣ አዎን፣ ከሁሉም በላይ አምላክ ነው። እናም አንተ፣ ኔፊ፣ የተባረክህ ነህ፣ ምክንያቱም አንተ በልዑል እግዚአብሔር ልጅ አምነሀልና፣ ስለዚህ የተመኘሀቸውን ነገሮች ታያለህ።

እና እነሆ እነዚህ ነገሮች ለአንተ ለምልክት ይሰጡሀል፣ አባትህ የቀመሰውን ፍሬ የሚሰጠውን ዛፍ ካየህ በኋላ ደግሞም አንድ ሰው ከሰማይ ሲወርድ ታያለህ፣ እናም አንተ እርሱን ታያለህ፤ እናም ካየኸውም በኋላ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ ትመሰክራለህ

እናም እንዲህ ሆነ መንፈስ እንዲህ አለኝ—ተመልከት! ተመለከትኩና ዛፍን አየሁ፤ አባቴም እንዳየው አይነት ዛፍ ነበር፤ ውበቱም አዎን ከሁሉም ውብ ነገር የላቀ ነበር፤ ንጣቱም ከሚገፋው በረዶ ንጣት የላቀ ነበር።

እናም እንዲህ ሆነ ዛፉን ካየሁ በኋላ፣ ለመንፈሱ፥ ከሁሉ በላይ የከበረውን ዛፍ እንዳሳየኸኝ ተመለከትኩ አልኩት።

እናም እርሱ፥ አንተ ምን ትፈልጋለህ? አለኝ።

፲፩ እናም እኔ ለእርሱ፥ ትርጓሜውን ለማወቅ ነው አልኩት—እኔም ሰው እንደሚናገረው ለእርሱ ተናገርኩት፤ ምክንያቱም እርሱ በሰው አምሳል እንደነበር ስለተመለከትኩ ነው፤ ይሁን እንጂ፣ የጌታ መንፈስ መሆኑን አውቅ ነበር፣ እናም ሰው ከሌላ እንደሚነጋገር እርሱ እኔን ተናገረኝ።

፲፪ እናም እንዲህ ሆነ እርሱ እኔን፥ ተመልከት! አለኝ፣ እኔም እርሱን ለመመልከት ዞርኩ እናም አላየሁትም ከእኔ ዘንድ ሄዶ ነበርና።

፲፫ እናም እንዲህ ሆነ እኔ ተመለከትኩ፣ እናም ታላቂቷን የኢየሩሳሌም ከተማ፣ ደግሞም ሌሎች ከተሞችን አየሁ። የናዝሬትንም ከተማ ተመለከትኩ፣ በናዝሬትም ከተማ አንዲት ድንግል ተመለከትኩ፣ እርሷም እጅግ ውብና ያማረች ነበረች።

፲፬ እናም እንዲህ ሆነ ሰማያት ሲከፈቱ አየሁ፤ እናም አንድ መልአክ ወረደና በፊቴ ቆመ፤ እንዲህም አለኝ፥ ኔፊ፣ ምን ትመለከታለህ?

፲፭ እናም አንዲት ከድንግሎች ሁሉ በላይ መልካም፣ በጣም ቆንጆ ድንግል፣ በማለት ተናገርኩት።

፲፮ እናም የእግዚአብሔርን ትህትና ታውቃለህ? አለኝ።

፲፯ እናም እርሱ ልጆቹን እንደሚወድ አውቃለሁ፣ ይሁን እንጂ፣ የሁሉን ነገሮች ትርጉም አላውቅም አልኩት።

፲፰ እነሆ የተመለከትካት ድንግል በስጋ የእግዚአብሔር ልጅ እናት ናት አለኝ።

፲፱ እናም እንዲህ ሆነ፣ እርሷ በመንፈስ እንደተወሰደች ተመለከትኩ፤ እና ለጥቂት ጊዜ በመንፈስ ከተወሰደች በኋላ መልአኩ እንዲህ ሲል ተናገረኝ፥ ተመልከት!

እናም በድጋሚ ድንግሊቷ፣ በክንዷ ልጅ ይዛ አየሁ፣ እንዲሁም ተመለከትኩ።

፳፩ እናም መልአኩ እንዲህ አለኝ፥ እነሆ የእግዚአብሔር በግ፣ አዎን እንዲያውም የዘላለማዊው አባት ልጅ! አባትህ ያየውን ዛፍ ትርጉም ታውቃለህ?

፳፪ እናም እንዲህ ስል መለስኩለት፤ አዎን፣ ይህ በሰው ልጆች ልብ ውስጥ ሁሉ ራሱን በስፋት የሚያፈስ የእግዚአብሔር ፍቅር ነው፤ ስለዚህ ከሁሉ ነገሮች በላይ መልካም ነው።

፳፫ እርሱም፣ አዎን፣ ለነፍስም በጣም ደስ የሚያሰኝ ነው አለኝ።

፳፬ እነዚህንም ነገሮች ካለ በኋላ፣ እንዲህ አለኝ—ተመልከት! እናም የእግዚአብሔር ልጅ በሰው ልጆች መካከል ሲሄድ ተመለከትኩ፤ ብዙዎችም በእግሩ ስር ሲወድቁና ሲሰግዱለት ተመለከትኩ።

፳፭ እናም እንዲህ ሆነ አባቴ ያየው የብረት በትር፣ ወደ ህይወት ውሃዎች ምንጭ፣ ወይንም ወደ ህይወት ዛፍ፣ የሚመራው የእግዚአብሔር ቃል እንደሆነ ተመለከትኩ፤ ውሃዎቹም የእግዚአብሔር ፍቅር ምልክት ናቸው፤ ደግሞም የህይወት ዛፉም የእግዚአብሔር ፍቅር ምልክት መሆኑን አየሁ።

፳፮ እናም መልአኩ እንደገና እንዲህ አለኝ—የእግዚአብሔርን ትህትና እይ እንዲሁም ተመልከት አለኝ።

፳፯ እናም እኔ ተመለከትኩና አባቴ የተናገረለትንም የዓለም መድኃኒት ተመለከትኩ፣ ደግሞም ከእርሱ በፊት መንገዱን የሚያዘጋጀውን ነቢይ ተመለከትኩ። የእግዚአብሔርም በግ ሄዶ በእርሱ ተጠመቀ፣ ከተጠመቀም በኋላ፣ ሰማያት ሲከፈቱና መንፈስ ቅዱስ ከሰማይ ሲወርድና በእርግብ አምሳል በእርሱ ላይ ሲያርፍ ተመለከትኩ።

፳፰ እናም እርሱ ህዝቡን በኃይልና በታላቅ ክብር እያገለገለ ሲሄድ ተመለከትኩ፤ ብዙ ህዝብም ሊያዳምጡት ተሰበሰቡ፤ ከመካከላቸው ሲያስወጡትም ተመለከትኩ።

፳፱ እናም ደግሞ ሌሎች አስራ ሁለት ሲከተሉት ተመለከትኩ። እናም እንዲህ ሆነ ከፊቴ በመንፈስ ተወሰዱም ተሰወሩብኝም።

እናም እንዲህ ሆነ መልአኩ በድጋሚ እንዲህ አለኝ፣ ተመልከት! እናም ተመለከትኩና፣ ሰማያት እንደገና ሲከፈቱ ተመለከትኩ፣ መላዕክትም በሰው ልጆች ላይ ሲወርዱ አየሁ፤ እነርሱንም አገለገሏቸው።

፴፩ እንደገናም እንዲህ ሲል ተናገረኝ፥ ተመልከት! እኔም ተመለከትኩ፣ እናም የእግዚአብሔር በግ በሰው ልጆች መካከል ሲሄድ ተመለከትኩ። ብዛት ያላቸው የታመሙ እና በብዙ በሽታዎች፣ በአጋንንትና በርኩሳን መናፍስት የሚሰቃዩ ሰዎችንም ተመለከትኩ፣ መልአኩም እነዚህን ሁሉ ነገሮች ለእኔ ተናገረም አሳየኝም። እነርሱም በእግዚአብሔር በግ ኃይል ተፈወሱ፣ እናም አጋንንትና ርኩሳን መናፍስትም ወጥተዋል።

፴፪ እናም እንዲህ ሆነ መልአኩ በድጋሚ እንዲህ ሲል ተናገረ—ተመልከት! እኔም የእግዚአብሔር በግ በሰዎች ሲወሰድ ተመለከትኩ፣ አዎን፣ የዘለዓለማዊው እግዚአብሔር ልጅ በዓለም ተፈረደበት፤ እኔም አየሁ፣ ምስክርም ሰጠሁ።

፴፫ እናም እኔ ኔፊ፣ ለዓለም ኃጢያት በመስቀል ላይ ሲሰቀልና ሲገደል ተመለከትኩ።

፴፬ እናም እርሱ ከተገደለ በኋላ የምድሪቱ ሰዎች የበጉን ሐዋርያት ለመዋጋት ሲሰበሰቡ ተመለከትኩ፣ ምክንያቱም እንደዚህ ነበር አስራ ሁለቱ በጌታ መልአክ የተጠሩት።

፴፭ እናም ብዙ የምድሪቱ ሰዎች በአንድነት ተሰበሰቡ፤ አባቴም እንዳየው ህንፃ አይነት ትልቅና ሰፊ ህንፃ ውስጥ እንደነበሩ ተመለከትኩ። እናም የጌታ መልአክ እንዲህ ሲል እንደገና ተናገረኝ፥ እነሆ ዓለምና በውስጧ ያለው ጥበብ፣ አዎን፣ እነሆ የእስራኤል ቤት የበጉን አስራ ሁለት ሐዋርያት ለመዋጋት በአንድነት ተሰበሰቡ።

፴፮ እናም እንዲህ ሆነ ትልቁና ሰፊው ህንፃ የዓለም ኩራት መሆኑን አየሁ፣ መሰከርኩም፤ ይህም ወደቀ፣ ውድቀቱም እጅግ ታላቅ ነበር። በድጋሚም የጌታ መልአክ እንዲህ ሲል ተናገረኝ፥ አስራ ሁለቱን የበጉን ሐዋርያት የሚዋጉ ሀገሮች፣ ነገዶች፣ ቋንቋዎችና ህዝቦች ሁሉ ውድቀት እንዲህ ይሆናል።