ቅዱሳት መጻህፍት
፩ ኔፊ ፲፰


ምዕራፍ ፲፰

መርከቡ ተጠናቀቀ—የያዕቆብና የዮሴፍ መወለድ ተጠቀሰ—ህዝቡም ወደ ቃልኪዳኑ ምድር ተጓዙ—የእስማኤል ወንዶች ልጆችና ሚስቶቻቸው በፈንጠዚያውና በአመፃው ተቀላቀሉ—ኔፊ ታሰረ፣ እናም መርከቡ በኃይለኛ አውሎ ነፋስ ወደኋላ ተነዳች—ኔፊ ተፈታ፣ እናም በእርሱ ፀሎት ማዕበሉ ቆመ—ህዝቡም ወደ ቃልኪዳኑ ምድር ደረሱ። ከ፭፻፺፩–፭፻፹፱ ም.ዓ. ገደማ።

እናም እንዲህ ሆነ እነርሱ ጌታን አመለኩና ከእኔ ጋር ሄዱ፤ እና ልዩ አይነት አሰራር ባለው እንጨት ስራ ሰራን። ጌታም የመርከቡን እንጨቶች እንዴት መስራት እንዳለብኝ በየጊዜው ያሳየኝ ነበር።

አሁን እኔ ኔፊ ይህንን እንጨት የቀረፅኩት ከሰው በተማርኩት መልኩ አልነበረም፣ መርከቡንም ቢሆን የሰራሁት በሰዎች መንገድ አልነበረም፤ ነገር ግን ጌታ ለእኔ ባሳየኝ መንገድ ነበር የሰራሁት፤ ስለዚህ ይህም በሰዎች መንገድ የተመሰረተ አልነበረም።

እና እኔ ኔፊ ወደተራራው ሁልጊዜ እሄድ ነበር፣ እና እኔ ሁልጊዜ ወደጌታ እፀልይ ነበር፤ ስለዚህ ጌታ ለእኔ ታላቅ ነገሮችን አሳየኝ

እናም እንዲህ ሆነ የጌታን መመሪያ በመከተል መርከቡን ከጨረስኩ በኋላ ወንድሞቼ ጥሩ እንደሆነና አሰራሩም እጅግ ረቂቅ እንደሆነ ተመለከቱ፤ ስለዚህ እንደገና ራሳቸውን በጌታ ፊት ዝቅ አደረጉ።

እናም እንዲህ ሆነ፣ ተነስተን ወደ መርከቡ እንድንወርድ፣ የጌታ ድምፅ ወደአባቴ መጣ።

እናም እንዲህ ሆነ በማግስቱ ከምድረበዳ ብዙ ፍሬዎችን፣ ስጋን፣ በቂ ማር፣ ጌታ እንደአዘዘን ስንቅና ሁሉን ነገሮች ካዘጋጀን በኋላ ከሁሉም ጭነታችንና ዘሮቻችን እናም ከእኛ ጋር ያመጣናቸውን ነገሮች በሙሉ ይዘን፣ እያንዳንዱ እንደ እድሜው ወደመርከቡ ወረድን፣ ስለዚህ ሁላችንም ከሚስቶቻችንና ከልጆቻችን ጋር ወደመርከቡ ወረድን።

እና አሁን አባቴ ሁለት ልጆች በምድረበዳ ወልዷል፤ ታላቁ ያዕቆብ፣ ታናሹ ዮሴፍ ይባሉ ነበር።

እናም እንዲህ ሆነ ሁላችንም የታዘዝነውን ከያዝንና ስንቃችንን ይዘን ወደመርከቡ ውስጥ ከወረድን በኋላ በባህሩ ጉዞን ጀመርን፣ እናም በነፋሱ ፊት ወደ ቃልኪዳኑ ምድር ተገፋን።

እናም ለብዙ ቀናት በነፋሱ ከተመራን በኋላ፣ እነሆ ወንድሞቼ እና የእስማኤል ልጆች እናም ሚስቶቻቸው መደሰት፣ መጨፈርና መዝፈን እንዲሁም ብዙ መጥፎ ነገር መናገር ጀመሩ፣ አዎን፣ በምን ኃይል ወደዚያ ቦታ እንደመጡ እንኳን ረሱት፤ አዎን ክፋታቸውም እጅግ ታላቅ ሆነ።

እናም እኔ ኔፊ በኃጢኣታችን ምክንያት ጌታ እንዳይቆጣንና እንዳይቀጣን በባህርም ጥልቅ ውስጥ እንዳንሰምጥ እጅግ መፍራት ጀመርኩ፤ ስለዚህ እኔ ኔፊ በጥሞና እናገራቸው ጀመርኩ፤ ነገር ግን እነሆ እነርሱ በእኔ ተቆጡ፣ እንዲህም አሉ—ታናሽ ወንድማችን በእኛ ላይ መሪ እንዲሆን አንፈቅድም።

፲፩ እናም እንዲህ ሆነ ላማንና ልሙኤል ወስደው በገመድ አሰሩኝ፣ በጣም አጎሳቆሉኝ፤ ይሁን እንጂ ስለኃጥአን የተናገረው ቃል በሙሉ ይፈፀም ዘንድ ኃይሉን ሊያሳይ ስለፈለገ ጌታ ይህን ፈቀደ

፲፪ እናም እንዲህ ሆነ መነቃነቅ እስኪያቅተኝ ካሰሩኝ በኋላ በጌታ የተዘጋጀው አቅጣጫ ጠቋሚ መስራቱን አቆመ።

፲፫ ስለዚህ መርከቧንም ወዴት መምራት እንዳለባቸው አላወቁም፣ በዚህም ምክንያት ታላቅ ማዕበል አዎን ታላቅና አስፈሪ አውሎ ንፋስ ተነሳ፣ እናም ለሶስት ቀናት ያህል ወደ ኋላ ተነዳን፣ እናም በባህር ውስጥ እንዳይሰምጡ መፍራት ጀመሩ፤ ይሁን እንጂ እኔን አልፈቱኝም።

፲፬ እናም ወደ ኋላ ስንነዳ በነበርንበት በአራተኛው ቀን ማዕበሉ እጅግ በረታ።

፲፭ እናም እንዲህ ሆነ ወደ ባህሩ ጥልቅ ልንሰጥም ነበር። እናም ለአራት ቀን በባህሩ ላይ ወደ ኋላ ከተነዳን በኋላ ወንድሞቼ የጌታ ፍርድ በእነርሱ ላይ መሆኑንና ከኃጢኣታቸው ንስሀ ካልገቡ በስተቀር እንደሚጠፉ መገንዘብ ጀመሩ፤ ስለዚህ ወደ እኔ መጡና የታሰርኩበትን ከክንዶቼ ላይ ፈቱ፣ እነርሱም አብጠው ነበር፤ እናም ደግሞ ቁርጭምጭሚቶቼም እጅግ አብጠው ነበር፣ ሁለቱም እጅግ ቆስለው ነበር።

፲፮ ይሁን እንጂ ወደ አምላኬ ተመለከትኩ፣ እናም ቀኑን ሙሉ እርሱን አመሰገንኩ፤ እናም በመከራዬ የተነሳ በጌታ ላይ አላጉረመረምኩም።

፲፯ አሁን አባቴ ሌሂ እነርሱን እናም ደግሞ የእስማኤልን ወንድ ልጆች ብዙ ነገሮች ተናገሯቸው ነበር፤ ነገር ግን እነሆ ስለእኔ የሚናገርን ማንንም ሰው በብዙ ማስፈራሪያ ተናግረው ነበር፤ እና ወላጆቼ በእርጅና በመያዝና በልጆቻቸው ምክንያት በሀዘን በብርቱ ስለተሰቃዩ ደካማ ሆኑ፣ አዎን አልጋቸው ላይም በበሽታ ወደቁ።

፲፰ በሀዘናቸው ብዛትና በወንድሞቼ ኃጢያት የተነሳ ከዚህ ህይወት ወደሚወሰዱበትና አምላካቸውን ወደሚገናኙበት ደርሰው ነበር፣ አዎን ያረጀ ሰውነታቸውም በአፈር ውስጥ ሊወድቁ እየደረሱ ነበሩ፤ አዎን በሀዘን ወደ ውኃማው መቃብር የሚጣሉበት ጊዜ እየቀረበ ነበር።

፲፱ እናም ያዕቆብና ዮሴፍ ልጆች እንደመሆናቸው ብዙ እንክብካቤ ይፈልጉ ስለነበር፣ በእናታቸው ስቃይ ምክንያት አዝነው ነበር፤ ደግሞም የባለቤቴና የልጆቼ እንባና ፀሎት ይፈቱኝ ዘንድ የወንድሞቼን ልብ አላራራም።

እና በጥፋት ካስፈራራቸው የእግዚአብሔር ኃይል በስተቀር ልባቸውን የሚያራራ ምንም ነገር አልነበረም፤ ስለዚህ በባህሩ ጥልቅ ሊዋጡ እንደሆነ ባዩ ጊዜ ለሰሩት ስራ ንስሀ ገቡ፣ በዚህም ምክንያት እኔን ፈቱኝ።

፳፩ እናም እንዲህ ሆነ እኔን ከፈቱኝ በኋላ አቅጣጫ ጠቋሚውን ወሰድኩት፣ እንደፈለኩትም ሰራ። እናም እንዲህ ሆነ እኔ ለጌታ ፀለይኩ፤ ከፀለይኩም በኋላ ነፋሱም፣ ማዕበሉም ቆመ፣ ታላቅ ፀጥታም ሆነ።

፳፪ እናም እንዲህ ሆነ እኔ ኔፊ መርከቡን መራሁ፣ እንደገናም ወደቃልኪዳኑ ምድር ተጓዝን።

፳፫ እናም እንዲህ ሆነ ለብዙ ቀናት ከተጓዝን በኋላ፣ በቃልኪዳኑ ምድር ደረስን፤ እናም በምድሩ ላይ ሄድንና፣ ድንኳኖቻችንን ተከልን፤ የቃልኪዳኑ ምድር ብለንም ጠራነው።

፳፬ እናም እንዲህ ሆነ መሬቱን ማረስ ጀመርን፣ ዘሮችንም መዝራት ጀመርን፤ አዎን ከኢየሩሳሌም ያመጣናቸውን ዘሮች በሙሉ ዘራናቸው። እናም እንዲህ ሆነ ዘሮቹ እጅግ አደጉ፤ ስለዚህ በብዙ ተባረክን።

፳፭ እናም እንዲህ ሆነ በቃል ኪዳን ምድር ውስጥ በምድረበዳው በተጓዝን ጊዜ ሁሉም አይነት እንስሳት ላም፣ በሬ፣ እና አህያና ፈረስ፣ እናም ፍየልና የዱር ፍየል፣ እንዲሁም ሁሉም አይነት ለሰው ጥቅም የሚውሉ የዱር እንስሳት በጫካው ውስጥ እንደነበሩ አገኘን። እንዲሁም ሁሉም አይነት የወርቅ፣ የብርና፣ የመዳብ የብረት አፈር አገኘን።