ቅዱሳት መጻህፍት
፪ ኔፊ ፴


ምዕራፍ ፴

የተለወጡት አህዛብ ከቃል ኪዳን ህዝብ ጋር ይቆጠራሉ—ብዙ ላማናውያንና አይሁዶች በቃሉ ያምናሉ እናም ያማሩ ይሆናሉ—እስራኤል ዳግም ትመለሳለች፣ እናም ኃጢአተኞች ይጠፋሉ። ከ፭፻፶፱–፭፻፵፭ ም.ዓ. ገደማ።

እናም አሁን እነሆ፣ የተወደዳችሁ ወንድሞቼ፣ እናገራችኋለሁ፤ እኔ ኔፊ እናንተ አህዛቦች ከሚሆኑት የበለጠ ፃድቃን እንሆናለን ብላችሁ እንድታስቡ አልፈቅድም። እነሆም የእግዚአብሔርን ትዕዛዝ ካልጠበቃችሁ በተመሳሳዩ ሁላችሁም ትጠፋላችሁ፤ እናም በተነገረው ቃል ምክንያት አህዛብ በሙሉ ጠፍተዋል ብላችሁም አታስቡ።

እነሆም፣ እላችኋለሁ ንሰሃ የሚገቡት አህዛቦች የጌታ ቃል ኪዳን ህዝብ ናቸው፤ እናም ንሰሃ የማይገቡት አይሁዶችም ይጣላሉ፤ ምክንያቱም ጌታ ንስሀ በሚገቡት እና የእስራኤል ቅዱስ በሆነው በልጁ ከሚያምኑት በስተቀር ለማንም ቃል ኪዳን አልገባምና።

እናም አሁን፣ በይበልጥ ስለአይሁዶችና ስለአህዛብ በመጠኑ ትንቢት እናገራለሁ። እኔ የተናገርኳችሁ መፅሐፍ ከመጣ፣ እናም ለአህዛቦች ከተፃፈና፣ በድጋሚ ወደ ጌታ ከታተመ በኋላ፣ በተፃፉት ቃላት የሚያምኑ ብዙዎች ይኖራሉ፤ እና እነርሱም ለቀሩት ዘሮቻችን ያደርሱአቸዋል።

እናም ከዚያ በኋላ የእኛ ዘሮች ቅሪት እኛን በተመለከተ፣ እንዴት አድርገን ከኢየሩሳሌም እንደወጣን፣ እናም እንዴትስ እነርሱ የአይሁድ ትውልድ እንደሆኑ ያውቃሉ።

እናም የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል በእነርሱ መካከላቸው ይሰበካል፤ ስለሆነ፣ እነርሱም ወደ አባቶቻቸው እውቀት፣ እናም ደግሞ በአባቶቻቸው መካከል ወደ ነበረው የኢየሱስ ክርስቶስ እውቀት ይመለሳሉ።

እናም ከዚያ በኋላ ይደሰታሉ፤ ምክንያቱም ይህ ከእግዚአብሔር እጅ የተሰጣቸው በረከት እንደሆነ ያውቃሉ፤ እናም የጨለማው ቅርፊት ከዐይናቸው መውደቅም ይጀምራል፤ እናም ንፁህና አስደሳች ህዝቦች እስኪሆኑ ድረስ ብዙ ትውልድ ከእነርሱ አያልፍም።

እናም እንዲህ ይሆናል የተበተኑት አይሁዶች ደግሞ በክርስቶስ ማመን ይጀምራሉ፤ በምድር ፊትም ላይ መሰብሰብ ይጀምራሉ፤ እናም በክርስቶስ የሚያምኑ ብዙዎችም አስደሳች ህዝብ ይሆናሉ።

እናም እንዲህ ይሆናል ጌታ እግዚአብሔር በምድር ላይ የህዝቡን ዳግም መመለስ ለማምጣት በሁሉም ሀገሮች፣ ወገኖች፣ ቋንቋና ህዝብ መካከል ስራውን ይጀምራል።

እናም ጌታ እግዚአብሔር ድሆችን በፅድቅ ይፈርዳል፣ የምድር ትሁታንም በእኩልነት ይገስጻል። እናም ምድርን በአፉ በትር ይመታል፤ በከንፈሩም ትንፋሽ ኃጢአተኞችን ይገድላል።

ጌታ እግዚአብሔር በሰዎች መካከል ታላቅ ክፍፍል የሚያደርግበት ጊዜ በፍጥነት ይመጣል፣ እናም በደለኞችን ያጠፋል፤ እናም ህዝቡን ይምራል፣ አዎን፣ በደለኞችን በእሳት ማጥፋት ቢኖርበትም።

፲፩ እናም ፅድቅነትም የወገቡ መታጠቅያው፣ ታማኝነትም የጎኑ መቀነትይሆናል።

፲፪ እናም ተኩላ ከበጉ ጋር ይኖራል፤ አቦሸማኔውም ከፍየል ግልገሎች ጋር፣ ጥጃውም የአንበሳ ደቦልም፣ ከፍሪዳውም ጋር በአንድ ላይ ይተኛሉ፤ እናም ትንሽ ልጅም ይመራቸዋል።

፲፫ እናም ላምና ድብ አብረው ይመገባሉ፤ ግልገሎቻቸውም በአንድነት ይተኛሉ፤ እናም አንበሳም እንደ በሬ ገለባ ይበላል።

፲፬ እናም የሚጠባው ህፃን በመርዛማው እባብ ጉድጓድ ላይ ይጫወታል፣ እናም ጡት የጣለውም ህፃን በእፉኝት ቤት ላይ እጁን ይጭናል።

፲፭ በተቀደሰው ተራራዬ ላይ ሁሉ አይጎዱም፣ አይጠፉምም፤ ውሃ ባህርን እንደሚሸፍን ሁሉ ምድር በጌታ እውቀትም ትሞላለችና።

፲፮ ስለሆነም፣ የሁሉም ሀገሮች ነገሮች ይታወቃሉ፤ አዎን፣ ሁሉም ነገሮች ለሰው ልጆች ይገለጣሉ

፲፯ ያልተገለጠ፣ ሚስጥር የሆነ ምንም የለም፤ በብርሃን የማይወጣ የጨለማ ስራ የለም፤ እናም የማይፈታ በምድር ላይ የሚታተም ምንም ነገር አይኖርም።

፲፰ ስለሆነም፣ ለሰው ልጆች ተገልጠው የነበሩት ሁሉም ነገሮች በዚያ ቀን ይገለጣሉ፤ እናም ከእንግዲህ ወዲህ ሰይጣን በሰዎች ልጆች ልብ ላይ ምንም ስልጣን ለብዙ ጊዜ አይኖረውም። እናም አሁን የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ንግግሬን እፈፅማለሁ።