ቅዱሳት መጻህፍት
፪ ኔፊ ፬


ምዕራፍ ፬

ሌሂ ዘሮቹን መከረ እንዲሁም ባረከ—ሞተና ተቀበረ—ኔፊ በእግዚአብሔር ቸርነት ተደሰተ—ኔፊ እምነቱን ለዘለዓለም በጌታ አደረገ። ከ፭፻፹፰–፭፻፸ ም.ዓ. ገደማ።

እናም አሁን፣ እኔ ኔፊ፣ አባቴ ወደ ግብፅ ተወስዶ ስለነበረው ዮሴፍ የተናገራቸውን ትንቢቶች በተመለከተ ተናገርኩ።

እነሆም እርሱ ዘሮቹን በተመለከተ በእውነት ተንብዮአል። እናም እርሱ ከፃፋቸው የበለጡ ትንቢቶች ብዙ የሉም። እናም እርሱ እኛን እንዲሁም የወደፊቱን ትውልድ በተመለከተ ተንብዮአል፤ እና እነሱም በነሀስ ሰሌዳው ላይ ተፅፈዋል።

ስለሆነም፣ አባቴ የዮሴፍን ትንቢት በተመለከተ መናገሩን ካቆመ በኋላ፣ የላማንን ወንዶችና ሴቶች ልጆች ጠርቶ እንዲህ አላቸው—እነሆ፣ ወንዶችና ሴቶች ልጆቼ የበኩር ልጄ ወንዶች ልጆችና ሴቶች ልጆች የሆናችሁ፣ ቃሌን እንድታደምጡ እፈልጋለሁ።

ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ብሏልና—ትዕዛዛቴን እስከጠበቃችሁ ድረስ በምድሪቷ ላይ ትበለፅጋላችሁ፤ እናም ትዕዛዛቴን የማትጠብቁ ከሆነ ከፊቴ ትለያላችሁ።

ነገር ግን እነሆ፣ ወንዶችና ሴቶች ልጆቼ፣ ለእናንተ በረከትን ሳልተውላችሁ ወደ መቃብሬ መሄድ አልችልም፤ እነሆም መሄድ ባለባችሁ መንገድ ካደጋችሁ ከእርሱ እንደማትሸሹ አውቃለሁ።

ስለሆነም፣ ከተረገማችሁ፣ እነሆ፣ እርግማኑ ከእናንተ እንዲወሰድና በወላጆቻችሁ ራስ ላይ ይመለስ ዘንድ በረከቴን በእናንተ ላይ እተዋለሁ።

ስለሆነም፣ በእኔ በረከት የተነሳ ጌታ እግዚአብሔር እናንተ እንድትጠፉ አይፈቅድም፤ ስለሆነም፣ እርሱ ለዘለዓለም ለእናንተ እና ለዘሮቻችሁ መሀሪ ይሆናል።

እናም እንዲህ ሆነ አባቴ ለላማን ወንዶችና ሴቶች ልጆች መናገሩን ካቆመ በኋላ፣ የልሙኤልን ወንዶችና ሴቶች ልጆች በፊቱ እንዲቀርቡ አስደረገ።

እናም እርሱ እንዲህ ሲል ተናገራቸው—እነሆ፣ የሁለተኛው ወንድ ልጄ ወንድና ሴት ልጆች የሆናችሁ ወንዶችና ሴት ልጆቼ፤ እነሆ እኔ ለላማን ወንዶችና ሴቶች ልጆች የሰጠሁት አይነት በረከት እሰጣችኋለሁ፤ ስለሆነም እናንተ ፈፅሞ አትጠፉም፤ ነገር ግን በመጨረሻ ዘሮቻችሁ ይባረካሉ።

እናም እንዲህ ሆነ አባቴ ለእነርሱ መናገሩን ከጨረሰ በኋላ፣ እነሆ፣ የእስማኤልን ወንዶች ልጆች፣ አዎን፣ እናም ቤተሰቡን ሁሉ ተናገራቸው።

፲፩ እናም እርሱ እነርሱን መናገር ካቆመ በኋላ፣ ለሳም እንዲህ ሲል ተናገረው፥ አንተ የተባረክህ ነህ፣ እንዲሁም ዘርህ፤ ምክንያቱም እንደወንድምህ ኔፊ ምድሪቱን ትወርሳለህና። እናም ዘርህ ከእርሱ ዘር ጋር ይቆጠራል፤ እናም አንተ ልክ እንደ ወንድምህ ትሆናለህ፣ ዘርህም ልክ እንደእርሱ ዘር ይሆናል፤ አንተም በዘመንህ ሁሉ ትባረካለህ።

፲፪ እናም እንዲህ ሆነ አባቴ፣ ሌሂ፣ በውስጡ ባለው የልቡ ስሜትና የጌታ መንፈስ መሰረት ለቤተሰቡ ሁሉ ከተናገረ በኋላ አረጀ። እንዲህም ሆነ እርሱም ሞተ፣ እናም ተቀበረ።

፲፫ እናም እንዲህ ሆነ ከሞተ በኋላ ብዙም ቀን ሳይሆን ላማንና ልሙኤል እንዲሁም የእስማኤል ወንድ ልጆች በጌታ ተግሳፅ የተነሳ በእኔ ተቆጡ።

፲፬ እኔ ኔፊ፣ እንደቃሉ እነርሱን እንድናገራቸው ተገፋፍቼ ነበርና፤ እኔ፣ እና ደግሞም አባቴ ከመሞቱ በፊት፣ ብዙ ነገሮችን ተናግረናቸው ነበር፤ ብዙዎቹ አባባሎች በሌሎች ሰሌዳዎቼ ላይ ተፅፈዋል፤ ታሪካዊ የሆነውም ይበልጡ ክፍል በሌላኛው ሰሌዳዎቼ ላይ ተፅፏልና።

፲፭ እናም በእነዚህ ላይ የነፍሴን ነገሮች፣ እናም በነሀስ ሰሌዳዎቹ ላይ የተቀረፁ ብዙዎቹ ቅዱሳት መጻሕፍት እፅፋለሁ። ነፍሴ በቅዱሳት መጻሕፍት ትደሰታለች፣ እንዲሁም ልቤ ታሰላስላቸዋለች፣ እንዲሁም እኔ እነርሱን ለልጆቼ ትምህርትና ጥቅም እፅፋለሁ።

፲፮ እነሆ፣ ነፍሴ በጌታ ነገሮች ትደሰታለች፤ እናም ልቤ ያየኋቸውንና የሰማኋቸውን ነገሮች ላይ ያለማቋረጥ ታሰላስላለች።

፲፯ ይሁን እንጂ፣ ጌታ ታላቅና ድንቅ ስራውን ለእኔ ለማሳየት ምንም እንኳን ቸርነቱ ታላቅ ቢሆንም ልቤ ይጮሀል—አቤቱ እኔ ምንኛ ጎስቋላ ሰው ነኝ! አዎን፣ ልቤ በስጋዬም የተነሳ ያዝናል፤ ነፍሴም በክፋቴ የተነሳ ታዝናለች።

፲፰ እኔ በቀላሉ በሚያስቸግሩኝ መከራዎችና ኃጢአቶች ተከብቤአለሁ።

፲፱ እናም ደስታን በምፈልግበት ጊዜ በኃጢአቴ የተነሳ ልቤ ያዝናል፤ ይሁን እንጂ በማን እንዳመንኩኝ አውቃለሁ።

እግዚአብሔር ረዳቴ ነበር፤ በምድረበዳ ውስጥ በስቃዬ መራኝ፤ እናም በታላቁን ጥልቅ ውኃ ላይ ጠበቀኝ።

፳፩ ሰውነቴን ሁሉ፣ ስጋዬም እስከሚነድ ድረስ፣ በፍቅሩ ሞላኝ።

፳፪ ጠላቶቼን በፊቴ በፍርሀት እስኪንቀጠቀጡ ድል ነሳቸው።

፳፫ እነሆ፣ በቀን ጩኸቴን ሰምቷል፣ እናም በምሽት በራዕይ እውቀትን ሰጥቶኛል።

፳፬ እናም፣ በቀን በፊቱ በታላቅ ፀሎት ተዳፈርኩ፤ አዎን፣ ድምጼንም ወደላይ ላኩኝ፤ እናም መላዕክት ወርደው አገለገሉኝ።

፳፭ እናም በመንፈሱ ክንፎች ሰውነቴ እጅግ ከፍ ወዳለው ተራራ ተወሰደ። እናም ዓይኖቼም ታላቅ ነገሮችን ተመልክተዋል፣ አዎን፣ እንዲያውም ለሰዎች እጅግ ታላቅ የሆነውን፤ ስለዚህ እኔ እነርሱን እንዳልፅፍ ታዝዤ ነበር።

፳፮ አቤቱ አሁን ታላቅ ነገሮችን ካየሁ፣ ጌታ ለሰው ልጆች እራሱን ዝቅ በማድረግ በእንዲህ ዓይነት ምህረቱ ከጎበኛቸው፣ ለምንድነው ልቤ የሚያለቅሰው፣ እንዲሁም ነፍሴ በሀዘን ሸለቆ ውስጥ የምትዘገየው፣ እናም ሰውነቴ የሚቃወሰው፣ እናም ጥንካሬዬ በመከራዬ የሚደክመው?

፳፯ እናም ለምን በስጋዬ የተነሳ ለኃጢያት ተገዢ እሆናለሁ? አዎን፣ ለምን በመከራ ውስጥ እወድቃለሁ፣ ክፉው ሰላሜን እንዲያጠፋ እንዲሁም ነፍሴን እንዲያሰቃያት በልቤ ውስጥ ቦታ ያገኛል ዘንድ ለምን በፈተና ተገዢ እሆናለሁ? በጠላቴ የተነሳ ለምን እቆጣለሁ?

፳፰ ነፍሴ ሆይ፣ ንቂ! ከእንግዲህ በኃጢያት አትድከሚ። አቤቱ ልቤ ተደሰቺ፣ እናም ለነፍሴ ጠላት ለሆነው ቦታ አትስጪ።

፳፱ በጠላቶቼ የተነሳ በድጋሚ አትቆጪ። በመከራዬም የተነሳ ብርታቴን አታድክሚ።

አቤቱ ልቤ ተደሰቺ፣ እንዲህም በማለት ወደ ጌታ ጩሂ—አቤቱ ጌታ አንተን ለዘለዓለም አወድስሀለሁ፤ አዎን አምላኬና የደህንነቴ አለት ነፍሴ በአንተ ደስ ይላታል።

፴፩ አቤቱ ጌታ፣ ነፍሴን ታድናለህን? ከጠላቶቼስ እጅ ታወጣኛለህን? ኃጢያትን በምመለከትበት ወቅት በጥላቻ ታንቀጠቅጠኛለህን?

፴፪ የሲኦል ደጆች ከፊቴ ይዘጉ፣ ምክንያቱም ልቤ የተሰበረ እና መንፈሴ የተዋረደ ነውና! አቤቱ ጌታ፣ እባክህ በጥልቁ ሸለቆ ጎዳና እጓዝበት ዘንድ በቀናው መንገድ እፀና ዘንድ፣ የፅድቅን በሮች ከፊቴ አትዝጋ!

፴፫ አቤቱ ጌታ፣ እባክህ የፅድቅህን መጎናፀፊያ ደርብልኝ! አቤቱ ጌታ፣ እባክህ ከጠላቶቼ የምሸሽበትን መንገድ አዘጋጅልኝ! እባክህ መንገዴን አቅናልኝ! እባክህ በመንገዴ እንቅፋትን አታድርግ—ነገር ግን አንተ መንገዴን ታጠራልኛለህ፣ እናም የጠላቶቼን መንገድ እንጂ የእኔን አትዘጋብኝም።

፴፬ አቤቱ ጌታ፣ በአንተ ታምኛለሁ፣ እንዲሁም ለዘለዓለም በአንተ እታመናለሁእምነቴን በስጋ ክንድ ላይ አላደርግም፤ ምክንያቱም በስጋ ክንድ ላይ የሚታመን የተረገመ እንደሚሆን አውቃለሁና። አዎን፣ በሰው ላይ እምነት የሚያደርግ ወይም ስጋ ለባሹን ክንዱ የሚያደርግም ሰው የተረገመ ነው።

፴፭ አዎን፣ እግዚአብሔርን ሳይነቅፍ ለለመነ ለእርሱ በልግስና እንደሚሰጠው አውቃለሁ። አዎን፣ አምላኬን የተሳሳተ ነገር ካልጠየቅሁት በስተቀር ይሰጠኛል፤ ስለዚህ ወደ አንተ ድምፄን ከፍ አደርጋለሁ፤ አዎን፣ አምላኬ የፅድቄ አለት ወደሆንከው አንተም እጮሀለሁ። እነሆ፣ አለቴና የዘለአለም አምላኬ፣ ድምፄ ለዘለዓለም ወደ አንተ ከፍ ይላል። አሜን።