ቅዱሳት መጻህፍት
፪ ኔፊ ፯


ምዕራፍ ፯

ያዕቆብ ከኢሳይያስ ማንበቡን ቀጠለ፥ ኢሳይያስ እንደ መሲሁ ይናገራል—መሲሁ የተማሩ ሰዎች ልሳን ይኖረዋል—ለሚገርፉት ጀርባውን ይሰጣል—እርሱ አያፍርም—ኢሳይያስ ፶ን አነጻፅሩ። ፭፻፶፱–፭፻፵፭ ም.ዓ. ገደማ።

አዎን፣ ጌታ እንዲህ ይላል—ፈትቻችኋለሁን፣ ወይንስ ለዘለዓለም ወርውሬአችኋለሁ? ጌታ እንዲህ ይላል—እናታችሁን የፈታሁበት የፍቺዋ ፅህፈት የት አለ? ለማን ነው አሳልፌ የሰጠኋችሁ? ወይስ እናንተን የሸጥኩት ከአበዳሪዎች ለየትኛው ነው? አዎን፣ ለማን ሸጥኳችሁ? እነሆ፣ ስለኃጢአታችሁ ራሳችሁን ሸጣችኋል፣ እናም ስለመተላለፋችሁ እናታችሁም ተፈታለች።

ስለሆነም፣ እኔ ስመጣ ማንም ሰው አልነበረም፤ በምጣራበትም ጊዜ አዎን፣ የሚመልስ አልነበረም። የእስራኤል ቤት ሆይ፣ መታደግ እንዳትችል እጄ ፈፅሞ አጥራለች፣ ወይስ ለማዳን ኃይል የለኝምን? እነሆ በግሰጻዬ ባህሩን አደርቃለሁ፣ ወንዞችንም ምድረበዳ አደርጋለሁ እናም አሳዎቻቸው ውሃው በመድረቁ ይገማሉ፣ እናም በጥማት ይሞታሉ።

ሰማያትን ጥቁረት አለብሳቸዋለሁ፣ እናም መሸፈኛቸውን ማቅ አደርጋለሁ።

የእስራኤል ቤት ሆይ ጌታ እግዚአብሔር በትክክለኛው ጊዜ ለእናንተ እንዴት መናገር እንድችል የተማሩትን ልሳን ሰጥቶኛል። እናንተ በደከማችሁ ጊዜ ማለዳ በማለዳ ያነቃችኋል። እንደተማሪ እንድሰማ ጆሮዬን ያነቃቃል።

ጌታ እግዚአብሔር ጆሮዬን ከፍቷል፣ እናም እኔ አመፀኛ አልነበርኩም፣ ወደኋላም አልተመለስኩም።

ጀርባዬን ለገራፊዎች፣ እናም ጉንጬንም ለፀጉር ነጪዎች ሰጠሁ። ፊቴንም ከውርደትና ከትፋት አልመለስኩም።

ጌታ እግዚአብሔር ይረዳኛል፣ ስለዚህም አላፍርም። ስለዚህ ፊቴን እንደባልጩት ድንጋይ አድርጌዋለሁ፣ እናም እንደማላፍር አውቃለሁ።

እናም ጌታ ቅርቤ ነው፣ እርሱም ያጸድቀኛል። ከእኔ ጋር የሚከራከር ማነው? በአንድነት እንቁም። ጠላቴስ ማነው? ወደ እኔ እንዲቀርብ ፍቀዱለት እናም በአፌ ኃይለ ቃል እመታዋለሁ።

ጌታ እግዚአብሔር ይረዳኛል። እናም እኔን የሚኮንኑ ሁሉ፣ እነሆ፣ ሁሉ እንደ ልብስ ያረጃሉ፣ እናም ብል ይበላቸዋል።

ከእናንተ መካከል ጌታን የሚፈራ፣ የአገልጋዩን ድምፅ የሚታዘዝ፣ በጨለማ የሚራመድ እንዲሁም ብርሃን የሌለው ማነው?

፲፩ እነሆ እናንተ እሳት የምታነዱ ሁሉ፣ የእሳትንም ወላፈን የምትጭሩ፣ በእሳታችሁ ብርሃን እና ባነደዳችሁት ወላፈን ተመላለሱ። ይህ ከእጄ ይሆንባችኋል—በሀዘንም ትሞታላችሁ።