ቅዱሳት መጻህፍት
፫ ኔፊ ፲፩


ህዝቡ በለጋስ ምድር በተሰበሰበበት ኢየሱስ ክርስቶስ ለኔፊ ህዝብ እራሱን ገለፀም፣ አስተማራቸውም፤ እናም በዚህ መንገድ ነበር እራሱን ያሳያቸው።

ምዕራፍ ፲፩ እስከ ፳፮ አጠቃሎ የያዘ።

ምዕራፍ ፲፩

አብ ስለተወደደው ልጁ መሰከረ—ክርስቶስ ተገለጠ፣ እናም ስለኃጢያት ክፍያው ተናገረ—ህዝቡም በእጁና በእግሩ፣ እናም በጎኑ ላይ የነበረውን የቁስሉን ምልክት ዳሰሱት—ሆሳዕና ብለውም ጮኹ—የጥምቀት ደንብና ስርዓት አስተማራቸው—የጸብ መንፈስ ከዲያብሎስ ነው—የክርስቶስ ትምህርት ሰዎች እንዲያምኑና፣ እንዲጠመቁ፣ እናም መንፈስ ቅዱስን እንዲቀበሉ ነው። ፴፬ ዓ.ም. ገደማ።

እናም አሁን እንዲህ ሆነ የኔፊ ህዝብ የሆኑ በቁጥር ብዙ የነበሩት በለጋስ ምድር በነበረው ቤተመቅደስ ዙሪያ በአንድነት ተሰብስበው ነበር፤ እናም እርስ በርሳቸውም ተገርመውና ተደንቀው ነበር፤ እናም አንዳቸው ለሌላኛቸውም ታላቅና አስገራሚ የነበሩትን ለውጦች እያሳዩ ነበር።

እናም ደግሞ ስለሞቱ የተሰጠውን ምልክት ተሰጥቶ ስለነበረው ስለዚህ ስለኢየሱስ ክርስቶስ በተመለከተ ይነጋገሩ ነበር።

እናም እንዲህ ሆነ እርስ በርሳቸው በሚነጋገሩበትም ወቅት፣ ከሰማይ የመጣ የሚመስል ድምፅ ሰሙ፤ የሰሙትንም ድምፅ ለመረዳት ባለመቻላቸው ዙሪያውን ተመለከቱ፤ እናም ድምፁ ሻካራ አልነበረም፣ ወይም የጩኸት ድምፅም አልነበረም፤ ይሁን እንጂ፣ ድምፁ አነስተኛ ቢሆንም እንኳን የሰሙት ውስጣቸውን ሰንጥቆ ገብቶ፣ በዚህም የተነሳ ከሰውነታቸው ያልተንቀሳቀሰ ክፍል አልነበረም፤ አዎን፣ እስከነፍሳቸው ድረስ ዘልቆ ገብቷል፣ እናም ልባቸውን እንዲቃጠል አድርጓል።

እናም እንዲህ ሆነ በድጋሚ ድምፁን ሰሙት፣ እናም አልተረዱትም ነበር።

እናም በድጋሚ ለሦስተኛ ጊዜ ድምፁን ሰሙትና፣ ለማዳመጥ ጆሮአቸውን ከፈቱ፤ እናም ዐይኖቻቸው ድምጹ ወደነበረበት እየተመለከቱ ነበር፤ ድምፁ ወደሚመጣበት ወደ ሰማይ አቅጣጫም በፅናት ተመለከቱ።

እናም እነሆ፣ ለሦስተኛ ጊዜም የሰሙትን ድምፅ ተረዱት፤ እንዲህም አላቸው፥

እነሆ በእርሱ ደስ የሚለኝ፤ ስሜንም ያከበርኩበት፣ የምወደው ልጄ ይህ ነው—እርሱን ስሙት።

እናም እንዲህ ሆነ በተረዱትም ጊዜ በድጋሚ በሰማይ ላይ ዐይናቸውን ጣሉ፤ እናም እነሆ፣ አንድ ሰው ከሰማይ ሲወርድ ተመለከቱ፤ እናም እርሱ ነጭ ልብስ ለብሶ ነበር፤ እናም ወረደና በመካከላቸው ቆመ፤ እናም የህዝቡም ዐይን ሙሉ በሙሉ በእርሱ ላይ ነበር፣ እናም እርስ በርሳቸውም ለመነጋገር አልደፈሩም ነበር፣ እናም መላዕክት እንደታያቸው በማሰባቸውም ምን ማለት እንደሆነ አላወቁም ነበር።

እናም እንዲህ ሆነ እርሱም እጁን ዘረጋና፣ ወደ ህዝቡም እንዲህ ሲል ተናገረ፥

እነሆ፣ እኔ ኢየሱስ ክርስቶስ ነኝ፣ ነቢያት ወደ ዓለም ይመጣል ብለው የመሰከሩልኝም።

፲፩ እናም እነሆ እኔ የዓለም ብርሃንና ህይወት ነኝ፤ እናም አብ ከሰጠኝ መራራ ፅዋም ጠጥቻለሁ፣ እናም የዓለምን ኃጢያት በራሴ ላይ በመውሰድም አብን አክብሬአለሁ፣ በዚህም ከመጀመሪያ ጀምሮ በሁሉም ነገሮች የአብን ፈቃድ ፈፅሜአለሁ።

፲፪ እናም እንዲህ ሆነ ኢየሱስም እነዚህን ቃላት በተናገረበት ጊዜ ሰዎቹ ሁሉ በመሬት ላይ ወደቁ፤ ምክንያቱም ክርስቶስ ወደ ሰማይ ካረገም በኋላ በመካከላቸው እራሱን እንደሚያሳይ በነቢያት ተተንብዮ እንደነበር አስታውሰዋልና።

፲፫ እናም እንዲህ ሆነ ጌታም እንዲህ ሲል ተናገራቸው፥

፲፬ ተነሱ እናም እጆቻችሁንም በጎኔ እንድታስገቡና ደግሞ የችንካሬን ምልክት በእጆቼና በእግሮቼ ላይ ትዳስሱት ዘንድ፣ እኔ የእስራኤል አምላክ፣ እናም የምድር ሁሉ አምላክ መሆኔንና፣ ለዓለም ኃጥያቶችም መገደሌንም እንድታውቁ ዘንድ ወደ እኔ ኑ።

፲፭ እናም እንዲህ ሆነ ህዝቡም ሄዱና እጃቸውን በጎኑ አስገቡ፣ እናም ምስማር የተቸነከሩባቸውን እጆቹንና እግሮቹን ዳሰሷቸው፤ ሁሉም እስከሚደርሳቸው አንድ በአንድ እየሄዱ ይህን አደረጉ፣ እናም በዐይኖቻቸው ተመለከቱና፣ በእጆቻቸው ዳሰሱ፣ እናም በነቢያቱ ስለመምጣቱም የተነገረለት እርሱ መሆኑን በእርግጥም አወቁና መሰከሩ።

፲፮ እናም ሁሉም በሄዱና ለየራሳቸውም በተመለከቱ ጊዜ በአንድነት እንዲህ ሲሉ ጮኹ፥

፲፯ ሆሳዕና! የልዑሉ አምላካችን ስም የተባረከ ይሁን! እናም በኢየሱስ እግር ስር ወደቁ፣ እናም አመለኩት

፲፰ እናም እንዲህ ሆነ እርሱም ለኔፊ ተናገረ (ኔፊ ከህዝቡ መካከል ስለነበር) እናም እርሱ ወደ ፊት እንዲመጣም አዘዘው።

፲፱ እናም ኔፊ ተነሳና፣ ሄደ እናም በጌታ ፊት አጎነበሰና፣ እግሮቹን ሳመ።

እናም ጌታ እንዲነሳ አዘዘው። እናም እርሱም ተነሳና በፊቱ ቆመ።

፳፩ እናም ጌታ እንዲህ ሲል ተናገረው፥ በድጋሚ ወደ ሰማይ በማርግበት ጊዜም ይህንን ህዝብ እንድታጠምቅ ስልጣንን እሰጥሃለሁ።

፳፪ እናም በድጋሚ ጌታ ሌሎችን ጠርቶ በተመሳሳይ ተናገራቸው፤ እንዲያጠምቁም ስልጣንን ሰጣቸው። እናም እንዲህ አላቸው፥ በዚህ መንገድ ታጠምቃላችሁ፤ በመካከላችሁም ምንም ፀብ አይኖርም።

፳፫ በእውነት እንዲህ እላችኋለሁ በእናንተ ቃላት አምኖ ለኃጢአቱ ንሰሃ የገባና በስሜም ለመጠመቅ የፈለጉትን በዚህ መንገድ አጥምቁአቸው—እነሆ፣ እናንተ ወርዳችሁ እናም በውሃው መካከል ትቆማላችሁ፣ እናም በስሜም ታጠምቁአቸዋላችሁ።

፳፬ እናም አሁን እነሆ በስማቸውም ጠርታችሁ የምትናገሩአቸው ቃላት እነዚህ ናቸው፥

፳፭ በኢየሱስ ክርስቶስ በተሰጠኝ ስልጣን መሰረት በአብ፤ በወልድ፤ እናም በመንፈስ ቅዱስ ስም አጠምቅሃለሁ። አሜን።

፳፮ እናም በውሃ ውስጥ ታጠልቋቸዋላችሁ፤ እናም ከውሃ ውስጥም በድጋሚ ታወጧቸዋላችሁ።

፳፯ እናም በዚህም መንገድ በስሜ ታጠምቃላችሁ፤ እነሆም፣ በእውነት አብና፣ ወልድ፣ እናም መንፈስ ቅዱስ አንድ ናቸው እላችኋለሁ፤ እናም እኔ በአብ እንዳለሁ አብም በእኔ ነው፣ እናም አብና እኔም አንድ ነን።

፳፰ እናም በዚህ በማዛችሁ መሰረትም እንደዚህ አጥምቁ። እናም ከዚህ በፊት እንደነበረውም በመካከላችሁ ፀብ አይኖርም፤ ከዚህ በፊት እንደነበረው በትምህርቴ ነጥቦችም ምክንያት በመካከላችሁ ፀብ አይኖርም።

፳፱ እውነት፣ እውነት እላችኋለሁ፣ የፀብ መንፈስ ያለበት፣ የፀብ አባት ከሆነ እናም የሰዎችን ልብ እርስ በርስ እንዲጣሉ በቁጣ ከሚያነሳሳው ከዲያብሎስ እንጂ፤ ከእኔ አይደለም።

እነሆ፣ ሰዎችን አንዳቸውን ከሌላኛው ልባቸውን ለቁጣ የሚያነሳሳ ይህ የእኔ ትምህርት አይደለም፤ ነገር ግን እንደነዚህ ያሉ ነገሮች እንዲወገዱ ማድረግ ይህ የእኔ ትምህርት ነው።

፴፩ እነሆ፣ እውነት፣ እውነት እላችኋለሁ፤ ትምህርቴን ለእናንተ አውጃለሁ።

፴፪ እናም ይህ የእኔ ትምህርት ነው፤ ይህም አብ ለእኔ የሰጠኝ ትምህርት ነው፤ ስለአብ እመሰክራለሁ፣ እንዲሁም አብ ስለእኔ ይመሰክራል፤ መንፈስ ቅዱስም ደግሞ ስለእኔና ስለአብ ይመሰክራል፤ በማንኛውም ስፍራ አብ ሰዎች በሙሉ ንሰሃ እንዲገቡና በእኔ እንዲያምኑ አዞአቸዋል።

፴፫ እናም በእኔ ያመነና የተጠመቀ ይድናል፤ እና እነርሱም የእግዚአብሔርን መንግስት የሚወርሱ ናቸው።

፴፬ እናም በእኔ የማያምን ቢኖርና ካልተጠመቅ እርሱ ይኮነናል።

፴፭ እውነት፣ እውነት እላችኋለሁ፣ ይህ የእኔ ትምህርት ነው፣ ከአብ መሆኑንም እመሰክራለሁ፤ በእኔ የሚያምንም ቢኖር ደግሞም በአብ ያምናል፤ ለእርሱም ስለእኔ አብ ይመሰክርለታል፤ አብም በእሳት እንዲሁም በመንፈስ ቅዱስ ይጎበኘዋል።

፴፮ እናም አብ ስለእኔ ይመሰክራል፣ መንፈስ ቅዱስም ስለአብና ስለእኔ ይመሰክራል፤ ምክንያቱም አብ እኔና መንፈስ ቅዱስ አንድ ነን።

፴፯ እናም በድጋሚ እንዲህ እላችኋለሁ፣ ንሰሃ ግቡና እንደ ህፃናት ሁኑ፤ በስሜም ተጠመቁ፣ አለበለዚያ እነዚህን ነገሮች በምንም መንገድ ልትቀበሉ አትችሉም።

፴፰ እናም በድጋሚ እንዲህ እላችኋለሁ፣ ንሰሃ ግቡና በስሜም ተጠመቁ፣ እናም እንደህፃናት ሁኑ፣ አለበለዚያ በምንም መንገድ የእግዚአብሔርን መንግስት ልትወርሱ አትችሉም።

፴፱ እውነት፣ እውነት እላችኋለሁ፣ ይህ የእኔ ትምህርት ነው፣ እናም በዚህም የሚገነባ በእኔ አለት ላይ መሰረቱን የገነባ፣ እናም የሲዖል ደጆችም አያሸንፋቸውም።

እናም ከዚህ የበለጠ ወይንም ያነሰ የሚናገርና፣ ይህን እንደ ትምህርቴ የሚመሰርት ቢኖር፣ እርሱ ከክፉ ነው፤ እናም በዓለት ላይ የገነባ አይደለም፤ ነገር ግን በአሸዋው ላይ መሰረቱን የገነባው ነው፣ የጥፋት ውሀ ሲመጣና፣ ነፋስ ሲመታው የገሃነም ደጆችም እርሱን ለመቀበል ክፍት ሆነው ይጠብቃሉ።

፵፩ ስለዚህ ወደእነዚህ ህዝቦች ሂዱ፤ እስከአለም ዳርቻም የተናገርኳቸውን ቃላት አስተምሩአቸው።