ቅዱሳት መጻህፍት
፫ ኔፊ ፳፫


ምዕራፍ ፳፫

ኢየሱስ የኢሳይያስን ቃላት አጸደቀ—ህዝቡ ነቢያትን እንዲፈልጉ አዘዘ—ላማናዊው ሳሙኤል ስለትንሣኤ የተናገራቸው ቃላት በመዝገቦቻቸው ተጨምረዋል። ፴፬ ዓ.ም. ገደማ።

እናም እንግዲህ፣ እነሆ፣ እንዲህ እላችኋለሁ፣ እነዚህን ነገሮች ፈልጉ። አዎን፣ እነዚህን ነገሮች በትጋት እንድትፈልጉ ትዕዛዝ እሰጣችኋለሁ፤ የኢሳይያስ ቃላት ታላቅ ናቸውና።

የእስራኤል ቤት የሆኑትን ህዝቦቼን በተመለከተ፣ ስለሁሉም ነገሮች በእርግጥ ተናግሯል፤ ስለዚህ ለአህዛብ ደግሞ መናገሩ አስፈላጊ ነው።

እናም የተናገራቸው፣ እንዲሁም በተናገራቸው ቃላት መሰረት፣ ሁሉም ነገሮች ሆነዋልም፣ ይሆናሉም

ስለዚህ ቃሌን ልብ ብላችሁ አድምጡ፤ የተናገርኳችሁንም ነገሮች ፃፉ፤ እናም በአብ ጊዜና ፈቃድ መሰረት እነርሱ ወደ አህዛብ ይሄዳሉ።

እናም ቃሌን የሚሰማና ንሰሃ የሚገባ እናም የሚጠመቅ እርሱ ይድናል። ነቢያትን ፈልጓቸው፣ ስለነዚህ ነገሮች የሚመሰክሩ ብዙዎች በዚያ ናቸውና።

እናም እንዲህ ሆነ ኢየሱስ እነዚህን ቃላት በድጋሚ በተናገራቸው ጊዜ፣ የተቀበሉአቸውን ቅዱሳን መፃህፍት በጥልቀት ካስረዳቸው በኋላ እንዲህ ሲል ተናገራቸው፥ እነሆ፣ እናንተ ያልጻፍኳቸው፣ እንድትፅፉ የፈለግሁት ሌሎች ቅዱሳን መጽሐፍት አሉ።

እናም እንዲህ ሆነ ለኔፊም እንዲህ አለው፥ ያስቀመጥከውን መዝገብ አምጣ።

እናም ኔፊም መዛግብቱን ባመጣና ከፊቱ ባደረገውም ጊዜ፣ ኢየሱስ ተመለከታቸውና እንዲህ አለ፥

እውነት እላችኋለሁ፣ አገልጋዬን ላማናዊውን ሳሙኤል በዛን ቀን አብ በእኔ ስሙን በሚያስከብርበት ጊዜ ብዙ የሞቱ ቅዱሳን እንደሚነሱና ለብዙዎች እንደሚታዩ፣ እናም እነርሱንም እንደሚያስተምሩ ለዚህ ህዝብ እንዲመሰክር አዘዝኩት። እናም ይህ አልነበረምን? ብሎ ተናገራቸው።

እናም ደቀመዛሙርቱ እንዲህ ሲሉ መለሱለት፥ አዎን፣ ጌታ ሆይ፣ ሳሙኤል በቃልህ መሰረት ተንብዮ ነበር፣ እናም ሁሉም ተፈጽመው ነበር።

፲፩ እናም ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፥ ብዙዎች ቅዱሳን እንደተነሱና፣ ለብዙዎች እንደተገለጡና እነርሱን እንዳስተማሩ እንዴት አልተፃፉም?

፲፪ እናም እንዲህ ሆነ ኔፊም ይህ ነገር እንዳልተፃፈ አስታወሰ።

፲፫ እናም እንዲህ ሆነ ኢየሱስም መፃፍ እንዳለበት አዘዘ፤ ስለዚህ እርሱ እንዳዘዘውም ተፃፈ።

፲፬ እናም እንዲህ ሆነ ኢየሱስም እነርሱ የፃፉትን ቅዱሳን መጽሐፍትን በሙሉ በአንድ ላይ በአስረዳቸው ጊዜ፣ እርሱም ለእነርሱ ያስረዳቸውን ነገሮች ማስተማር እንዳለባቸው አዘዛቸው።