ሦስተኛው ኔፊ

የኔፊ መፅሐፍ የሔለማን ልጅ የነበረው የኔፊ ልጅ

፫ ኔፊ 

እናም ሔለማን፤ የአልማ ልጅ የነበረው፣ የአልማ ልጅ በሴዴቅያስ የመጀመሪያ የንግስ ዘመን የይሁዳ ንጉስ የነበረው ከኢየሩሳሌም የወጣው፣ የኔፊ ዝርያ የነበረውና የሌሂ ልጅ የነበረው፤ የሔለማን ልጅ ነበር።
ምዕራፍ ፩

የሔለማን ልጅ፣ ኔፊ፣ ከምድሪቱ ሄደ፤ እናም የእርሱ ልጅ ኔፊ መዛግብቱን ጠበቃቸው—ምልክቶች እንደዚሁም ድንቅ ነገሮች ብዙ ቢሆንም ኃጢአተኞች ፃድቃንን ለመግደል አቀዱ—የክርስቶስ መወለጃ ምሽትም ደረሰ—ምልክቱ ተሰጠ፣ እናም አዲስ ኮከብ ታየች—ውሸትና ማጭበርበር ተስፋፋ፣ እናም የጋድያንቶን ዘራፊዎች ብዙዎችን ገደሉ። ፩–፬ ዓ.ም. ገደማ።

ምዕርፍ ፪

ክፋትና እርኩሰት በህዝቡ መካከል ተስፋፋ—ኔፋውያን እና ላማናውያን ከጋድያንቶን ዘራፊዎች እራሳቸውን ለመከላከል ተዋሃዱ—የተለወጡ ላማናውያን ነጭ ሆኑ እናም ኔፋውያን ተብለው ተጠሩ። ፭–፲፮ ዓ.ም. ገደማ።

ምዕራፍ ፫

የጋድያንቶን መሪ፣ ጊድያንሒ፣ ላኮኔዎስ እናም ኔፋውያን እራሳቸውን እንዲሁም ምድራቸውን እንዲያስረክቡ በማስገደድ ጠየቀ—ላኮኔዎስ የወታደሮቹ ዋና ሻምበል አድርጎ ጊድጊዶኒን ሾመው—ኔፋውያን በዛራሄምላ እናም በለጋሱ ምድር እራሳቸውን ለመከላከል በአንድነት ተሰበሰቡ። ፲፮–፲፰ ዓ.ም. ገደማ።

ምዕራፍ ፬

የኔፋውያን ወታደሮች የጋድያንቶን ዘራፊዎችን አሸነፉ—ጊድያንሒ ተገደለ፣ እናም ተከታዩ ዜምነሪያህ ተሰቀለ—ኔፋውያን ለድላቸው ጌታን አወደሱ። ፲፱–፳፪ ዓ.ም. ገደማ።

ምዕራፍ ፭

ኔፋውያን ንሰሃ ገቡ እናም ኃጢአቶቻቸውን ተዉ—ሞርሞን የህዝቡን ታሪክ ፃፈ እናም ዘላለማዊውን ቃል አወጀ—እስራኤል ለረጅም ጊዜ ከተበተነበት ይሰበሰባል። ፳፪–፳፮ ዓ.ም. ገደማ።

ምዕራፍ ፮

ኔፋውያን በለፀጉ—ኩራት፤ ሀብት እናም በመደብ መለያየት ተጀመረ—በጥል የተነሳም ቤተክርስቲያኗ ተከፋፈለች—ሰይጣን ሰዎችን በአመጽ መራቸው—ብዙ ነቢያት ስለንሰሃ ጮሁ እናም ተገደሉ—ገዳዮቻቸውም የአስተዳደሩን ቦታ ለመያዝ አሴሩ። ፳፮–፴ ዓ.ም. ገደማ።

ምዕራፍ ፯

ዋናው ዳኛ ተገደለ፣ መንግስቱም ጠፋ፣ እናም ህዝቡም በጎሳ ተከፋፈለ—ፀረ ክርስቶስ የሆነው ያዕቆብም የሚስጥራዊው ሴራዎች ንጉስ ሆነ—ኔፊ ንሰሃንና በክርስቶስ እምነትን ሰበከ—መላዕክት ዕለት በዕለት አገለገሉት፣ እናም ወንድሙን ከሞት አስነሳ—ብዙዎች ንሰሃ ገቡ፣ እናም ተጠመቁ። ፴–፴፫ ዓ.ም. ገደማ።

ምዕራፍ ፰

ኃይለኛ ነፋስ፤ የመሬት መንቀጥቀጥ፤ እሳት፤ አውሎ ነፋስ እናም ታላቁ ጥፋት የክርስቶስን ስቅለት መሰከሩ—ብዙ ሰዎች ጠፉ—ምድርን ለሦስት ቀናት ጨለማ ሸፈናት—በህይወት የተረፉት ሰዎች በዕድላቸው አማረሩ። ፴፫–፴፬ ዓ.ም. ገደማ።

ምዕራፍ ፱

በጭለማው ውስጥ፣ የክርስቶስ ድምጽ በክፋታቸው የተነሳ የብዙ ሰዎችን እንዲሁም የከተሞቹን ጥፋት አወጀ—መለኮታዊነቱንም ደግሞ አወጀ፣ የሙሴ ህግም እንደተሟላም አስታወቀ፣ እናም ሰዎችም ወደ እርሱ እንዲመጡ፣ እናም እንዲድኑ ጋበዛቸው። ፴፬ ዓ.ም. ገደማ።

ምዕራፍ ፲

በምድሪቱም ላይ ለብዙ ሰዓታት ዝምታ ሆነ—ዶሮ ጫጩቶችዋን እንደምትሰበስብ የክርስቶስ ድምፅም ህዝቡን ለመሰብሰብ ቃል ኪዳን ገባ—ፃድቃኖች የነበሩትም አብዛኞቹም ተጠብቀዋል። ፴፬–፴፭ ዓ.ም. ገደማ።

ህዝቡ በለጋስ ምድር በተሰበሰበበት ኢየሱስ ክርስቶስ ለኔፊ ህዝብ እራሱን ገለፀም፣ አስተማራቸውም፤ እናም በዚህ መንገድ ነበር እራሱን ያሳያቸው።

ምዕራፍ ፲፩ እስከ ፳፮ አጠቃሎ የያዘ።

ምዕራፍ ፲፩

አብ ስለተወደደው ልጁ መሰከረ—ክርስቶስ ተገለጠ፣ እናም ስለኃጢያት ክፍያው ተናገረ—ህዝቡም በእጁና በእግሩ፣ እናም በጎኑ ላይ የነበረውን የቁስሉን ምልክት ዳሰሱት—ሆሳዕና ብለውም ጮኹ—የጥምቀት ደንብና ስርዓት አስተማራቸው—የጸብ መንፈስ ከዲያብሎስ ነው—የክርስቶስ ትምህርት ሰዎች እንዲያምኑና፣ እንዲጠመቁ፣ እናም መንፈስ ቅዱስን እንዲቀበሉ ነው። ፴፬ ዓ.ም. ገደማ።

ምዕራፍ ፲፪

ኢየሱስ አስራ ሁለቱን ደቀመዛሙርት ጠራ እናም ስልጣንን ሰጣቸው—በተራራው ላይ እንዳደረገው ስብከት ለኔፋውያንም አደረገ—ብፅዕናን ተናገራቸው—ትምህርቱም የላቀ ነበር እናም ከሙሴ ህግም ቅድሚያ ያለው ነው—እርሱና አባቱ ፍፁም እንደሆኑ እነርሱም ፍጹም እንዲሆኑ ታዘዋል—ማቴዎስ ፭ን አነጻፅሩ። ፴፬ ዓ.ም. ገደማ።

ምዕራፍ ፲፫

ኢየሱስ ለኔፋውያን የጌታን ፀሎት አስተማረ—በሰማይ ሀብትን ማስቀመጥ ይገባቸዋል—አስራ ሁለቱ ሐዋርያት በአገልግሎታቸው ወቅት ስለጊዜያዊ ነገሮች እንዳያስቡ ታዘዙ—ማቴዎስ ፮ን አነጻፅሩ። ፴፬ ዓ.ም. ገደማ።

ምዕራፍ ፲፬

አትፍረዱ፤ እግዚአብሔርን ጠይቁ፤ ከሃሰተኛ ነቢያት ተጠንቀቁ በማለት ኢየሱስ አዘዘ—የአባታቸውን ፈቃድ ለሚያደርጉ የደህንነትን ቃል ገብቶላቸዋል—ማቴዎስ ፯ን አነጻፅሩ። ፴፬ ዓ.ም. ገደማ።

ምዕራፍ ፲፭

ኢየሱስ የሙሴ ህግ በእርሱ እንደተፈፀም ተናገረ—ኔፋውያን በኢየሩሳሌም የተናገረላቸው ሌሎቹ በጎች ናቸው—በክፋታቸው የተነሳ፣ በኢየሩሳሌም ያሉ የጌታ ሰዎች ስለተበተኑት የእስራኤል በጎች አያውቁም። ፴፬ ዓ.ም. ገደማ።

ምዕራፍ ፲፮

ኢየሱስ ሌሎችን የጠፉትን የእስራኤል በጎች ይጎበኛቸዋል—በኋለኛው ቀን ወንጌል ለአህዛብ እናም ወደ እስራኤል ቤት ይሄዳል—እግዚአብሔር ፅዮንን ዳግም በሚመልስበት ጊዜ የጌታ ሰዎች ዐይን ለዐይን ይተያያሉ። ፴፬ ዓ.ም. ገደማ።

ምዕራፍ ፲፯

ኢየሱስ ህዝቡ ስለቃሉ እንዲያገናዝቡ እናም እንዲፀልዩ አዘዘ—በሽተኞቻቸውን ፈወሰ—ለመፃፍ በማይቻል ቋንቋ ስለህዝቡ ፀለየ—ህፃናቶቻቸውን መላዕክት አስተማሩአቸው እናም በእሳት ተከበቡ። ፴፬ ዓ.ም. ገደማ።

ምዕራፍ ፲፰

ኢየሱስ በኔፋውያን መካከል ቅዱስ ቁርባንን ጀመረ—ሁል ጊዜም በስሙ እንዲጸልዩ ታዘዙ—ብቁ ሳይሆኑ ስጋውን የሚበሉ እናም ደሙን የሚጠጡ ይኮነናሉ—ደቀመዛሙርቱ መንፈስ ቅዱስን እንዲሰጡ ስልጣን ተሰጣቸው። ፴፬ ዓ.ም. ገደማ።

ምዕራፍ ፲፱

አስራ ሁለቱ ደቀመዛሙርት ህዝቡን አስተማሩና መንፈስ ቅዱስንም እንዲቀበሉ ፀለዩ—ደቀመዛሙርቱም ተጠመቁና መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ እናም የመላዕክት አገልግሎትንም ተቀበሉ—ኢየሱስ ሊፃፉ የማይችሉ ቃላትን በመጠቀም ፀለየ—ስለነዚህ የኔፋውያንንም እጅግ ታላቅ የሆነ እምነት መሰከረ። ፴፬ ዓ.ም. ገደማ።

ምዕራፍ ፳

ኢየሱስ በተአምራት ዳቦና ወይኑን አቀረበ፣ እናም በድጋሚ ለህዝቡ ቅዱስ ቁርባንን ሰጣቸው—የያዕቆብ ቅሪት የሆኑትም ጌታ አምላካቸውን ወደማወቁ ይመጣሉና አሜሪካንም ይወርሳሉ—ኢየሱስ እንደሙሴ ዓይነት ነቢይ ነው፣ እናም ኔፋውያን የነቢያቱ ልጆች ናቸው—ሌሎቹ የጌታ የሆኑት ህዝቦችም በኢየሩሳሌም ይሰበሰባሉ። ፴፬ ዓ.ም. ገደማ።

ምዕራፍ ፳፩

መፅሐፈ ሞርሞን ሲመጣ እስራኤል ትሰበሰባለች—አህዛብም ነፃ ህዝብ በመሆን በአሜሪካ ይደራጃሉ—ካመኑ እናም ታዛዥ ከሆኑ ይድናሉ፤ አለበለዚያ ይቆረጣሉ እናም ይጠፋሉ—እስራኤል አዲሲቷን ኢየሩሳሌ ትመሰርታለች፣ እናም የጠፉት ነገዶችም ይመለሳሉ። ፴፬ ዓ.ም. ገደማ።

ምዕራፍ ፳፪

በመጨረሻው ቀን ፅዮንና ካስሚያዎችዋ ይቋቋማሉ፣ እናም እስራኤል በምህረትና በደግነት ይሰበሰባሉ—እነርሱም አሸናፊ ይሆናሉ—ኢሳይያስ ፶፬ን አነጻፅሩ። ፴፬ ዓ.ም. ገደማ።

ምዕራፍ ፳፫

ኢየሱስ የኢሳይያስን ቃላት አጸደቀ—ህዝቡ ነቢያትን እንዲፈልጉ አዘዘ—ላማናዊው ሳሙኤል ስለትንሣኤ የተናገራቸው ቃላት በመዝገቦቻቸው ተጨምረዋል። ፴፬ ዓ.ም. ገደማ።

ምዕራፍ ፳፬

የጌታ መልዕክተኛ የክርስቶን ዳግም ምፅዓት መንገድ ያዘጋጃል—ክርስቶስ በፍርድ ወንበር ይቀመጣል—እስራኤል አስራትን እናም በኩራትን እንዲከፍል ታዛለች—የመታሰቢያ መጽሐፍ ተጠብቋል—ሚልክያስ ፫ን አነጻፅሩ። ፴፬ ዓ.ም. ገደማ።

ምዕራፍ ፳፭

በዳግም ምፅዓት ጊዜ ትዕቢተኞች፣ እናም ኃጢአተኞች እንደገለባ ይቃጠላሉ—ኤልያስ ከታላቁና ከአስፈሪው ቀን በፊት ይመለሳል—ሚልክያስ ፬ን አነጻፅሩ። ፴፬ ዓ.ም. ገደማ።

ምዕራፍ ፳፮

ኢየሱስ ከመጀመሪያ እስከመጨረሻው ያሉትን ነገሮች በሙሉ አብራራ—ህፃናት እንዲሁም ልጆች ሊፃፉ የማይችሉ አስደናቂ ነገሮችን ተናገሩ—በክርስቶስ ቤተክርስቲያን የነበሩት በመካከላቸው ሁሉም ነገሮች በጋራ ነበሩአቸው። ፴፬ ዓ.ም. ገደማ።

ምዕራፍ ፳፯

ኢየሱስ ቤተክርስቲያኗን በስሙ እንዲጠሩ አዘዛቸው—ወንጌሉም አገልግሎቱንና የኃጢያት ክፍያውን የያዘ ነው—ሰዎች በመንፈስ ቅዱስም ይነፁ ዘንድ ንሰሃ እንዲገቡና እንዲጠመቁ ታዘዋል—ኢየሱስ እንደሚሆነውም ይሁኑ። ከ፴፬–፴፭ ዓ.ም. ገደማ።

ምዕራፍ ፳፰

ከአስራ ሁለቱ ደቀመዛሙርት ዘጠኙ ሲሞቱ የክርስቶስን መንግስት ለመውረስ ፈለጉ እናም ቃል ተገብቶላቸዋል—ሦስቱ ኔፋውያን ክርስቶስ በድጋሚ ወደ ምድር እስከሚመጣ በምድር ላይ ለመቆየት ፈለጉና በሞት ላይም ስልጣን ተሰጣቸው—እነርሱም ተለውጠዋልና ሊነገሩ የማይገቡ ነገሮችን አዩ፣ እናም አሁን በሰዎች መካከል እያገለገሉ ናቸው። ከ፴፬–፴፭ ዓ.ም. ገደማ።

ምዕራፍ ፳፱

የመፅሐፈ ሞርሞን መምጣት ጌታ እስራኤልን የሚሰበስብበት እንዲሁም ቃል ኪዳኑን ለመፈጸም የሚጀምርበት ምልክት ነው—የኋለኛው ቀን ራዕዮችን እንዲሁም ስጦታዎችን የማይቀበሉ የተረገሙ ይሆናሉ። ከ፴፬–፴፭ ዓ.ም. ገደማ።

ምዕራፍ ፴

የኋለኛው ቀን አህዛብ ንሰሃ እንዲገቡ፣ እናም ወደ ክርስቶስ እንዲመጡ፣ እና ከእስራኤል ቤትም ጋር እንዲቆጠሩ ታዘዋል። ከ፴፬–፴፭ ዓ.ም. ገደማ።