ቅዱሳት መጻህፍት
አልማ ፴፬


ምዕራፍ ፴፬

አሙሌቅ ቃሉ ለቤዛነታቸው በክርስቶስ ውስጥ መሆኑን መሰከረ—የኃጢያት ክፍያው ካልተደረገ፣ የሰው ዘር ሁሉ መጥፋት ነበረበት—የሙሴ ህጎች በሙሉ ወደ እግዚአብሔር ልጅ መስዋዕትነት ይጠቁማሉ—ዘለዓለማዊው የደህንነት ዕቅድ የተመሰረተው በእምነት እና በንስሃ ላይ ነው—ለጊዜያዊውና ለመንፈሳዊው በረከት ፀልዩ—ይህ ህይወት ሰዎች እግዚአብሔርን ለመገናኘት የሚዘጋጁበት ወቅት ነው—በእግዚአብሔር ፊት በፍርሀት የ ራሳችሁን ደህንነት አከናውኑ። በ፸፬ ም.ዓ. ገደማ።

እናም አሁን እንዲህ ሆነ አልማ እነዚህን ቃላት ከተናገራቸው በኋላ በመሬት ላይ ተቀምጦ ነበር፣ እናም አሙሌቅ ተነሳና፣ እንዲህ በማለት እነርሱን ማስተማር ጀመረ፥

ወንድሞቼ እንደማስበው የእግዚአብሔር ልጅ ስለመሆኑ ያስተማርናችሁን የክርስቶስን መምጣት በተመለከተ የተነገሩትን ችላ ማለት የማይቻል ነው፤ አዎን፣ ከእኛ ከመለየታችሁ በፊት እነዚህን ነገሮች በይበልጥ እንደተማራችሁት አውቃለሁ።

እናም በስቃያችሁ የተነሳ ምን ማድረግ እንዳለባችሁ እንዲያሳውቃችሁ የተወደደውን ወንድሜን ለመጠየቅ በመፈለጋችሁና፣ እርሱ የ ራሳችሁን አዕምሮ እንድታዘጋጁ በመጠኑ ተናግሯል፤ አዎን እናም እምነትና ትዕግስት እንዲኖራችሁ መክሯችኋል—

አዎን፣ የመልካምነቱን ልምምድ እንድትሞክሩት ዘንድ፣ ታላቅ እምነት ኖሯችሁ ቃሉን በልባችሁ እንድትተክሉትም መክሯችኋል።

እናም ቃሉ በእግዚአብሔር ልጅ ውስጥ መኖሩን፣ ወይም ክርስቶስ እንደሌለ ያላችሁን ታላቅ ጥያቄ በአዕምሮአችሁ ውስጥ እንደሆነ ተመልክተናል።

እናም በብዙ ማስረጃዎች ቃሉ ደህንነት በክርስቶስ ውስጥ መሆኑን ወንድሜ እንዳረጋገጠላችሁ ደግሞም ተመልክታችኋል።

ወንድሜም ቤዛነት በእግዚአብሔር ልጅ አማካኝነት እንደሚመጣ የዜኖስን ቃል፣ እናም ደግሞ የዜኖቅን ቃል፣ በመጥቀስ ተናገረ፤ እናም ደግሞ እነዚህ ነገሮች እውነት መሆናቸውን ለማረጋገጥ የሙሴን ቃላት ጠቀሰ።

እናም አሁን፣ እነሆ፣ እኔ ራሴ እነዚህ ነገሮች እውነት መሆናቸውን እመሰክራለሁ። እነሆ፣ እንዲህም እላችኋለሁ፥ ክርስቶስ የህዝቡን መተላለፍ በእራሱ ላይ ለመሸከም በሰው ልጆች መካከል እንደሚመጣ፣ እናም ለዓለም ኃጢያት ክፍያን እንደሚከፍል አውቃለሁ፤ ጌታ እግዚአብሔር ይህን ተናግሯልና።

የኃጢያት ክፍያ መኖሩ አስፈላጊ ነውና፤ በዘለአለማዊው አምላክ ታላቅ ዕቅድ መሰረት የኃጢያት ክፍያ መኖር አለበት፤ አለበለዚያ የሰው ዘር ሁሉ መጥፋት እንዳለባቸው የማይቀር ነበር፤ አዎን ሁሉም ጠጣሮች ናቸው፤ አዎን ሁሉም ወድቀዋልና ጠፍተዋል፣ እናም መፈጸሙ አስፈላጊ ከሆነው ከኃጢያት ክፍያ በቀር መጥፋት አለባቸው።

ታላቅ እና የመጨረሻ መስዋዕትነት መኖሩ አስፈላጊ ነውና፤ አዎን፣ የሰውም ሆነ የእንሰሳ እንዲሁም የማንኛውም አዕዋፍ መስዋዕትነት አይደለም፤ ምክንያቱም የሰው መስዋዕትነት መሆን አይገባውም፤ ነገር ግን መጨረሻ የሌለው እንዲሁም ዘለአለማዊ መስዋዕት መሆን ይገባዋል።

፲፩ እንግዲህ ለሌላኛው እንደ ኃጢያቶች ክፍያ ደሙን መስዋዕት ሊያደርግ የሚችል ማንም ሰው የለም። እንግዲህ፣ አንድ ሰው ከገደለ እነሆ ፍፁም የሆነው ህጋችን የወንድሙን ህይወት ያጠፋልን? እኔ ግን አይሆንም እላለሁ።

፲፪ ነገር ግን ህጉ የገደለውን ሰው ህይወት ይጠይቃል፤ ስለዚህ ለዓለም ኃጢያት ወሰን ከሌለው የኃጢያት ክፍያ በስተቀር ሊበቃ የሚችል ምንም የለም።

፲፫ ስለዚህ፣ ታላቅና የመጨረሻ መስዋዕትነት መኖሩ አስፈላጊ ነው፤ እናም የደም መፋሰሱ መቆም መሆን አለበት፣ እንዲሁም መሆኑ አስፈላጊ ነው፤ ከዚያም የሙሴ ህግ ይፈፀማል፤ አዎን፣ እያንዳንዱ ነጥብና ምልክት በሙሉ ይፈፀማል፣ እናም የትኛውም ሳይከናወን አይቀርም።

፲፬ እናም እነሆ፣ ይህ እያንዳንዱ ትንሽ ክፍል ወደ ታላቁና የመጨረሻ መስዋዕት የሚጠቁምበት አጠቃላይ የህጉ ትርጓሜ ነው፤ እናም የታላቁና የመጨረሻ መስዋዕትነት የእግዚአብሔር ልጅ ይሆናል፤ አዎን፣ መጨረሻ የሌለውና ዘለዓለማዊ የሆነው።

፲፭ በዚህም በስሙ ለሚያምኑ ሁሉ ደህንነትን ያመጣል፤ የዚህ የመጨረሻው መስዋዕት ዓላማ ከፍትህ የሚልቀውን ከአንጀት የሆነን ምህረትን ለማምጣት ነው፤ እንዲሁም ለሰዎች በንስሃ እምነት ይኖራቸው ዘንድ መፍትሄ ለማምጣት ነው።

፲፮ እናምእንደዚህም ምህረት የፍትህን ፍላጎት ሊያሟላ ይችላል፣ እናም በጠባቂ ክንዶቹ ይከባቸዋል፤ እምነትንም ንስሃ በመግባት ያልተለማመደ ፍትህ ለሚፈልግበት ህግጋት ሁሉ የተጋለጠ ይሆናል፤ ስለዚህ ለንስሃ እምነት ላለው ብቻ ታላቁና የዘለዓለማዊው ዕቅድ ቤዛነት እንዲመጣ የሚሆነው።

፲፯ ስለዚህ ወንድሞቼ ለንስሃ እምነታችሁን መለማመድ ትጀምሩ ዘንድ፣ በእናንተም ላይ ምህረት እንዲኖረው ቅዱስ ስሙን መጥራት ትጀምሩ ዘንድ እግዚአብሔር ለእናንተ ይፍቀድላችሁ፤

፲፰ አዎን፣ ለምህረት ወደ እርሱ ጩኹ፤ ምክንያቱም እርሱ ለማዳን ኃያል ነውና።

፲፱ አዎን፣ ራሳችሁን ዝቅ አድርጉ፣ እናም ወደ እርሱ ፀሎታችሁን አታቋርጡ።

በመስካችሁ ሳላችሁ ወደ እርሱ ጩኹ፤ አዎን በመንጋዎቻችሁ ሁሉ ላይ።

፳፩ በቤታችሁ፣ አዎን፣ በቤተሰዎቻችሁ ላይ፣ በጠዋት፣ በቀን እንዲሁም በምሽት ወደ እርሱ ጩኹ

፳፪ አዎን፣ የጠላቶቻችሁን ኃይል በመቃወም ወደ እርሱ ጩኹ።

፳፫ አዎን፣ የፅድቅ ሁሉ ጠላት የሆነውን ዲያብሎስን በመቃወም ወደ እርሱ ጩኹ

፳፬ በእርሻችሁ እህሎች ትበለጽጉ ዘንድ ወደ እርሱ ጩኹ።

፳፭ በመስኩ ላይ ያሉት መንጎቻችሁ ይበዙላችሁ ዘንድ ስለእነርሱ ጩኹ።

፳፮ ነገር ግን ይህ ብቻም አይደለም፤ ነፍሳችሁን በእልፍኞቻችሁ፤ እናም በሚስጥር ቦታዎቻችሁ እንዲሁም በምድረበዳው አፍስሱ።

፳፯ አዎን፣ እናም ወደ ጌታ በማትጮኹበት ጊዜ፣ ልባችሁ ለደህንነታችሁና፣ ደግሞ በዙሪያችሁ ላሉት ደህንነት ባለማቋረጥ በፀሎት ወደ እርሱ በመትጋት ሙሉ ይሁን።

፳፰ እናም አሁን እነሆ፣ የተወደዳችሁ ወንድሞቼ፣ እንዲህ እላችኋለሁ፤ ይህ ብቻ ነው ብላችሁ አትገምቱ፤ ምክንያቱም ይህንን ነገር በሙሉ ካደረጋችሁ በኋላ፣ የተቸገሩትንና፣ የታረዙትን ካልረዳችሁ፣ እናም የታመሙትንና የተሰቃዩትን ካልጎበኛችሁና፣ እያላችሁ ለሚሹት ካላችሁ ነገር ካላካፈላችሁ—እኔ እንዲህ እላችኋለሁ፥ ከእነዚህ ነገሮች የትኛውንም ካላደረጋችሁ፣ እነሆ፣ ፀሎታችሁ ከንቱ ነው፣ እናም ለእናንተ የሚጠቅማችሁ ምንም የለም፤ እናንተም እምነትን እንደሚከዱት ግብዞች ናችሁ።

፳፱ ስለዚህ፣ ቸር መሆንን ካላስታወሳችሁ፣ (ምክንያቱም ዋጋ ቢስ ነውና) አጣሪዎቹ እንደሚጥሉዋቸው እናም በሰዎች እግር እንደሚረገጡ አተላ ናችሁ።

እናም አሁን፣ ወንድሞቼ፣ ብዙ ምስክሮችን ከተቀበላችሁ በኋላ፣ ቅዱሳን መጻሕፍት እነዚህን ነገሮች እንደሚመሰከሩላችሁ እያያችሁ፣ እንድትመጡና ለንስሀ ብቁ የሆነ ፍሬ እንድታመጡ ፍላጎቴ ነው።

፴፩ አዎን፣ እናንተ እንድትመጡና፣ ከእንግዲህ ልባችሁን እንዳታጠጥሩ እፈልጋለሁ፤ እነሆም አሁን የደህንነታችሁ ጊዜና ቀን ነው፤ እናም ስለዚህ ንስሃ የምትገቡ ከሆነና፣ ልባችሁን የማታጠጥሩ ከሆነ፣ ታላቁ የቤዛነት ዕቅድ በፍጥነት በእናንተ ላይ ይሆናል።

፴፪ እነሆም፣ ይህ ጊዜ ለሰዎች እግዚአብሔርን ለመገናኘት የዝግጅት ወቅት ነው፤ አዎን፣ እነሆ የዚህ ህይወት ቀናት ሰዎች ስራቸውን የሚያከናውኑባቸው ቀናቶች ናቸው።

፴፫ እናም አሁን፣ ለእናንተ ብዙ ምስክር እንዳላችሁ ቀደም ሲል እንደተናገርኩት፣ ስለዚህ እስከመጨረሻው ድረስ የንስሃ ቀናችሁን እንዳታዘገዩ እለምናችኋለሁ፤ ለዘለዓለማዊው ህይወት እንድንዘጋጅ ከተሰጠን ከዚህ የህይወት ቀን በኋላ፣ እነሆ፣ በዚህ ህይወት ውስጥ ጊዜያችንን በተሻለ ካልተጠቀምን፣ ከዚያም ስራ ለመስራት የማንችልበት የጨለማ ምሽት ይመጣል።

፴፬ ወደ አሰቃቂው ሁኔታ ስትመጡም፣ ንስሃ እገባለሁ፣ እናም ወደ አምላኬ እመለሳለሁ ለማለት አትችሉም። እንደዚህም ለማለት አትችሉም፤ ከዚህ ህይወት በምትወጡ ጊዜ እናንተን የእራሱ ያደረገው ይኸው መንፈስ በዘለዓለማዊው ዓለም እናንተን የእራሱ ለማድረግ ስልጣን ይኖረዋል።

፴፭ እነሆም እስክትሞቱ ድረስ የንስሃ ቀናችሁን የምታዘገዩ ከሆነ፣ እነሆ፣ ለዲያብሎስ መንፈስ ተገዢ ትሆናላችሁና፣ የእራሱ አድርጎ ያትምባችኋል፤ ስለዚህ የእግዚአብሔር መንፈስ ከውስጣችሁ ይወጣልና፣ በእናንተ ውስጥ ስፍራ አይኖረውም፣ እንዲሁም ዲያብሎስ በእናንተ ላይ ሁሉም ስልጣን ይኖረዋል፤ እናም የኃጢአተኞች የመጨረሻ ሁኔታ ይህ ነው።

፴፮ እናም ይህን ያወቅሁት በረከሰ ቤተመቅደስ እንደማይኖር፣ ነገር ግን በፃድቃኖች ልብ ውስጥ እንደሚያድር ጌታ ስለተናገረ ነው፤ አዎን፣ እናም ደግሞ ፃድቃኖች በመንግስቱ እንደሚቀመጡ፣ ከዚያም ደግሞ እንደማይወጡ ተናግሯል፤ ነገር ግን በበጉ ደም ልብሳቸው ይጸዳል።

፴፯ እናም አሁን፣ የተወደዳችሁ ወንድሞቼ፣ እነዚህን ነገሮች እንድታስታውሱ እፈልጋለሁ፣ እናም በእግዚአብሔር ፊት በፍርሃት ደኅንነታችሁን እንድትፈፅሙና፣ የክርስቶስን መምጣት ከእንግዲህ እንዳትክዱ እፈልጋለሁ፤

፴፰ ከእንግዲህ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር እንዳትጣሉም፣ ነገር ግን እንድትቀበሉትና፣ የክርስቶስን ስም በእራሳችሁ ላይ እንድትወስዱት፤ ራሳችሁን እስከትቢያው ድረስ ዝቅ እንድታደርጉና፣ ባላችሁበት ስፍራ ሁሉ በመንፈስና በእውነት እግዚአብሔርን እንድታመልኩ፤ እናም በየቀኑ በእናንተ ላይ ባደረገው ስለበዛው ምህረቱና በረከቱ በምስጋና እንድትኖሩ እፈልጋለሁ።

፴፱ አዎን፣ እናም ደግሞ ወንድሞቼ በዲያብሎስ ፈተናም እንዳትወሰዱ፣ እርሱም በእናንተ ላይ ስልጣን እንዳይኖረው፣ በመጨረሻው ቀንም በእርሱ ስር እንዳትሆኑ ያለማቋረጥ እንድትፀልዩ እመክራችኋለሁ፤ እነሆ እርሱ ምንም መልካም ነገር ዋጋ አይሰጣችሁምና።

እናም አሁን የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ትዕግስት እንዲኖራችሁና፣ ስቃያችሁን ሁሉ እንድትታገሱ እመክራችኋለሁ፤ እጅግ ድሆች በመሆናችሁ ከአስወጧችሁም ላይ አጥብቃችሁ አትነቅፉ፣ ያለበለዚያ እንደእነርሱም ኃጢአተኞች ትሆናላችሁና፤

፵፩ ነገር ግን ትዕግስት ይኑራችሁ፣ እናም አንድ ቀን ከስቃያችሁ ሁሉ እንደምታርፉ ተስፋ በማድረግ ስቃያችሁን ታገሱ።