ቅዱሳት መጻህፍት
አልማ ፴፭


ምዕራፍ ፴፭

የቃሉ መሰበክ የዞራማውያንን ተንኮል ያጠፋል—ወደጌታ የተለወጡትን አስወጡአቸው፣ እነርሱም በኢየርሾን ከአሞንን ሰዎች ጋር ተቀላቀሉ—አልማ በህዝቡ ክፋት አዘነ። በ፸፬ ም.ዓ. ገደማ።

አሁን እንዲህ ሆነ አሙሌቅ ንግግሩን ከጨረሰ በኋላ፣ እራሳቸውን ከህዝቡ ለዩ እናም ወደ ኢየርሾን ምድር መጡ።

አዎን እናም የቀሩት ወንድሞች ቃሉን ለዞራማውያን ከሰበኩ በኋላ ደግሞ ወደ ኢየርሾን ምድር መጡ።

እናም እንዲህ ሆነ በጣም ታዋቂ የሆኑት ዞራማውያን የተሰበኩትን ቃላት በተመለከተ እርስ በእርሳቸው ከተመካከሩ በኋላ ተንኮላቸውን የሚያጠፉባቸው በመሆኑ በቃሉ ተቆጡ፤ ስለዚህ ቃላቱንም አላደመጡትም።

እናም በምድሪቱ ሁሉ የሚኖሩትን ሰዎች በሙሉ መልዕክት ላኩላቸውና፣ ሰበሰቡአቸው፣ እናም የተነገሩትን ቃላት በተመለከተ ከእነርሱ ጋር ተመካከሩ።

እንግዲህ ገዢዎቻቸውና፣ ካህናቶቻቸው፣ እናም መምህራኖቻቸው ለህዝቡ የእነርሱን ፍላጎት እንዲያውቅ አልፈቀዱም፣ ስለዚህ የህዝቡን ሀሳብ በሚስጥር አወቁ።

እናም እንዲህ ሆነ የህዝቡን በሙሉ ሀሳብ ካወቁ በኋላ፣ በአልማና በወንድሞቹ የተነገሩትን ቃላት የሚደግፉትን ሰዎች ከምድሪቱ አባረሩአቸው፤ እነርሱም ብዙ ነበሩ፤ እናም ደግሞ እነርሱ ወደ ኢየርሾን ምድር መጡ።

እናም እንዲህ ሆነ አልማና ወንድሞቹ ሰበኩላቸው።

እንግዲህ በኢየርሾን በነበሩት በአሞን ሰዎች ላይ ዞራማውያን ተቆጥተው ነበር፣ እናም የዞራማውያን ዋና ገዢ እጅግ ክፉ ሰው ስለነበር ከዞራማውያን ምድር ወደ እነርሱ የመጡትን ከምድራቸው እንዲወጡ በመፈለጉ ለአሞን ህዝብ መልዕክት ላከባቸው።

እናም እርሱ በእነርሱ ላይ በርካታ ማስፈራሪያዎችን ተናገረ። እናም አሁን የአሞን ህዝብ ቃሉን አልፈሩም ነበር፤ ስለዚህ እነርሱን አላስወጧቸውም ነበር፣ ነገር ግን ወደእነርሱ የመጡትን ምስኪን ዞራማውያንን በሙሉ ተቀበሉአቸው፤ እናም ተንከባከቧቸውና፣ አለበሱአቸው እንዲሁም የውርስ ምድርንም ሰጡአቸው፤ እናም እንደፈለጉት አስተዳደሩአቸው።

እንግዲህ ይህም ዞራማውያን በአሞን ህዝብ ላይ ለቁጣ እንዲነሳሱ ቀሰቀሳቸው፤ እናም ከላማናውያን ጋር ተቀላቀሉ፣ ደግሞም እነርሱንም በቁጣ ማነሳሳት ጀመሩ።

፲፩ እናም ዞራማውያንና ላማናውያን በአሞን ላይና፣ ደግሞ በኔፋውያን ህዝብ ላይ ለጦርነት ዝግጅት ጀመሩ።

፲፪ እናም በኔፊ ህዝብ ላይ የመሣፍንቱ አስራ ሰባተኛው የንግሥ ዘመን ተፈፀመ።

፲፫ እናም የአሞን ህዝብ ከኢየርሾን ምድር ሸሹና፣ ወደ ሜሌቅ ምድር መጡ፣ እናም የኔፋውያን ወታደሮች ከላማናውያን ወታደሮች እንዲሁም ከዞራማውያን ወታደሮች ጋር ይጣሉ ዘንድ የኢየርሾን ምድርን ሰጡአቸው፤ እናም በመሣፍንቱ አስራ ስምንተኛ የንግስ ዘመን መጀመሪያ ላይ በላማናውያንና በኔፋውያን መካከል ጦርነት ተጀመረ፤ እናም የጦርነታቸው ታሪክም ከዚህ በኋላ ይቀርባል።

፲፬ እናም አልማና፣ አሞን፣ እናም ወንድሞቻቸው፣ ደግሞም የአልማ ሁለት ልጆች በርካታ ዞራማውያንን ወደ ንስሃው ለማምጣት በእግዚአብሔር እጅ መገልገያ ከሆኑ በኋላ ወደ ዛራሔምላ ምድር ተመለሱና፣ ወደ ንስሃው የመጡት ብዙዎች ከምድራቸው ተሰደዱ፤ ነገር ግን በኢየርሾን ምድር የርስት ሥፍራ ነበራቸው፣ እናም እራሳቸውንና፣ ሚስቶቻቸውን፣ እናም ልጆቻቸውንና፣ ምድራቸውን ለመከላከል የጦር መሳሪያዎቻቸውን አነሱ።

፲፭ እንግዲህ አልማ በህዝቡ ክፋት፣ አዎን ጦርነትና፣ ደም መፋሰስ፣ እናም በመካከላቸው በነበረው ፀብ በማዘኑ፤ በሁሉም ከተሞች እንዲሁም በህዝቡ ሁሉ መካከል ቃሉን በመናገሩ፣ ወይም ቃሉን ለመናገር መልዕክት በመላኩ፤ እናም የህዝቡ ልብ መጠጠሩን በመመልከቱና በቃሉም ጥብቅነት የተነሳ መናደድ በመጀመራቸው ልቡ እጅግ አዝኖ ነበር።

፲፮ ስለዚህ ለፅድቅ አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች በተመለከተ ለእያንዳንዱ በየግላቸው ሀላፊነታቸውን ለመስጠት ልጆቹን በአንድ ላይ እንዲሰባሰቡ አደረገ። እናም በአልማ ምዝገባ መሰረት እርሱ የሰጣቸው የትዕዛዛት መዛግብት አሉን።