ቅዱሳት መጻህፍት
አልማ ፶፬


ምዕራፍ ፶፬

አሞሮን እና ሞሮኒ እስረኞቻቸውን ለመለዋወጥ ተደራደሩ—ላማናውያን እንዲወጡ እናም የሞት ጥቃታቸውን እንዲያቆሙ ሞሮኒ ጠየቀ—አሞሮን ኔፋውያን የጦር መሳሪያቸውን እንዲጥሉ፣ እናም በላማናውያን ስር እንዲሆኑ ጠየቀ። በ፷፫ ም.ዓ. ገደማ።

እናም አሁን እንዲህ ሆነ በመሣፍንቱ ሀያ ዘጠነኛ ዓመት የንግስ ዘመን ውስጥ አሞሮን እስረኞችን ለመለዋወጥ በመፈለጉ ወደ ሞሮኒ መልዕክተኛን ላከ።

እናም እንዲህ ሆነ ሞሮኒ ላማናውያንን ለመርዳት የቀረበውን ድጋፍ ለራሱ ህዝቦች ድጋፍ እንዲሆን በመፈለጉ በጥያቄው እጅግ ደስታ ተሰማው፤ እናም ደግሞ የራሱን ህዝብ ወታደሮቹን እንዲያጠናክሩለት ፈለገ።

እንግዲህ ላማናውያን በርካታ ሴቶችንና ልጆችን ማርከው ነበር፣ እናም ከሞሮኒ እስረኞች ውስጥ፣ ወይንም ሞሮኒ ከማረካቸው መካከል ምንም ሴትም ሆነ ልጅ አልነበረም፤ ስለዚህ ሞሮኒ ከላማናውያን በሚቻለው ሁሉ የኔፋውያን እስረኞች የሆኑትን ብዙዎችን ለማግኘት በእርቅ ላይ ወሰነ።

ስለዚህ ሞሮኒ ደብዳቤ ፃፈ፣ እናም በአሞሮን አገልጋይ ላከ፣ ይኸው አገልጋይም ደብዳቤ ወደ ሞሮኒ አምጥቶ የነበረው ነው። እናም ለአሞሮን የፃፈው ቃል እንዲህ ይላል፥

እነሆ፣ አሞሮን፣ በህዝቤ ላይ ያደረጋችሁትን፣ ወይንም የአንተ ወንድም በእነርሱ ላይ ያነሳውን፣ እናም ከሞተም በኋላ ጦርነቱን ለመቀጠል ስለወሰንከው ጦርነት በተመለከተ በመጠኑ ፅፌአለሁ።

እነሆ፣ ንስሃ ካልገባችሁ፣ እናም ሠራዊቶቻችሁን ወደ ራሳችሁም ምድር ወይንም የኔፊ ምድር ወደሆነው ካልወሰዳችሁ በእናንተ ላይ ስለሚንዠበባለው ስለእግዚአብሔር ፍትህ እና የኃያሉ ጎራዴ ቁጣ በመጠኑ ልንገርህ።

አዎን፣ ልትሰሟቸው የምትችሉ ቢሆን ኖሮ፣ እነዚህን ነገሮች እነግራችኋለሁ፤ አዎን፣ ንስሃ ካልገባችሁ እናም የመግደል ዓላማችሁን ካልተዋችሁ፣ እናም ወደራሳችሁ ምድር ከወታደሮቻችሁ ጋር ካልተመለሳችሁ፣ እንደ አንተና ወንድምህ እንደነበራችሁበት ግድያ ያደረጉትን ሊቀበላቸው ስለሚጠብቀው፣ አሰቃቂውን ሲኦል በተመለከተ እነግራችኋለሁ።

ነገር ግን አንዴ እነዚህን ነገሮች ስላልተቀበላችሁ፣ እናም ከጌታ ህዝብም ጋር ስለተዋጋችሁ፣ እንደዚሁ በድጋሚ እንደምታደርጉት እገምታለሁ።

እናም አሁን እነሆ፣ እናንተን ለመቀበል ተዘጋጅተናል፤ አዎን፣ እናም ያሰባችሁትን ካልተዋችሁ፣ እነሆ የዚያን ያልተቀበላችሁትን እግዚአብሔር ቁጣውን በራሳችሁ ታደርጋላችሁ፣ እንዲሁም በፍጹም እስክትጠፉ ድረስ።

ነገር ግን ጌታ ህያው እንደሆነ እናንተ ካልለቀቃችሁ በቀር ወታደሮቻችን በእናንተ ላይ ይመጣሉ፣ እናም በቅርቡ ሞት ይመጣባችኋል፣ ከተሞቻችንንና መሬታችንንም መልሰን እናገኛለንና፤ አዎን፣ እናም ኃይማኖታችንንና የአምላካችንን ሁኔታ እንጠብቃለን።

፲፩ ነገር ግን እነሆ፣ እነዚህን ነገሮች በተመለከተ በከንቱ የተናገርኩ ይመስለኛል፤ ወይንም አንተም የሲኦል ልጅ እንደሆንክ እገምታለሁ፣ ስለዚህ ለአንድ እስረኛ የአንድን ሰው፣ ሚስቱንና ልጆቹን ካልለቀቃችሁ በስተቀር፣ እስረኞችን አልለዋወጥም፤ ይህንን የምታደርጉ ከሆነ እስረኞችን እንለዋወጣለን።

፲፪ እናም እነሆ፣ ይህንን የማታደርጉ ከሆነ፣ ከሠራዊቴ ጋር በእናንተ ላይ እመጣባችኋለሁ፣ አዎን፣ ሴቶችና ልጆች ሳይቀሩ አስታጥቃቸዋለሁ፣ እናም በእናንተ ላይ እመጣባችኋለሁና፣ የመጀመሪያው የውርሳችን ምድር ወደሆነው ወደራሳችሁ ምድር ድረስ እከተላችኋለሁ፤ አዎን፣ እናም ደም ለደም፣ አዎን፣ ህይወትም ለህይወት ይሆናል፤ እናም ከምድር ገፅ እስከምትጠፉም ድረስ እዋጋሀለሁ።

፲፫ እነሆ፣ እኔና ህዝቤ ተቆጥተናል፤ እኛን ለመግደል ፈልጋችሁ ነበር፣ እናም እኛ እራሳችንን ብቻ ለመከላከል ፈልገን ነበር። ነገር ግን እነሆ፣ ከዚህ የበለጠም ልታጠፉን ከፈለጋችሁ ልናጠፋችሁ እንፈልጋለን፤ አዎን፣ እናም የመጀመሪያው ውርሳችን የሆነችውን ምድራችንንም እንፈልጋለን።

፲፬ አሁን ደብዳቤዬን እጨርሳለሁ። እኔ ሞሮኒ ነኝ፣ የኔፋውያን ህዝብ መሪ ነኝ።

፲፭ እናም እንዲህ ሆነ አሞሮን ይህንን ደብዳቤ በተቀበለ ጊዜ፣ ተቆጥቶ ነበር፤ እናም ለሞሮኒ ሌላ ደብዳቤ ፃፈ፣ እናም የፃፈው ቃልም እንዲህ ይል ነበር፥

፲፮ እኔ የላማናውያን ንጉስ የሆንኩ አሞሮን ነኝ፤ እናንተ የገደላችሁት የአማሊቅያ ወንድም ነኝ። እነሆ፣ ደሙን በእናንተ እበቀላለሁ፣ አዎን፣ እናም ማስፈራሪያችሁን ስለማልፈራ ከሠራዊቴ ጋር እመጣባችኋለሁ።

፲፯ እነሆ፣ በትክክል ለእነርሱ የሆነውን የመንግስት መብታቸውን እስኪነጥቋቸው ድረስ አባቶቻችሁ በወንድሞቻቸው ላይ ግፍ ሰሩባቸው።

፲፰ እናም አሁን እነሆ፣ የጦር መሳሪያዎቻችሁን የምትጥሉ ከሆነ፣ እናም መንግስት በትክክል ለሚገባቸው ራሳችሁን የምታስገዙ ከሆነ፣ ህዝቤ የጦር መሳሪያውን እንዲጥልና ከእንግዲህ እንዳይዋጋ አደርጋለሁ።

፲፱ እነሆ፣ በእኔና በህዝቤ ላይ ብዙ የሚያስፈሩ ንግግር ተናግራችኋል፤ ነገር ግን እነሆ፣ ማስፈራሪያችሁን አልፈራነውም።

ይሁን እንጂ፣ ለጦር ሰዎቼ ምግብ አስቀምጥላቸው ዘንድ በጥያቄህ መሰረት በደስታ እስረኞችን እቀያየራለሁ፤ እናም ኔፋውያንን በእኛ አገዛዝ ስር ለማድረግ ወይንም ለዘለዓለም እስከሚጠፉ ዘለዓለማዊ የሆነ ጦርነት እናስነሳለን።

፳፩ እናም አልተቀበላችሁትም ያላችሁትን እግዚአብሔር በተመለከተ፣ እነሆ፣ እንደዚህ ዓይነት ፍጡር አናውቅም፤ እናንተም አታውቁም፤ ነገር ግን እንደዚህ ዓይነት ፍጡር ካለ አናውቀውም፣ ነገር ግን እኛንም ሆነ እናንተን ፈጥሯል።

፳፪ እናም ዲያብሎስና ሲኦል ካለ እነሆ እናንተ ከገደላችሁት እንደዚህ ወዳለው ስፍራ ሄዷል ካላችሁበት ከወንድሜ ጋር እንድትኖሩ አይልካችሁምን? ነገር ግን እነዚህ ነገሮች ምንም አይደሉም።

፳፫ እኔ አሞሮን ነኝ፣ እናም አባቶቻችሁ ከኢየሩሳሌም እንዲወጣ ያስገደዱት የዞራም ወገን ነኝ።

፳፬ እናም እነሆ አሁን ደፋር ላማናዊ ነኝ፣ እነሆ ይህ ጦርነት የተደረገው ለተበደሉበት ብቀላ ለማግኘትና፣ ለመንግስታቸው መብታቸውን ለመጠበቅና ለማግኘት ነው፤ እናም ለሞሮኒ የፃፍኩትን ደብዳቤ እደመድማለሁ።