ቅዱሳት መጻህፍት
አልማ ፶፱


ምዕራፍ ፶፱

ሞሮኒ የሔለማንን ወታደሮችን እንዲያጠናክር ፓሆራንን ጠየቀው—ላማናውያን የኔፋውያን ከተማ ያዙ—ሞሮኒ በመንግስቱ ላይ ተናደደ። በ፷፪ ም.ዓ. ገደማ።

እንግዲህ እንዲህ ሆነ በኔፊ ህዝብ ላይ በመሣፍንቱ ሠላሳኛ ዓመት የንግስ ዘመን ሞሮኒ የሔለማንን ደብዳቤ ተቀብሎ ካነበበ በኋላ፣ በደህንነቱ አዎን፣ ሔለማን የተቀሙትን ምድሮች ለማግኘት ባደረገው ታላቅ ድል እጅግ ተደስቶ ነበር።

አዎን እናም ሞሮኒ እርሱ በነበረበትም ምድር ሁሉ ዙሪያ ያሉት ይደሰቱ ዘንድ ለህዝቡ ይህ ሁሉ እንዲታወቅ አስደረገ።

እናም እንዲህ ሆነ ሞሮኒ በአስደናቂ ሁኔታ በድጋሚ ያገኟቸውን ምድሮች ለመጠበቅ እንዲችሉ፣ ሔለማንን ወይንም የሔለማን ወታደሮችን ለማበርታት ሰዎች እንዲሰባሰቡ እንደፈለገ ለፓሆራን በፍጥነት ደብዳቤ ላከ።

እናም እንዲህ ሆነ ሞሮኒ ወደ ዛራሔምላ ምድር ይህንን ደብዳቤ በላከ ጊዜ፣ የቀሩትንና ላማናውያን የወሰዱባቸውን ከተሞች ያገኝ ዘንድ በድጋሚ ዕቅድ ማቀድ ጀመረ።

እናም እንዲህ ሆነ ሞሮኒ ከላማናውያን ጋር ለመዋጋት ዝግጅት በሚያደርግበት ጊዜ፣ እነሆ፣ ከሞሮኒ ከተማና፣ ከሌሂ ከተማና፣ ከሞሪያንተን ከተማ የተሰባሰቡት የኔፋውያን ሰዎች በላማናውያን ጥቃት ደረሰባቸው።

አዎን፣ ከማንቲ ምድር እናም በዙሪያው ካለው ምድር እንዲሸሹ የተገደዱትም በዚህች ምድር ከላማናውያን ጋር ሊቀላቀሉ መጡ።

እናም በቁጥር እጅግ ብዙ ስለነበሩ፣ አዎን፣ እናም በአሞሮን ትዕዛዝ ከቀን ቀን ጥንካሬን በማግኘታቸው በኔፋውያን ሰዎች ላይ መጡና፣ በአሰቃቂ ሁኔታ ያጠቁአቸውና ይገድሉአቸው ጀመሩ።

እናም ወታደሮቻቸው በቁጥር ብዙ ስለነበሩ የተቀሩት የኒፋያህ ሰዎች እንዲሸሹ ተገደዱ፤ እናም ከሞሮኒ ሠራዊት ጋር ተቀላቀሉ።

እናም እንግዲህ ከተማዋን ህዝቡ እንዲጠብቅ ለመርዳት ሞሮኒ ወደ ኔፋውያን ከተማ ሰዎች ተልከዋል ብሎ ገምቶ ነበር፣ እናም ከተማዋን ከእነርሱ እጅ ዳግም ከመውሰድ ይልቅ በላማናውያን እጅ እንዳይገባ መጠበቁ ቀላል መሆኑን በማወቁ ከተማዋን በቀላሉ ይጠብቋታል ብሎ ገምቶ ነበር።

ስለዚህ የያዛቸውን ስፍራዎች ለመጠበቅ ኃይሉን ከእርሱ ጋር አስቀርቶ ነበር።

፲፩ እናም እንግዲህ፣ ሞሮኒ የኔፋውያን ከተማ መወሰዷን በተመለከተ ጊዜ እጅግ አዝኖ ነበር፣ እናም በህዝቡ ክፋት የተነሳ በወንድሞቻቸው እጅ መውደቅ እንደሚገባቸው መጠራጠር ጀመረ።

፲፪ እንግዲህ ዋና ሻምበሎች የነበራቸው ጥርጣሬ ይህ ነበር። እነርሱም በህዝቦች ክፋት ምክንያት ተጠራጠሩና ተደነቁ፣ እናም ይህ የሆነው ላማናውያን በእነርሱ ላይ ድል በማግኘታቸው ነው።

፲፫ እናም እንዲህ ሆነ ሞሮኒ የሀገራቸውን ነፃነት በተመለከተ በመንግስቱ ግዴለሽነት ተቆጥቶ ነበር።