ቅዱሳት መጻህፍት
ሔለማን ፲፪


ምዕራፍ ፲፪

ሰዎች ያልተረጋጉ እናም፣ ሞኞች፣ እንዲሁም ክፋትን ለመስራት የፈጠኑ ናቸው—ጌታ ህዝቡን ይገስጻል—የሰዎች ከንቱነት ከእግዚአብሔር ኃይል ጋር ተነፃፀረ—በፍርድ ቀን ሰዎች የዘለዓለም ህይወትን ወይንም የዘለዓለም ፍርድን ያገኛሉ። በ፮ ም.ዓ. ገደማ።

እናም የሰው ልጆች እንዴት ሀሰተኞች፣ እናም ደግሞ ልባቸው ያልተረጋጋ መሆኑን ለመመልከት እንችላለን፤ አዎን፣ ጌታም እምነታቸውን በእርሱ ላደረጉ መጨረሻ በሌለው ቸርነቱ ሲባርካቸውና፣ ሲያበለፅጋቸው ለመመልከት እንችላለን።

አዎን፣ እናም በመስካቸውም ላይ ከብቶቻቸውንና፣ መንጋዎቻቸውን፣ በወርቃቸውም፣ በብራቸውም፣ እናም ሁሉንም ዓይነት የከበሩ ነገሮቻቸውን በሚያበዛላቸው ህዝቡን እናያለን፤ ህይወታቸውን በማትረፍና፣ ከጠላቶቻቸው እጅ እነርሱን በማስለቀቅም፤ ጠላቶቻቸው በእነርሱ ላይ ጦርነት እንዳያውጁ ልባቸውን በሚያራራበት፤ አዎን፣ እናም በአጠቃላይ ለህዝቡ ደህንነትና ደስታ ሁሉንም ነገሮች በሚያደርግበት ጊዜ፤ አዎን ይህም ልባቸውን የሚያጠጥሩበትና፣ ጌታ አምላካቸውን የሚረሱበት፣ ቅዱስ የሆነውንም በእግራቸው የሚረግጡበት ጊዜ ነው—አዎን፣ ይህም የሆነበት ምክንያት ሰዎቹ ስለተመቻቹ፣ እናም እጅግ በታላቅ ሁኔታ ስለበለፀጉ ነው።

እናም ጌታ ህዝቡን በብዙ ስቃይ ካልገሰጻቸው፤ አዎን፣ በሞትና በፍርሃትና፣ በረሃብ እናም በሁሉም ዓይነት ቸነፈር ካልጎበኛቸው በስተቀር እርሱን እንደማያስታውሱት እናያለን።

አቤቱ የሰው ልጆች እንዴት ሞኞችና፣ ከንቱዎችና፣ ክፉዎች፣ እንዲሁም ዲያብሎስን ተከታዮች፣ እናም እንዴት ኃጢያትን ለመስራት ፈጣንና፣ መልካምን ለማድረግ እንዴት የዘገዩ ናቸው፤ አዎን የዚያን ክፉ የሆነውን ቃላት ለመስማት፣ እናም በዓለም ከንቱ ነገሮች ላይ ልባቸውን ለማድረግ እንዴት ፈጣን ናቸው!

አዎን፣ በኩራት ለመወጠር ምንኛ ፈጣን ናቸው፤ አዎን፣ ለጉራና፣ ክፉ የሆኑትን ነገሮች ሁሉ ለማድረግ ምንኛ ይፈጥናሉ፤ እናም ጌታ አምላካቸውን ለማስታወስና፣ ለምክሮቹ ጆሮአቸውን ለመስጠት እንዴት ይዘገያሉ፣ አዎን በጥበብ ጎዳናስ ለመራመድ እንዴት ያዘግማሉ!

እነሆ፣ እነርሱን የፈጠረው ጌታ አምላካቸው፣ በእነርሱ ላይ እንዲገዛና እንዲነግስ አይፈልጉም፤ ታላቅ ቸርነትና ምህረት በእነርሱ ላይ ቢኖረውም ምክሩን ችላ ይሉታል፤ እናም መሪያቸው እንዲሆን አልፈለጉም።

አቤቱ የሰው ልጆች ከንቱነት እንዴት ታላቅ ነው፣ አዎን ከመሬት ትቢያ እንኳን ያነሱ ናቸው።

እነሆም፣ በታላቁ እና በዘለዓለማዊው አምላካችን ትዕዛዝ የምድር ትቢያ እስከሚከፈል ወዲህና ወዲያ ይንቀሳቀሳል።

አዎን፣ እነሆ በድምጹ ኮረብቶችና፣ እና ተራሮች ይናወጣሉ፣ እናም ይንቀጠቀጣሉ

እናም በድምፁም ኃይል ይሰባበራሉና፣ የተስተካከሉ ይሆናሉ፤ አዎን፣ እንደ ሸለቆም ይሆናሉ።

፲፩ አዎን፣ በድምፁም ኃይል መላዋ ምድር ትንቀጠቀጣለች፤

፲፪ አዎን፣ በድምፁም ኃይል፣ የመሠረት ድንጋዮችም ከመሃላቸው ይናወጣሉ።

፲፫ አዎን፣ እናም ምድርንም ተንቀሳቀሽ ቢላት—ትንቀሳቀሳለች።

፲፬ አዎን፣ ምድሪቱን—ቀኑ ለብዙ ሰዓታት ይረዝም ዘንድ ወደኋላ ተመለሽ ቢላት—ይህም ይሆናል፤

፲፭ እናም እንደ ቃሉ መሰረት ምድር ወደኋላ ትጓዛለች፤ ለሰውም ፀሐይ የቆመች ሆና ትታያለች፤ አዎን፣ እናም እነሆ፣ ይህም እንዲህ ነው፤ በእርግጥም መሬት ትንቀሳቀሳለች እንጂ ፀሐይ አይደለችምና።

፲፮ እናም እነሆ፣ ደግሞ ታላቁ ጥልቅ የሆነውን ውሀምድረቅ ቢለው—ይደርቃል።

፲፯ እነሆ፣ ይህንን ተራራ—ተነስ እናም በከተማዋ ላይ እንድትቀበር ውደቅ ቢለው—እነሆ ይሆናል።

፲፰ እናም እነሆ፣ አንድ ሰው በምድር ውስጥ ሀብቱን ቢቀብርና ጌታ በደበቀው ክፋት የተነሳ የተረገመ ይሁን ቢለው፣ እነሆ፣ የተረገመ ይሆናል።

፲፱ እናም ጌታ—ማንም ሰው ከዚህ ጊዜ ጀምሮ እስከዘላለሙ እንዳያገኝህ የተረገምህ ሁን ቢለው—እነሆ፣ ማንም ሰው ከዚህ ጊዜ ጀምሮ፣ እናም እስከዘላለሙ አያገኘውም።

እናም እነሆ፣ ጌታ አንድን ሰው—በክፋትህ የተነሳ ለዘለዓለም የተረገምህ ትሆናለህ ቢለው—ይህም ይሆናል።

፳፩ እናም ጌታ—በክፋታችሁ የተነሳ ከፊቴ ትለያላችሁ ቢል—እንዲያ እንዲሆን ያደርጋል።

፳፪ እናም ይህን ለሚለው ለእርሱ ወዮለት፤ ምክንያቱም ክፋትን ለሚያደርግ ይሆናል፤ እናም ሊድን አይቻለውም፤ ስለዚህ፣ በዚህም የተነሳ፣ ሰዎች እንዲድኑ ዘንድ፣ ንስሃም ታውጇል።

፳፫ ስለዚህ፣ ንስሃ የገቡ፣ እናም የጌታ የአምላካቸውን ድምፅ የሰሙ የተባረኩ ናቸው፤ የሚድኑትም እነዚህ ናቸውና።

፳፬ እናም እግዚአብሔር በታላቁ ሙላቱ ሰዎች ወደ ንሰሃ እና መልካም ሥራዎች ይመጡ ዘንድ፣ እንደሥራቸውም ከፀጋም ወደ ፀጋ ይመልሳቸው ዘንድ ያድርግላቸው።

፳፭ እናም ሰዎች ሁሉ እንዲድኑ እፈልጋለሁ። ነገር ግን በታላቁ እና በመጨረሻው ቀን የሚጣሉ አዎን፣ ከጌታ ፊት የሚጣሉ፣ ጥቂቶች እንዳሉ አንብበናል፤

፳፮ አዎን፣ እነርሱም መልካም የሚያደርጉ ዘለዓለማዊ ህይወት ይኖራቸዋል፤ እናም ክፉ የሚያደርጉ ለዘለዓለም ይፈረድባችኋል የሚለውን ቃል ለማሟላት ወደ ዘለዓለማዊው ስቃይ ይላካሉ። እናም ይህ ነው። አሜን።