ቅዱሳት መጻህፍት
ሔለማን ፭


ምዕራፍ ፭

ኔፊ፣ እና ሌሂ እራሳቸውን ለስብከት ሰጡ—ስሞቻቸው እንደቅድመ አያቶቻቸው ህይወታቸውን ይመስሉበት ዘንድ ይጋብዛቸዋል—ክርስቶስ ንስሃ የሚገቡትን ያድናል—ኔፊና ሌሂ ብዙዎችን ለወጡ፣ እናም ወደ ወህኒ ተወሰዱና እሳት እነርሱን ከበባቸው—የጨለማው ጭጋግም ሶስት መቶ ሰዎችን ሸፈነ—መሬት ተንቀጠቀጠች፣ እናም ድምፅም ሰዎችን ንስሃ እንዲገቡ አዘዘ—ኔፊና ሌሂ ከመላዕክት ጋር ተነጋገሩ፣ እናም ብዙ ህዝብም በእሳት ተከበበ። በ፴ ም.ዓ. ገደማ።

እናም እንዲህ ሆነ በዚሁ ዓመት፣ እነሆ፣ ኔፊ ሴዞራም ተብሎ ለሚጠራ ሰው የፍርድ ወንበሩን ሰጠ።

ህግጋቶቻቸው፣ እናም መንግስታቸው በህዝቡ ድምፅ በመቋቋሙ፣ እናም መልካምን ከመረጡት ክፉውን የመረጡት ቁጥር ብዙ በመሆኑ ለጥፋት በስለዋል፣ ምክንያቱም ህጎቹ ተበላሽተዋልና።

አዎን እናም ይህ ብቻም አልነበረም፤ ለጥፋታቸው ካልሆነ በቀር በህግም ሆነ በፍትህ መገዛት እስከማይችሉ ድረስ አንገተ ደንዳናዎች ነበሩ።

እናም እንዲህ ሆነ ኔፊ በክፋታቸውም የተነሳ ታከተው፤ እናም የፍርድ ወንበሩን ለቀቀና፣ በቀሩት ቀኖቹ፣ እንዲሁም ደግሞ ወንድሙ ሌሂ በቀሩት ቀኖቹ፣ የእግዚአብሔርን ቃል ለማስተማር ኃላፊነትን ወሰዱ፤

አባታቸው ሔለማን የተናገረውን ቃላት አስታውሰዋልና። እናም እርሱ የተናገራቸው ቃላት እነዚህ ናቸው፥

እነሆ፣ ልጆቼ፣ የእግዚአብሔርን ትዕዛዛት ለመጠበቅ እንድታስታውሱት እፈልጋለሁ፣ እነዚህንም ቃላት ለህዝቡ እንድታውጁ እፈልጋለሁ። እነሆ ከኢየሩሳሌም ምድር ለቀው የወጡትን የመጀመሪያ ወላጆቻችንን ስም ሰጥቻችኋለሁ፤ ይህንን ያደረግሁትም ስማችሁን ስታስቡ እነርሱን ታስታውሱ ዘንድ ነው፤ እናም እነርሱን ስታስታውሱ ስራቸውን ታስታውሱ ዘንድ ነው፣ ስራቸውንም ስታስታውሱ መልካም እንደነበሩ እንዴት እንደተባለና፣ ደግሞ እንደተፃፈ እንድታውቁ ዘንድ ነው።

ስለዚህ፣ ልጆቼ፣ እንደ እነርሱ እንደተባለው እናም እንደተጻፈው ስለእናንተ እንዲባልና ደግሞ እንዲጻፍ መልካም የሆኑትን እንድታደርጉ እፈልጋለሁ።

እናም እንግዲህ ልጆቼ፣ እነሆ ከዚህ የበለጠ እንድታደርጉ የምፈልገው አለኝ፣ ይህ ፍላጎቴም ለመኩራት ብላችሁ እነዚህን ነገሮች አታድርጉ፤ ነገር ግን በሰማይ ለራሳችሁ፣ አዎን ዘለዓለማዊ የሆነ እናም የማይጠፋን የሰማይ ሀብትን ታከማቹ ዘንድ፤ አዎን ለአባቶቻችን ይሰጣሉ ብለን ላለመገመት ምክንያት እንደሌለን አይነት የዘለዓለም ህይወት የተከበረ ስጦታ ይኖራችሁ ዘንድ ይሁን እነዚህን ነገሮች አድርጉ።

አቤቱ ልጆቼ አስታውሱ፣ ንጉስ ቢንያም ለህዝቡ የተናገረውን ቃላት አስታውሱ፣ አዎን፣ በሚመጣው በአዳኙ የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ካልሆነ በቀር የሰው ልጅ ሊድንበት የሚችልበት መንገድም ሆነ ዘዴ የለም፤ አዎን፣ ዓለምን ለማዳን እንደሚመጣም አስታውሱ።

እናም ደግሞ አሙሌቅ በአሞኒሀ ከተማ ለዚኤዝሮም የተናገራቸውን ቃላት አስታውሱ፤ ምክንያቱም እርሱ ጌታ በእርግጥ ህዝቡን ለማዳን እንደሚመጣ ተናግሯልና፤ ነገር ግን ከኃጢአታቸው ሊያድናቸው እንጂ፣ ከነኃጢአታቸው ሊፈውሳቸው አይመጣም።

፲፩ እናም ጌታ በንስሃ የተነሳ ከኃጢአታቸው እንዲያድናቸው ከአብ ስልጣን ተሰጥቶታል፤ ስለዚህ ህዝቡን ወደማዳን ስልጣን እንዲሁም ወደነፍሳቸው ደህንነት የሚያመጣቸውን የንስሃን የምስራች ሁኔታ ለመናገር መላዕክቱን ልኳል

፲፪ እናም አሁን ልጆቼ አስታውሱ፣ አስታውሱ፣ አዳኝ በሆነው የእግዚአብሔር ልጅ በሆነው በክርስቶስ ዓለት መሰረታችሁን መገንባት እንዳለባችሁ፤ ዲያብሎስ ኃይሉን ንፋሱን፣ አዎን፣ በአውሎ ነፋስ እንደሚወረወር ዘንጉን በላከ ጊዜ፣ አዎን በረዶው፣ እናም ኃይለኛው ውሽንፍር በሚመታችሁ ጊዜ፣ እርግጠኛ መሰረት በሆነው ሰዎች ከገነቡበት ሊወድቁበት በማይችሉበት አለት ላይ ስለገነባችሁ እናንተን ወደ ስቃይና ወደባህር ስላጤና መጨረሻ ወደሌለው ዋይታ ጎትቶ ለመጣል ኃይል አይኖረውም።

፲፫ እናም እንዲህ ሆነ እነዚህ ቃላትን ነበር ሔለማን ለልጆቹ ያስተማራቸው፤ አዎን፣ ብዙ ያልተፃፉ ነገሮችንም እናም ደግሞ ብዙ የተፃፉ ነገሮችንም አስተምሯቸዋል።

፲፬ እናም ቃላቱን አስታውሰዋል፤ እናም ስለዚህ የእግዚአብሔርን ትዕዛዛት በመጠበቅ ከለጋስ ከተማ በመጀመር በኔፊ ህዝብ ሁሉ መካከል የእግዚአብሔርን ቃል ለማስተማር ተጓዙ።

፲፭ እናም ከዚያን በኋላ ወደ ጊድ ከተማና፣ ከጊድ ከተማ ወደ ሙሌቅ ከተማ ሄዱ፤

፲፮ እናም በምድሪቱ በስተደቡብ በኩል ከነበሩት ከኔፊ ሰዎች ጋር እስከሚጓዙ ድረስ ከአንዱ ከተማ ወደ ሌላኛው ሄዱ፤ እናም ከዚያ ከላማናውያን መካከል ወደ ዛራሔምላ ምድር ተጓዙ።

፲፯ እናም እንዲህ ሆነ ከኔፋውያን የተገነጠሉትን ብዙዎች እስከሚያሳፍሩ፣ ኃጢአታቸውን በመናዘዝ ለንስሃ እስከሚጠመቁ፣ እናም የሰሩትን ስህተት ለማረም ጥረት በማድረግ ወደ ኔፋውያን በፍጥነት እስከሚመለሱ ድረስ በታላቅ ኃይል ሰብከውላቸው ነበር።

፲፰ እናም እንዲህ ሆነ ኔፊና ሌሂ ይናገሩ ዘንድ ኃይልና ስልጣን ስለተሰጣቸው፣ እናም ደግሞ ምን መናገር እንዳለባቸው ስለተሰጣቸው በታላቅ ኃይልና ስልጣን ለላማናውያን ሰበኩ—

፲፱ ስለዚህ በዛራሔምላ ምድር እንዲሁም በዙሪያው የነበሩት ስምንት ሺህ ላማናውያን ለንስሃ እስከሚጠመቁ፣ እናም የአባቶቻቸው ወግ ኃጢያት መሆኑን እስከሚያምኑ ድረስ ላማናውያኑም እጅግ እስኪገረሙ ይናገሩ ነበር።

እናም እንዲህ ሆነ ኔፊና ሌሂ ከዚያ ቦታ ወደ ኔፊ ምድር ለመሄድ ጉዞአቸውን ቀጠሉ።

፳፩ እናም እንዲህ ሆነ እነርሱም በላማናውያን ወታደሮች ተወሰዱና፣ ወህኒ ቤት፣ አዎን አሞንና ወንድሞቹ በሊምሂ አገልጋዮች ተጥለውበት በነበረው በዚሁ ወህኒ ቤት ተጣሉ።

፳፪ እናም ለብዙ ቀናት ያለምግብ በወህኒ ቤት ከተጣሉ በኋላ፣ እነሆ ይገድሉአቸው ዘንድ እነርሱን ለማውጣት ወደ ወህኒ ቤቱ ሄዱ።

፳፫ እናም እንዲህ ሆነ እንቃጠላለን በማለት እጃቸውን በእነርሱ ላይ ለማሳረፍ እስከሚፈሩ እንኳን ኔፊና ሌሂ እሳት በሚመስል ነገር ተከበው ነበር። ይሁን እንጂ፣ ኔፊና ሌሂ አልተቃጠሉም ነበር፤ ልክ በእሳት መካከል የቆሙ ይመስሉ ነበር እናም አልተቃጠሉም ነበር።

፳፬ እናም በእሳት አምድ መከበባቸውን እናም እንደማይቃጠሉ በተመለከቱ ጊዜ፣ ልባቸው ተበረታታ።

፳፭ ላማናውያን እጃቸውን ለመጫን እንዳልደፈሩ ተመለከቱ፤ አጠገባቸው ለመቅረብም አልደፈሩም፤ ነገር ግን ተደንቀው ዲዳ የሆኑ በመምሰል ቆሙ።

፳፮ እናም እንዲህ ሆነ ኔፊና ሌሂ ቆሙ፣ እናም ለእነርሱም እንዲህ በማለት መናገር ጀመሩ፥ አትፍሩ፣ እነሆም እኛን ለመግደል እጃችሁን በእኛ ላይ ማድረግ እንደማትችሉ የምታዩትን ይህን አስገራሚ ነገር የሚያሳያችሁ እግዚአብሔር ነው።

፳፯ እናም እነሆ ይህንን ቃላት በተናገሩ ጊዜ መሬቱ በኃይል ተንቀጠቀጠ፤ እናም የወህኒ ቤቱ ግድግዳ በመሬት ላይ የተንከባለለ እስከሚመስል ድረስ ተንቀጠቀጠ፤ ነገር ግን እነሆ አልወደቁም። እናም እነሆ በወህኒ ቤት ውስጥ የነበሩት ላማናውያንና ተገንጥለው የነበሩት ኔፋውያን ነበሩ።

፳፰ እናም እንዲህ ሆነ በደመና ጭጋግም ተሸፈኑ፤ እናም አሰቃቂ የሆነ ከባድ ፍርሃት በእነርሱ ላይ መጣ።

፳፱ እናም እንዲህ ሆነ በደመናው ጭጋግ ከበላይ በኩል በሚመስል ሁኔታ ድምፅ እንዲህ ሲል መጣ፥ ንስሃ ግቡ፣ ንስሃ ግቡ፤ እናም መልካም ዜናን ለእናንተ እንዲናገሩ የላኳቸውን አገልጋዮቼን ለማጥፋት ከእንግዲህ አትሹ።

እናም እንዲህ ሆነ ይህንን ድምፅ በሰሙ ጊዜና፣ የመብረቅ ድምፅ አለመሆኑን፣ ታላቅ የሁካታም ጫጫታ ድምፅ አለመሆኑን ተመለከቱ፤ ነገር ግን እነሆ ፍፁም የሆነ እርጋታ ያለው ለስላሳ ድምፅ ነበር፤ ልክ እንደሹክሹክታ፣ እናም ነፍስንም እንኳን የሚወጋ ነበር—

፴፩ እናም ድምፁ ለስላሳ ቢሆንም፣ እነሆ መሬቱ በኃይል ተንቀጠቀጠ፤ የወህኒ ቤቱ ግድግዳ ወደመሬት የሚወድቅ በመምሰል በድጋሚ ተንቀጠቀጠ፤ እናም እነሆ እነርሱን የሸፈናቸው የደመናም ጭጋግ አልተበተነም ነበር—

፴፪ እናም እነሆ ድምፅ በድጋሚ እንዲህ ሲል መጣ፥ ንስሃ ግቡ፣ ንስሃ ግቡ መንግስተ ሰማያት ቀርባለችና፤ እናም ከእንግዲህ አገልጋዮቼን ለማጥፋት አትሞክሩ። እናም እንዲህ ሆነ መሬት በድጋሚ ተንቀጠቀጠችና፣ ግድግዳው ተናወጠ።

፴፫ እናም ደግሞ ለሶስተኛ ጊዜ በድጋሚ ድምፅ መጣና፣ በሰው ሊነገሩ የማይችሉ አስደናቂ ቃላት ተናገረ፤ እናም ግድግዳው በድጋሚ ተንቀጠቀጠና ምድር ተሰነጣጥቃ የተከፈለች እስከሚመስል ድረስ ተናወጠች።

፴፬ እናም እንዲህ ሆነ የደመናው ጭጋግ ስለሸፈናቸው ላማናውያን ለመሸሽ አልቻሉም፤ አዎን እናም ደግሞ በላያቸው ላይ በመጣው ፍርሃት የተነሳ አይንቀሳቀሱም ነበር።

፴፭ እንግዲህ ከኔፋውያን የተወለደ፣ በአንድ ወቅት በእግዚአብሔር ቤተክርስቲያን አባል የነበረ ነገር ግን ተለይቶ የሄደ አንድ ሰው በመካከላቸው ነበር።

፴፮ እናም እንዲህ ሆነ በሌላ አቅጣጫ ዞረና፣ እነሆ በደመናው ጭጋግ ውስጥ የኔፊንና የሌሂን ፊት ተመለከተ፤ እናም እነሆ ፊታቸውም ልክ እንደመላዕክት እጅግ ያበራ ነበር። ወደሰማይ ሲመለከቱም ተመለከታቸው፤ እናም ወደሚመለከቱት ፍጡር ድምፃቸውን ከፍ እንደሚያደርጉ ወይም እንደሚነጋገሩ ዓይነት መስለዋል።

፴፯ እናም እንዲህ ሆነ ይህ ሰው ይመለከቱ ዘንድ ወደ ህዝቡ ጮኸ። እናም እነሆ ለመዞርና ለመመልከት ሀይል ስለተሰጣቸው ዞሩና ተመለከቱ፤ እናም የኔፊንና የሌሂን ፊት ተመለከቱ።

፴፰ እናም ለሰውየውም እንዲህ አሉ፥ እነሆ ይህ ሁሉ ነገር ምን ማለት ነው፣ እናስ እነዚህ ሰዎች የሚነጋገሩት ከማን ጋር ነው?

፴፱ እንግዲህ የሰውየው ስም አሚናዳብ ይባል ነበር። እናም አሚናዳብ እንዲህ ሲል ተናገራቸው፥ እነርሱ ከእግዚአብሔር መላእክት ጋር ይነጋገራሉ።

እናም እንዲህ ሆነ ላማናውያን እንዲህ አሉት፥ ይህ የጨለማው ጭጋግ እኛን ከመሸፈን ይወገድ ዘንድ ምን እናድርግ?

፵፩ እናም አሚናዳብ እንዲህ አላቸው፥ አልማና፣ አሙሌቅ፣ እናም ዚኤዝሮም ባስተማሯችሁ በክርስቶስም እምነት እስከሚኖራችሁ ድረስ ድምፃችሁን በማንሳት ንስሃ መግባት እንዲሁም ማልቀስ ይገባችኋል፤ እናም ይህንን በምታደርጉበት ጊዜ የሸፈናችሁ የጨለማ ጭጋግ ይወገድላችኋል።

፵፪ እናም እንዲህ ሆነ ምድርን በማንቀጥቀጥ ወዳናወጠው ድምፅ ሁሉም መጮህ ጀመሩ፤ አዎን የደመናው ጭጋግ እስከሚበታተን ድረስም ጮኹ።

፵፫ እናም እንዲህ ሆነ አይኖቻቸውን ወዲህና ወዲያ አዞሩ፣ እናም የደመናው ጭጋግ ለቋቸው መሄዱን ተመለከቱ፣ እነሆ እነርሱ፣ አዎን፣ እያንዳንዱ ነፍስ በእሳቱ አምድ መከበቡን ተመለከተ።

፵፬ እናም ኔፊና ሌሂ በላማናውያን መካከል ነበሩ፤ አዎን ተከበው ነበር፤ አዎን፣ ልክ በሚነድ ነበልባል መካከል እንዳሉ ነበር፤ ይሁን እንጂ እነርሱን የሚጎዳም ሆነ የወህኒ ቤቱን ግድግዳ የሚያቃጥል አልነበረም፤ እናም ለመናገር በሚያዳግት እንዲሁም በክብር በተሞላ ደስታ ተሞልተው ነበር።

፵፭ እናም እነሆ፣ የእግዚአብሔር ቅዱስ መንፈስ ከሰማይ መጣና፣ ወደ ልባቸው ገባ፣ እናም በእሳት የተሞሉ ይመስል ነበር፣ አስደናቂ ቃላትንም መናገር ይችሉ ነበር።

፵፮ እናም እንዲህ ሆነ አንድ ድምፅ፣ አዎን የሚያምር ድምፅ፣ ልክ እንደሹክሹክታ እንዲህ ሲል መጣ፥

፵፯ ከዓለም መፈጠር ጀምሮ በነበረው በተወዳጄ ባላችሁ እምነት ምክንያት ሰላም፣ ሰላም ለእናንተ ይሁን።

፵፰ እናም እንግዲህ ይህንን በሰሙ ጊዜ ድምፁ ከመጣበት ቦታ ለመመልከት ዐይናቸውን ወደ ላይ አነሱ፤ እናም እነሆ ሰማይ ሲከፈት ተመለከቱ፤ መላዕክትም ከሰማይ መጡና አገለገሏቸው።

፵፱ እናም እነዚህን ነገሮች ያዩና የሰሙ ወደ ሶስት መቶ የሚጠጉ ነፍሳት ነበሩ፤ እናም እንዲሄዱና፣ እንዳይገረሙ፣ እናም እንዳይጠራጠሩ ታዘዙ።

እናም እንዲህ ሆነ እነርሱም ሄዱ፤ እናም ለህዝቡ ተናገሩ፣ በምድሪቱም ዙሪያ ሁሉ ባጠቃላይ ስለተመለከቱት እንዲሁም ስለአዩአቸው ነገሮች በሙሉ ተናገሩ፤ የተቀበሉት መረጃ ታላቅ በመሆኑ ብዙዎች ላማናውያን በእነርሱ ተቀይረው ነበር።

፶፩ እናም ብዙዎች ያመኑትም የጦር መሳሪያዎቻቸውንና፣ ደግሞ ጥላቻቸውንና የአባቶቻቸውን ወግ ተዉ።

፶፪ እናም እንዲህ ሆነ ላማናውያን ለኔፋውያን ምድራቸውን ተዉላቸው።