መፅሐፈ ሞርሞን ከመፅሐፍ ቅዱስ ጋር የሚመሳሰል ቅዱስ መፅሐፍ ነው። እግዚአብሔር በጥንት በአሜሪካ ከኖሩት ህዝቦች ጋር ያደረጋቸው ነገሮች መዝገብ ነው፣ እናም ዘለዓለማዊ የሆነውን የወንጌል ሙላት የያዘ ነው።

መጽሐፉ በብዙ ጥንታዊ ነቢያት በትንቢትና በራዕይ መንፈስ የተፃፈ ነበር። በወርቅ ሰሌዳ ላይ የተፃፉት ቃላቶቻቸው፣ ሞርሞን በተባለ ታሪካዊ ነቢይ የተጠቀሱና ያጠሩ ነበሩ። መዝገቡ ስለ ሁለት ታላላቅ ስልጣኔዎች ይዘግባል። አንደኛው በ፮፻ ም.ዓ. ከኢየሩሳሌም መጣ እና በኋላም ኔፋውያን እና ላማናውያን ወደሚባሉት ሁለት ሀገሮች ተከፈለ። ሌላኛው ይበልጥ ቀድሞ የመጣው ጌታ በባቢሎን ግንብ የህዝቡን ቋንቋ በቀላቀለበት ጊዜ ነው። ይህ ወገን ያሬዳውያን ይባላል። ከሺህ ዓመታት በኋላ፣ ከላማናውያን በስተቀር ሁሉም ጠፉ፣ እናም እነርሱ ከአሜሪካ ሕንዶች ቅድመ አያቶች መካከል አንዳንዶቹ ናቸው።

በመፅሐፈ ሞርሞን ውስጥ የተመዘገበው ታላቁ ድርጊት ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ከሞት እንደተነሳ በኔፋውያን መካከል ያደረገው የግል አገልግሎት ነው። የወንጌልን ትምህርት ይገልፃል፣ የደህንነትን ዕቅድ ይዘረዝራል፣ እናም በዚህ ህይወት ሰላምን እንዲሁም በሚመጣው ህይወት ዘለዓለማዊ ደህንነትን ለማግኘት ሰዎች ምን ማድረግ እንዳለባቸው ይናገራል።

ሞርሞን ጽሑፉን ካጠናቀቀ በኋላ፣ መዝገቡን ለወንድ ልጁ ለሞሮኒ ሰጠው፤ እርሱም ከራሱ ትንሽ ቃላት በመጨመር በከሞራ ኮረብታ ውስጥ ሰሌዳዎቹን ደበቀ። መስከረም ፳፩፣ ፲፰፻፳፫ (እ.አ.አ.)፣ ይኸው የከበረው ሞሮኒ፣ ከሞት የተነሳው ሰው፣ ለነቢዩ ጆሴፍ ስሚዝ ታየው፣ እናም ስለጥንታዊው መዝገብ እናም ወደ እንግሊዝኛ ቋንቋ መተርጎም ስላለው እጣ ፈንታ አስተማረው።

በመጨረሻም ሰሌዳዎቹ በእግዚአብሔር ኃይልና ስጦታ ለተረጎማቸው ለጆሴፍ ስሚዝ ተሰጡ። መዝገቡ አሁን ኢየሱስ ክርስቶስ የህያው እግዚአብሔር ልጅ ለመሆኑ እንደ አዲስና ተጨማሪ ምስክርነት፣ እናም፤ ወደ እርሱ የሚመጡና የወንጌሉን ህግጋትና ስርዓቶች የሚቀበሉ ሁሉ ይድኑ ዘንድ በብዙ ቋንቋዎች እየተተረጎመ ነው።

ይህንን መዝገብ በተመለከተ ነቢዩ ጆሴፍ ስሚዝ እንዲህ ብሏል፥ “ለወንድሞች መፅሐፈ ሞርሞን በምድር ካሉ መፅሐፍት በሙሉ የበለጠ ትክክል እንደሆነ፣ እናም የኃይማኖታችን የማዕዘን ድንጋይ እንደሆነ፣ እናም ከየትኛውም መፅሐፍ በበለጠ በውስጡ ባሉት አዕምሮአዊ ትእዛዝ በመኖር ሰው ወደ እግዚአብሔር ሊቀርብ ይችላል ብዬ ነገርኳቸው።”

ከጆሴፍ ስሚዝ በተጨማሪ፣ ጌታ ለራሳቸው የወርቅ ሰሌዳዎቹን እንዲያዩና የመፅሐፈ ሞርሞን እውነተኛነትና መለኮታዊነት ልዩ ምስክር እንዲሆኑ ሌሎች አስራ አንድን መረጠ። የእነዚህ ሰዎች የጽሑፍ ምስክርነት “የሶስቱ ምስክሮች ምስክርነት” እና “የስምንቱ ምስክሮች ምስክርነት” ተብሎ በዚህ መፅሐፍ ውስጥ ተጨምረው ይገኛሉ።

እኛ ሁሉንም ሰዎች በሁሉም ቦታ መፅሐፈ ሞርሞንን እንዲያነቡት፣ የያዘውን መልዕክት በልባቸው እንዲያሰላስሉት፣ እናም ዘለዓለማዊውን አባት እግዚአብሔርን በክርስቶስ ስም ይህ መፅሐፍ እውነት እንደሆነ እንዲጠይቁት እንጋብዛለን። ይህን ምክር የሚከተሉ እናም በእምነት የሚጠይቁ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል አማካኝነት የእውነተኛነቱን እንዲሁም የመለኮታዊነቱን ምስክር ያገኛሉ። (ሞሮኒ ፲፥፫–፭ን ተመልከቱ።)

ይህንን መለኮታዊ ምስክርነት ከመንፈስ ቅዱስ የተቀበሉ በዚሁ ኃይል ደግሞ ኢየሱስ ክርስቶስ የዓለም አዳኝ እንደሆነ፣ ጆሴፍ ስሚዝ የእርሱ ገላጭ እና በእነዚህ በኋለኛው ዘመናት ነቢይ እንደሆነ፣ እና ለመሲሁ ዳግም ምፅዓት መዘጋጃም፣ የኋለኛው ቀን ቅዱሳን የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን የጌታ መንግስት እንደገና በምድር ላይ የተቋቋመችበት እንደሆነ ያውቃሉ።