ቅዱሳት መጻህፍት
ሞርሞን ፭


ምዕራፍ ፭

ሞርሞን የኔፊን ሠራዊት በድጋሚ የደም መፋሰስና ዕልቂት ወዳለበት ውጊያ መራቸው—መፅሐፈ ሞርሞን ኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑን ለእስራኤል ሁሉ ለማሳመን ይመጣል—ላማናውያን ባለማመናቸው ይበተናሉ፣ እናም መንፈስም ከእነርሱ ጋር መሆኑን ያቆማል—በኋለኛው ቀን ከአህዛብ ወንጌልን ይቀበላሉ። ከ፫፻፸፭–፫፻፹፬ ዓ.ም. ገደማ።

እናም እንዲህ ሆነ ከኔፋውያን መካከል ሔድኩና፣ እነርሱን ከእንግዲህ አልረዳቸውም ብዬ ለገባሁት መሃላ ንሰሃ ገባሁ፤ እናም በድጋሚም በወታደሮቻቸው ላይ ስልጣን ሰጡኝ ምክንያቱም እኔ ከስቃያቸው ለማስለቀቅ የምችል አድርገው ይገምቱ ስለነበር ነው።

ነገር ግን እነሆ፣ ተስፋ አልነበረኝም፣ ምክንያቱም የጌታ ቅጣት በእነርሱ ላይ እንደሚመጣ አውቅ ነበርና፤ እነርሱ ስለኃጢአቶቻቸው ንሰሃ አልገቡምና፣ ነገር ግን ወደ ፈጣሪያቸው ፀሎት ሳያደርጉ ለህይወታቸው ይታገሉ ነበርና።

እናም እንዲህ ሆነ ላማናውያን እኛ ወደ ዮርዳኖስ ከተማ ስንሸሽ በእኛ ላይ መጡብን፤ ነገር ግን እነሆ፣ ስለተሸነፉ በዚያን ጊዜ ከተማዋን የራሳቸው አላደረጉም።

እናም እንዲህ ሆነ በድጋሚ መጡብን፣ እኛም ከተማዋን ተቆጣጥረን ነበር። እናም ደግሞ በኔፋውያን ተይዘው የነበሩ ሌሎች ከተሞች፣ የምድራችንን ነዋሪዎች ለማጥፋት ከእኛ በፊት የነበሩትን ስፍራዎች ለመያዝ የማያስችሏቸው ጠንካራ ምሽጎች ነበሩ።

ነገር ግን እንዲህ ሆነ ባለፍንበት ምድር ሁሉና፣ ያልተሰባሰቡት ነዋሪዎች በላማናውያን ጠፉ፣ እናም ከተሞቻቸውና መንደሮቻቸው በእሳት ተቃጠሉ፤ እናም ሦስት መቶ ሰባ ዘጠኝ ዓመት በዚህ አለፈ።

እናም እንዲህ ሆነ በሦስት መቶ ሰማንያኛው ዓመት፣ ላማናውያን በድጋሚ ሊዋጉን መጡ፣ እኛም በድፍረት ተቋቋምናቸው፤ ነገር ግን ይህ ሁሉ ከንቱ ነበር፣ ምክንያቱም በቁጥር እጅግ ብዙ ስለነበሩ የኔፋውያን ህዝቦች በእግራቸው ሥር ረጋገጡአቸው።

እናም እንዲህ ሆነ በድጋሚ ሸሸንና፣ ሽሽታቸው ከላማናውያን ፈጣን የነበሩት አመለጡና፣ ከላማናውያን ሸሽተው ሊያመልጡ ያልቻሉት ተጠረጉና ጠፉ።

እናም እንግዲህ እነሆ፣ እኔ ሞርሞን፣ የሰዎች ነፍስ በፊቴ እንደነበረው በዐይኔ እንደተመለከትኩት አሰቃቂ የሆነ የደም መፋሰስና ዕልቂት ዓይነት ስቃይ እንዲጣል አልፈልግም፤ ነገር ግን እነዚህ ነገሮች በእርግጥ እንዲታወቁ መደረጉንና፣ የተደበቁት ሁሉም ነገሮች በሰገነት መገለጥ እንዳለባቸው በማወቅ፣

እናም ደግሞ የዚህ ህዝብ ቅሪት የሆኑትና ደግሞ ጌታ ይበትኗቸዋል ብሎ የተናገራቸው፣ እናም ይህም ህዝብ በመካከላቸው ዋጋ እንደሌላቸው እንደሚቆረጡ ጌታ የተናገረባቸው አህዛብ እነዚህን ነገሮች ማወቅ እንዳለባቸው ስለማውቅ—ስለዚህ በተቀበልኩት ትዕዛዝ ምክንያትና፣ ደግሞ በዚህ ህዝብ ክፋትም ታላቅ ሀዘን እንዳይኖራቸው፣ ስላየኋቸው ነገሮች በሙሉ ለመፃፍ ባለመድፈሬ ትንሽ ታሪክ አሳጥሬ እፅፋለሁ።

እናም አሁን እነሆ፣ ይህን ለዘራቸውና፣ ደግሞ የእስራኤል ቤት ለሚንከባከቧቸውና በረከታቸውን ስለሚገነዘቡት እናም ከየት እንደሚመጣ ለሚያውቁትም አህዛብም እናገራለሁ።

፲፩ እንደነዚህ አይነቶች በእስራኤል ቤት መቅሰፍት እንደሚያዝኑ አውቃለሁና፤ አዎን፣ በዚህ ህዝብ መጥፋትም ያዝናሉ፤ ህዝቡም በኢየሱስ ተቀባይነትን ያገኙ ዘንድ ንሰሃ ባለመግባታቸውም ያዝናሉ።

፲፪ እንግዲህ እነዚህ ነገሮች የያዕቆብ ቤት ቅሪት ለሆኑት የተፃፉ ናቸው፤ እናም በዚህም ስርዓት የተጻፈው ክፋት ወደእነርሱ ወደፊት እንደማያመጣቸው በእግዚአብሔር በመታወቁ ነው፤ እናም በራሱ ጊዜ ይገለጡ ዘንድ በጌታም ተደብቀዋል

፲፫ እናም ይህ እኔ የተቀበልኩት ትዕዛዝ ነው፤ እናም እነሆ ጌታ በጥበቡ ተስማሚነቱን በተመለከተ ጊዜ በጌታ ትዕዛዝ መሰረት ይመጣሉ።

፲፬ እናም እነሆ፣ ከአይሁዶች መካከል ወደማያምኑት ይሄዳሉ፤ ለዚህ ዓላማም ይሄዳሉ—ኢየሱስ ክርስቶስ፣ የህያው እግዚአብሔር ልጅ መሆኑን ለማሳመን፤ አብም ቃል ኪዳኑ ይፈፀም ዘንድ አይሁዶችን እንዲሁም የእስራኤል ቤት የሆኑትን በሙሉ ጌታ አምላካቸው ወደሰጣቸው ወደ ትውልድ ምድራቸው ለመመለስ ታላቅና ዘላለማዊ ዓላማውን በሚወደው በልጁ አማካይነት እንደሚያመጣ ለማሳመን፤

፲፭ እናም ደግሞ የዚህ ህዝብ ዘር የሆኑትም ከአህዛብ የሚሄድላቸውን ወንጌሉን ይበልጥ እንዲያምኑ ዘንድ፤ ምክንያቱም ይህ ህዝብ ይበተናል፣ እናም ጨለማ፣ የጎደፈ፣ እናም ከመካከላችን ከነበረው ነገር በላይ፣ አዎን፣ በላማናውያን መካከል ከነበረው የበለጠ ለመግለፅ በማያስችል ሁኔታ የሚያስጠሉ ይሆናሉና፤ እናም ይህም የሆነው ባለማመናቸውና ጣዖት አምላኪ በመሆናቸው ነው።

፲፮ እነሆም፣ የጌታ መንፈስ ከአባቶቻቸው ጋር መስራቱን አቁሟል፤ እናም በዓለም ውስጥ ያለክርስቶስና ያለእግዚአብሔር ናቸውና፤ እናም ገለባ በነፋስ ፊት እንደሚሆነው ይበተናሉና።

፲፯ በአንድ ወቅት አስደሳች ሰዎች ነበሩ፣ እንዲሁም ክርስቶስም እረኛቸው ነበር፤ አዎን፣ በእግዚአብሔር አብም እንኳን ተመርተው ነበር።

፲፰ ነገር ግን አሁንም እነሆ፣ ገለባ በነፋስ ፊት እንደሚወሰደው ወይም ሸራ እናም መሃለቁ ሳይኖራት ወይም ቀጽዘፊም እንደሌሉባት በሞገድ እንደምትናወጥ ጀልባ እነርሱም በሰይጣን ተመርተዋል፤ እናም እርሷም እንደዚህ እንደሆነች፣ እነርሱም ናቸው።

፲፱ እናም እነሆ፣ ጌታም በምድሪቷ ለመቀበል የሚችሉትን በረከት አስቀምጦላቸዋል፣ አህዛብም ምድሪቱን ይዘዋታልና።

ነገር ግን እነሆ፣ እነርሱም በአህዛብ ይባረራሉና ይበተናሉ፤ እናም በአህዛብ ከተባረሩና ከተበተኑ በኋላ፣ እነሆ፣ ጌታ ከአብርሃም እንዲሁም ከእስራኤል ቤት በሙሉ ጋር የገባውን ቃል ኪዳን ያስታውሳል

፳፩ እናም ደግሞ ጌታ በፊቱ ለእነርሱ የተቀመጠለትን የፃድቃኖች ፀሎት ያስታውሳል።

፳፪ እና እንግዲህ አህዛብ ሆይ፣ ንሰሃ ካልገባችሁና ክፉ ስራችሁን ካልተዋችሁ በቀር በእግዚአብሔር ኃይል በፊቱ እንዴት ለመቆም ትችላላችሁ?

፳፫ በእግዚአብሔር እጅ መሆናችሁን አታውቁምን? ስልጣን ሁሉ የእርሱ መሆኑንና በታላቅ ትዕዛዙም ምድር በአንድነት እንደ መጽሐፍ ጥቅልል የምትጠቀለል መሆኗን አታውቁምን?

፳፬ ስለዚህ፣ እናንተ ንሰሃ ግቡ፣ እናም በፊቱም ራሳችሁን አዋርዱ፣ ያለበለዚያ ፍርዱ በላያችሁ እንዳይመጣባችሁ—ያለበለዚያ የያዕቆብ ዘር ቅሪት የሆኑት በመካከላችሁ እንደአንበሳ ይመጣሉ፣ እናም ይበጫጭቋችኋልና፣ ሊያድን የሚችል አይኖርም።