ቅዱሳት መጻህፍት
ሞርሞን ፯


ምዕራፍ ፯

ሞርሞን የኋለኛው ዘመን ላማናውያን በክርስቶስ እንዲያምኑ፤ ወንጌሉን እንዲቀበሉ እናም እንዲድኑ አጥብቆ ጋበዛቸው—መጽሐፍ ቅዱስን የሚያምኑ ሁሉ መፅሐፈ ሞርሞንን እንዲሁ ያምናሉ። በ፫፻፹፭ ዓ.ም. ገደማ።

እናም አሁን፣ እነሆ፣ የአባቶቻቸውን ነገሮች ያውቁ ዘንድ እግዚአብሔር ቃሌን ከሰጣቸው፣ ለነዚህ ለተረፉት የዚህ ሕዝብ ቅሪት ለሆኑት ጥቂት እናገራለሁ፤ አዎን፣ የእስራኤል ቤት ቅሪት ለሆናችሁ ለእናንተ እናገራለሁ፤ እናም የምናገራቸው ቃላት እነዚህ ናቸው፥

እናንተ ከእስራኤል ቤት መሆናችሁን እወቁ።

ንሰሃ መግባት እንዳለባችሁ፣ አለበለዚያ ለመዳን እንደማትችሉ እወቁ።

የጦር መሳሪያዎቻችሁን መጣል እንዳለባችሁ እወቁ፣ እናም ከእንግዲህ በደም መፍሰስ በምንም አትደሰቱ፣ እናም ከእንግዲህ እግዚአብሔር ካላዘዛችሁ በስተቀር የጦር መሳሪያዎቻችሁን በድጋሚ አታንሱ።

አባቶቻችሁ ያወቁትን ለማወቅና፣ እናም ለኃጢአቶቻችሁ ሁሉና ለክፋቶቻችሁ ንሰሃ መግባት እንዳለባችሁ፣ እናም በአይሁዶች የተገደለው ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑንና፣ እርሱም በአብ ኃይል ዳግም እንደተነሳ፣ ስለዚህ በመቃብር ላይ ድል እንዳደረገ ማመን እንዳለባችሁ እወቁ፣ እናም ደግሞ በእርሱም የሞት መውጊያ ተውጣለች።

እናም እርሱም ሰውም በፍርድ ወንበር ፊት ለመቆም የሚነሳበትን የሙታንን ትንሣኤ ያመጣል።

እናም በእርሱም ፊት በፍርድ ቀን ጥፋተኛ ሳይሆን የሚገኝ፣ አንድ አምላክ የሆኑትን፣ አብ፣ እናም ወልድ፣ እናም መንፈስ ቅዱስን መጨረሻ በሌለው ደስታ ያለማቋረጥ ከበላይ ዘማሪዎች ጋር ለማወደስ በእግዚአብሔር መንግስት በፊቱ እንዲኖር የሚሰጥበትን ለዓለም ቤዛነትን አምጥቷል።

ስለዚህ ንሰሃ ግቡና፣ በኢየሱስ ስም ተጠመቁ፣ እናም በዚህ መዝገብ ብቻ ሳይሆን ነገር ግን ከአይሁዶች ለአህዛብ የሚመጣውን መዝገብ ውስጥ የተመሰረተውን የክርስቶስን ወንጌል በጥብቅ ያዙ፣ ይህም መዝገብ ከአህዛብ ለእናንተ ይመጣል።

እነሆም፣ ይህም እናንተ እንድታምኑበት ነው የተፃፈው፤ እናም ያንን የምታምኑት ከሆነ፣ ይህንንም ደግሞ ታምናላችሁ፤ እናም ይህንን የምታምኑ ከሆነ ስለአባቶቻችሁና፣ ደግሞ በእግዚአብሔር አማካኝነት በመካከላቸው የተሰራውን ድንቅ ሥራዎች ጭምር ታውቃላችሁ።

እናም ደግሞ የያዕቆብ ዘር ቅሪት መሆናችሁን ታውቃላችሁ፤ ስለዚህ ከመጀመሪያዎቹ የቃል ኪዳን ህዝቦች ጋር ተቆጥራችኋል፣ እናም በክርስቶስ የምታምኑ ከሆነ፣ እናም እርሱ በሰጠው ትእዛዝ መሰረት፣ የአዳኛችንን ምሳሌ በመከተል መጀመሪያ በውኃ በኋላም በእሳትና በመንፈስ ቅዱስ የምትጠመቁ ከሆነ በፍርድ ቀን ለእናንተ መልካም ይሆንላችኋል። አሜን።