ቅዱሳት መጻህፍት
ሞዛያ ፲፩


ምዕራፍ ፲፩

ንጉስ ኖህ በክፋት ገዛ—ከሚስቶቹና ከዕቁባቶቹ ጋር በቀበጠ ብልሹ አኗኗር ፈነጠዘ—አቢናዲ ህዝቡ ለባርነት እንደሚወሰድ ተነበየ—ንጉስ ኖህ ህይወቱን ሊያጠፋ ፈለገ። ከ፻፷–፻፶ ም.ዓ. ገደማ።

እናም አሁን እንዲህ ሆነ ዜኒፍ ከልጆቹ አንዱ ለሆነው ለኖህ መንግስቱን ሰጠው፤ ስለሆነም ኖህ በእርሱ ቦታ መንገስ ጀመረ፤ እናም በአባቱ መንገድ አልተራመደም ነበር።

እነሆም፣ የጌታን ትዕዛዛት አልጠበቀም ነበር፣ ነገር ግን በልቡ ፍላጎት ይራመድ ነበር። እናም ብዙ ሚስቶችና ዕቁባቶች ነበሩት። እናም ህዝቡም ኃጢያትን እንዲፈፅሙና፣ በጌታ ፊት ርኩስ የሆነውን እንዲሰሩ አደረገ። አዎን፣ እናም ዝሙትንና ሁሉንም ዓይነት ኃጢአቶችን ፈፀሙ።

ባላቸው ንብረት ላይ ሁሉ፣ አንድ አምስተኛ ከወርቃቸውና፣ ከብራቸው፣ እናም አንድ አምስተኛ ከዚፋቸው፣ ከመዳባቸውም፣ ከነሃሳቸውና ከብረታቸውም፣ እናም ከሰቡ ጠቦቶቻቸው አንድ አምስተኛው፣ ደግሞም ከእህላቸው ሁሉ አንድ አምስተኛው ላይ ቀረጥ መደበባቸው።

እናም እነዚህን በሙሉ የወሰደው ሚስቶቹንና፣ ዕቁባቶቹን፣ ደግሞም ካህናቱን፣ እንዲሁም የእነርሱን ሚስቶችና ዕቁባቶችን ለመርዳት ነበር፤ እንደዚህም የመንግስቱንም ጉዳዮች ለወጣቸው።

በአባቱ የተሾሙትን ካህናት ሁሉ ሻራቸው፣ እናም በልባቸው ኩራት ያበጡትን አዳዲሶች በምትካቸው ሾማቸው።

አዎን፣ እናም ለስንፍናቸውና፣ ለጣኦት አምላኪነታቸው፣ እናም ለዝሙታቸው፣ ንጉስ ኖህ በህዝቡ ላይ ባደረገው ቀረጥ ተደግፈዋል፤ እንደዚህ ነበር ህዝቡ ጥፋትን ለመደገፍ በጣም የሰሩት።

አዎን፣ እናም ደግሞ እነርሱ ጣኦት አምላኪ ሆነው ነበር፣ ምክንያቱም በንጉሱና በካህናቱ ከንቱና የሽንገላ ቃላት ተታለው ነበር፤ እነርሱም ከንቱ የሆኑትን ነገሮች ይናገሩአቸው ነበርና።

እናም እንዲህ ሆነ ንጉስ ኖህ ያማሩና ሰፊ ህንፃዎችን ገነባ፤ እናም በማለፊያ የእንጨት ስራዎችና በሁሉም ዓይነት ውድ ነገሮች፣ በወርቅም፣ በብርም፣ በብረትም፣ በነሀስም፣ እንዲሁም በዚፍና በመዳብ አስጌጣቸው።

እናም ደግሞ ለራሱ ትልቅ ቤተ መንግስትንና በመካከሉ ዙፋንን ሰራ፣ ሁሉም ማለፊያ እንጨት እናም በወርቅና በብር፣ እንዲሁም በውድ ነገሮች ያጌጡ ነበር።

እናም ደግሞ ሰራተኞቹ በቤተ መቅደሱ ግንብ ክልል ውስጥ ከማለፊያ እንጨትና መዳብ እንዲሁም ከነሀስ ስራቸውን እንዲሰሩ አደረገ።

፲፩ እናም ከሌሎች መቀመጫዎች ሁሉ በላይ የሆነው ለሊቀ ካህናት የተዘጋጀውን መቀመጫ በንፁህ ወርቅ አስጌጠው፤ እናም ውሸትንና ከንቱ ቃላትን ለህዝባቸው ሲናገሩ ሰውነታቸውንና ክንዶቻቸውን በላያቸው ላይ ያሳርፉበት ዘንድ በፊታቸው መደገፊያን ገነቡላቸው።

፲፪ እናም እንዲህ ሆነ በቤተ መቅደሱ አጠገብ ረጅም ሠገነት ገነባ፤ አዎን፣ በጣም ከፍ ያለ ግንብ፣ በላዩ ላይ በመቆም የሻምሎን ምድር ለማየት የሚያስችል ከፍታ ያለውን፤ እናም ደግሞ በላማናውያን የተያዘውን የሻምሎን ምድር፤ እናም በዙሪያው ያሉትን ቦታዎች ሁሉ መመልከት የሚችልበትን ግንብ ሠራ።

፲፫ እናም እንዲህ ሆነ በሼምሎን ምድር ብዙ ህንፃዎች እንዲገነቡ አደረገ፣ እናም ታላቅ ግንብ የኔፊ ልጆች ከምድሪቱ ሸሽተው በወጡበት ጊዜ ማረፊያቸው በነበረው በሼምሎን በስተሰሜን ኮረብታው ላይ እንዲገነባ አደረገ፤ እናም እንደዚህም ነበር በቀረጥ ከህዝቡ ባካበተው ሀብት የሰራው።

፲፬ እናም እንዲህ ሆነ ልቡን በሃብቶች ላይ አደረገ፣ እናም ከሚስቶቹና ከዕቁባቶቹ ጋር በቀበጠ ብልሹ ህይወት ጊዜውን አሳለፈ፤ እናም ካህናቱም ደግሞ እንደዚሁ ከጋለሞታዎች ጋር ጊዜያቸውን አሳለፉ።

፲፭ እናም እንዲህ ሆነ በምድሪቱ ዙሪያ ወይን አትክልቶችን ተከለ፤ የወይን መጭመቂያንም ሰራ፤ ወይን ጠጅንም በብዛት ሰራ፤ እናም በዚህ ምክንያት እርሱና ህዝቡ የወይን ጠጅ ጠጪ ሆኑ።

፲፮ እናም እንዲህ ሆነ የትንሽ ቁጥር ህዝቦቹ በሜዳው ላይ ከብቶቻቸውን በሚጠብቁበት ጊዜ ላማናውያን በምድሩ ላይ ሊገድሉአቸው መምጣት ጀመሩ።

፲፯ እናም ንጉስ ኖህ እነርሱን ለማባረር ጠባቂዎችን በምድሪቱ ላከ፤ ነገር ግን በቂ ቁጥር አልላከም ነበር፣ እናም ላማናውያን በእነርሱ ላይ መጡና ገደሏቸው፣ እናም ብዙ መንጋዎቻቸውን ከምድሪቱ አባረሩ። እንደዚህም ላማናውያን እነርሱን ማጥፋት እናም ጥላቻቸውን በእነርሱ ላይ መለማመድ ጀመሩ።

፲፰ እናም እንዲህ ሆነ ንጉስ ኖህ ወታደሮቹን ላከባቸውና፣ ወደ ኋላ ተመለሱ፣ ወይንም ለጊዜው ወደ ኋላ ተመለሱ፤ ስለዚህ በዘረፉት ተደስተው ተመለሱ።

፲፱ እናም አሁን፣ በዚህ በታላቁ ድል ምክንያት በልባቸው ኩራት ተሞልተው ነበር፤ በራሳቸውም ጥንካሬ እንዲህ በማለት፥ የእነርሱ ሀምሳዎች የላማናውያንን ሺህ መቋቋም እንደሚችሉ ፎከሩ፤ እናም በደምና በወንድሞቻቸው ደም መፋሰስ ተደሰቱ፣ ይህም በንጉሳቸውና በካህናቶቻቸው ክፋት የተነሳ ነው።

እናም እንዲህ ሆነ በእነርሱ መካከል ስሙ አቢናዲ የሚባል አንድ ሰው ነበር፤ እርሱ በመካከላቸው እየሄደም እንዲህ በማለት ትንቢት መናገር ጀመረ፤ እነሆ ጌታ እንዲህ ይላል፤ እናም እንዲህ በማለት አዞኛል፥ ሂድና ለዚህ ህዝብ ጌታ እንዲህ ብሎአል በላቸው—ለዚህ ህዝብ ወዮለት፣ እርኩሰታቸውንና፣ ኃጢአታችውን እንዲሁም ዝሙታቸውን አይቻለሁና፤ እናም ንስሃ ካልገቡ በቁጣዬ እጎበኛቸዋለሁ።

፳፩ እናም ንስሃ ካልገቡና ወደ ጌታ አምላካቸው ካልተመለሱ፣ እነሆ፣ በጠላቶቻቸው እጅ እንዲወድቁ አደርጋለሁ፤ አዎን፣ እናም በባርነት ስር ይሆናሉ፤ እናም በጠላቶቻቸው እጅ ይሰቃያሉ።

፳፪ እናም እንዲህ ይሆናል እኔ ጌታ አምላካቸው እንደሆንኩና፣ ቀናተኛ አምላክ መሆኔን፣ የህዝቤን ጥፋት የምጎበኝ እንደሆንኩ ያውቃሉ።

፳፫ እናም እንዲህ ይሆናል፣ ይህ ህዝብ ንስሃ ካልገባ እናም ወደ ጌታ አምላካቸው ካልተመለሱ ወደ ባርነት ይሄዳሉ፤ እናም ሁሉን ከሚገዛው ጌታ እግዚአብሔር በቀር ማንም አያላቅቃቸውም።

፳፬ አዎን፣ እናም እንዲህ ይሆናል፣ ወደ እኔ በሚጮሁበትም ጊዜ ጩኸታቸውን ለመስማት እዘገያለሁ፤ አዎን እናም በጠላቶቻቸው እንዲመቱ እፈቅዳለሁ።

፳፭ እናም ማቅ ለብሰው፣ አመድ ነስንሰው ንስሃ ካልገቡ እንዲሁም ወደ ጌታ አምላካቸው በኃይል ካልጮሁ በስተቀር፣ ፀሎታቸውን አልሰማም፣ ወይም ከስቃያቸው አላላቅቃቸውም፤ እናም ጌታ እንዲህ ይላል፣ እንዲህም አዞኛል።

፳፮ አሁን እንዲህ ሆነ አቢናዲ ይህንን ቃል ለእነርሱ በተናገረበት ጊዜ ተቆጡበት፣ እናም ህይወቱን ሊያጠፉ ፈለጉ፤ ነገር ግን ጌታ ከእጃቸው አዳነው።

፳፯ አሁን ንጉስ ኖህ አቢናዲ ለህዝቡ የተናገረውን ቃላት በሰማ ጊዜ እርሱም ደግሞ ተቆጣ፤ እናም እንዲህ አለ፥ አቢናዲ ማን ነው፣ በእኔና በህዝቤ የሚፈርድ፣ ወይም በህዝቤ ላይ ታላቅ ስቃይን የሚያመጣው ጌታስ ማን ነው?

፳፰ አቢናዲን እገድለው ዘንድ እንድታመጡት አዛለሁ፣ ምክንያቱም ህዝቦቼ አንዱ በአንዱ ላይ ተቆጥቶ ይታወክ ዘንድ እናም በህዝቤም መካከል ፀብ ለማንሳት እነዚህን ነገሮች ተናግሯልና፤ ስለዚህ እርሱን እገድለዋለሁ።

፳፱ አሁን የህዝቡ ዐይን ታውሯል፤ ስለዚህ በአቢናዲ ቃላት ላይ ልባቸውን አጠጥረዋል፤ እናም ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እርሱን ለመውሰድ ሞክረዋል። እናም ንጉስ ኖህ በጌታ ቃል ላይ ልቡን አጠጠረም፣ ለመጥፎ ስራውም ንስሃ አልገባም።