ቅዱሳት መጻህፍት
ሞዛያ ፲፱


ምዕራፍ ፲፱

ጌዴዎን ንጉስ ኖህን ለመግደል ፈለገ—ላማናውያን ምድሪቱን ወረሩ—ንጉስ ኖህ በእሳት ሞተ—ሊምሂ እንደ ግብር ከፋይ ንጉስ ገዛ። ከ፻፵፭–፻፳፩ ም.ዓ. ገደማ።

እናም እንዲህ ሆነ የጌታን ህዝብ በከንቱ ከፈለጉ በኋላ የንጉሱ ወታደሮች ተመለሱ።

እናም አሁን እነሆ፣ የንጉሱ ኃይል በመቀነሳቸው፣ ትንሽ ነበሩ፤ በቀሪው ህዝብ መካከል መከፋፈል ተጀመረ።

እናም ትንሹ ክፍል ንጉሱን ማስፈራራት ጀመረ፤ እናም በመካከላቸው ታላቅ ፀብ ተጀመረ።

እናም አሁን በመካከላቸው ጌዴዎን የሚባል ሰው ነበር፣ እርሱም ጠንካራ ሰውና ለንጉሱ ጠላት በመሆኑ፣ ስለዚህ ጎራዴውን መዘዘና ንጉሱን እንደሚገድለው በቁጣው ማለ።

እናም እንዲህ ሆነ ከንጉሱ ጋር ተዋጋ፤ ንጉሱም እንደሚያሸንፈው በተመለከተ ጊዜ፣ ሸሸና፣ ሮጠ፣ እና በቤተ መቅደሱ አጠገብ በሚገኘው ግንብ ላይ ወጣ።

እናም ጌዴዎን ተከተለውና ንጉሱን ለመግደል ወደ ግንቡ ተጠጋ፣ እናም ንጉሱ አይኑን በዚህና በዚያ ተመለከተና በሻምሎን ምድር ላይ አይኑን ጣለ፣ እናም እነሆ፣ የላማናውያን ወታደሮች በምድሪቱ ዳርቻ እንደ ነበሩ ተመለከተ።

እናም አሁን ንጉሱ በጭንቀት እንዲህ በማለት ጮኸ፥ ጌዴዎን፣ ህይወቴን አትርፈው፣ ላማናውያን በእኛ ላይ መጥተዋልና፣ እናም ያጠፉናል፤ አዎን፣ ህዝቤንም ያጠፉታል።

እናም አሁን ንጉሱ ለህይወቱ እንዳሰበው ያህል ለህዝቡ አላሰበም ነበር፤ ይሁን እንጂ፣ ጌዴዎን ህይወቱን አተረፈለት።

እናም ንጉሱ ህዝቡ ከላማናውያን እንዲሸሽ አዘዘ፤ እርሱም ራሱ ከፊታቸው ሄደ፣ እናም እነርሱ ከሴቶቻቸውና ከልጆቻቸው ጋር ወደ ምድረበዳ ሸሹ።

እናም እንዲህ ሆነ ላማናውያን ተከተሉአቸውና፣ ደረሱባቸው፣ ይገድሉአቸውም ጀመሩ።

፲፩ አሁን እንዲህ ሆነ ንጉሱ ሁሉም ወንዶች ሚስቶቻቸውንና ልጆቻቸውን እንዲተው እናም ከላማናውያን ፊት እንዲሸሹ አዘዘ።

፲፪ አሁን ትተዋቸው ያልሄዱ ብዙዎች ነበሩ፣ ነገር ግን ከእነርሱ ጋር መቆየትና መጥፋት ፈለጉ። እናም የተቀሩት ሚስቶቻቸውንና ልጆቻቸውን ትተው ሸሹ።

፲፫ እናም እንዲህ ሆነ ከሚስቶቻቸውና ከልጆቻቸው ጋር የቀሩት፣ ቆንጆዎቹ ሴቶች ልጆቻቸው ላማናውያን እንዳይገድሉአቸው እንዲለምኑ ወደፊት እንዲቆሙ አስደረጉ።

፲፬ እናም እንዲህ ሆነ ላማናውያን በሴቶቻቸው ውበት በመማረካቸው አዘኑላቸው።

፲፭ ስለዚህ ላማናውያን ህይወታቸውን አተረፉላቸውና፣ ማረኩአቸው፣ እንዲሁም ወደኔፊ ምድር መለሱአቸው፣ እናም ንጉስ ኖህን ለላማናውያን ካቀረቡ፤ ንብረቶቻቸውን፣ እንዲሁም ካሉአቸው ሁሉ ግማሹን፣ ከወርቃቸው ግማሹንና፣ ከብራቸው፣ እናም ከሁሉም ከከበሩ ነገሮቻቸው አሳልፈው ከሰጡ ምድሪቱን እንደሚይዙ ተስማምተው ሰጡአቸው፣ በዚህም በየዓመቱ ለላማናውያን ንጉስ ግብርን እንዲከፍሉ አደረጉአቸው።

፲፮ እናም አሁን በምርኮ ከተወሰዱት መካከል ስሙ ሊምሂ የተባለ የንጉሱ ልጆች የሆነ አንድ ልጅ ነበር።

፲፯ እናም አሁን ሊምሂ አባቱ እንዳይጠፋ ፈልጎ ነበር፤ ይሁን እንጂ፣ ሊምሂ የአባቱን ክፋት የማያውቅ አልነበረም፣ እርሱ ራሱ ፃድቅ ሰው ነበርና።

፲፰ እናም እንዲህ ሆነ ጌዴዎን ንጉሱንና ከእርሱ ጋር ያሉትን ለማግኘት በሚስጥር ወደ ምድረበዳው ሰዎችን ላከ። እናም እንዲህ ሆነ ከንጉሱና ከካህናቱ በስተቀር በምድረበዳ ውስጥ ከሰዎች ጋር ተገናኙ።

፲፱ አሁን ሚስቶቻቸውና ልጆቻቸው፣ እናም ደግሞ ከእነርሱ ጋር የተቀሩት ቢገደሉ በቀልንና ደግሞ ከእነርሱ ጋር መጥፋትን በመፈለግ ወደ ኔፊ ምድር እንደሚመለሱ በልባቸው ምለው ነበር።

እናም ንጉሱ መመለስ እንደሌለባቸው አዘዛቸውና፣ በንጉሱ ተቆጡ፣ በእሳትም እስኪሞት እንኳን እንዲሰቃይ አደረጉ።

፳፩ እናም ካህናቱን ደግሞ ለመውሰድና፣ ለመግደል ፈለጉ፣ እነርሱም ሸሽተው አመለጡአቸው።

፳፪ እናም እንዲህ ሆነ ወደ ኔፊ ምድር እየተመለሱ እያሉ፣ እናም የጌዴዎንን ሰዎች አገኙ። የጌዴዎን ሰዎችም በልጆቻቸውና በሚስቶቻቸው ላይ ስለተፈፀመው ነገር ሁሉ ነገሯችው፤ እንዲሁም ለላማናውያን ካላቸው ሁሉ አንድ ሁለተኛውን ግብር ከከፈሉ ላማናውያን ምድሩን እንዲይዙ እንደፈቀዱላቸው ነገሯቸው።

፳፫ እናም ህዝቡ ለጌዴዎን ህዝብ ንጉሱን እንደገደሉትና፣ ካህናቱ ወደ ጥልቅ ምድረበዳው እንደሸሹ ነገሩአቸው።

፳፬ እናም እንዲህ ሆነ ስነስርዓቱ ካለቀ በኋላ፣ ወደኔፊ ምድር በደስታ ተመለሱ፣ ምክንያቱም ሚስቶቻቸውና ልጆቻቸው አልተገደሉም ነበርና፤ እናም ለጌዴዎን በንጉሱ ላይ ያደረጉትን ነገሩት።

፳፭ እናም እንዲህ ሆነ የላማናውያን ንጉስ ህዝቡ እንደማይገድሉአቸው መሀላ ፈፀመ።

፳፮ እናም ደግሞ ሊምሂ የንጉስ ልጅ በመሆኑ፣ በህዝቡም በገዥነት በመሾሙ፣ ህዝቡ ካለው ግማሹን ያህል ግብር እንደሚከፍሉ ለላማናውያን ንጉስ መሃላ አደረገ።

፳፯ እናም እንዲህ ሆነ ሊምሂ መንግስት መመስረት እናም በህዝቡ መካከል ሰላምን መመስረት ጀመረ።

፳፰ እናም የሊምሂ ህዝብ በምድር ውስጥ እንዲጠብቁ፣ ወደ ምድረበዳው እንዳይሸሹ፣ የላማናውያን ንጉስ በሀገሪቱ ዙሪያ ጠባቂዎችን አስቀመጠ፤ እናም ከኔፋውያን በሚቀበለው ግብርም ጠባቂዎቹን ደገፈ።

፳፱ እናም አሁን ንጉስ ሊምሂ ያለማቋረጥ ለሁለት ዓመታት በመንግስቱ ላይ ሰላም ነበረው፣ ላማናውያንም አላበሳጩአቸውም እንዲሁም ሊያጠፉአቸው አልፈለጉም።