ቅዱሳት መጻህፍት
ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች ፮


ክፍል ፮

ሚያዚያ ፲፰፻፳፱ (እ.አ.አ.) በሀርመኒ፣ ፔንስልቬንያ፣ ለነቢዩ ጆሴፍ ስሚዝ እና ለኦሊቨር ካውድሪ የተሰጠ ራዕይ። በሚያዚያ ፯፣ ፲፰፻፳፱ (እ.አ.አ.) ኦሊቨር ካውድሪ የመፅሐፈ ሞርሞን ትርጉም ጸሐፊ በመሆን ማገልገል ጀመረ። የመፅሐፈ ሞርሞን መዛግብት የተቀረጹበትን ሰሌዳዎች በተመለከተ ስለነቢዩ ምስክርነት እውነትነት ቀደም ብሎ መለኮታዊ መገለጥን ተቀብሎ ነበር። ነቢዩ በኡሪምና ቱሚም ጌታን ጠየቀ እናም ይህን መልስ ተቀበለ።

፩–፮፣ በጌታ የእርሻ ስፍራ የሚያገለግሉ ሰራተኞች ደህንነትን ያገኛሉ፤ ፯–፲፫፣ ከደህንነት ስጦታ የበለጠ ስጦታ የለም፤ ፲፬–፳፯፣ የእውነት ምስክርነት በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ይመጣል፤ ፳፰–፴፯፣ ወደ ክርስቶስ ተመልከቱ እናም ሁልጊዜ መልካምን አድርጉ።

ታላቅ እና ድንቅ ስራ ወደ ሰዎች ልጆች ሊመጣ ነው።

እነሆ፣ እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ ፈጣን እና ሀያል፣ ሁለት ስለት ካለው ሰይፍ ይልቅ የተሳለ፣ መገጣጠሚያን እና መቅኔን እስኪለይ ድረስ የሚሰራውን ቃሌን አድምጡ፤ ስለዚህ ቃሎቼን አድምጡ።

እነሆ፣ የእርሻው ስፍራ ነጭ ሆኖ አዝመራው ዝግጁ ነው፣ ስለዚህ፣ ለነፍሱም ዘለአለማዊ ደህንነት በእግዚአብሔር መንግስት ያከማች ዘንድ መሰብሰብ የሚሻ በኃይሉ ይጨድ እናም ቀኑም እየመሸ ሳለም ይሰብስብ።

አዎን፣ ማንኛውም የሚያጭድ እናም የሚሰበስብ፣ እንዲሁ በእግዚአብሔር የተጠራ ነው።

ስለዚህ፣ እኔን ብትጠይቁኝ ትቀበላላችሁ፣ ካንኳኳችሁ ይከፈትላችኋል።

አሁን፣ እንደጠየቃችሁት፣ እነሆ፣ እንዲህ እላችኋለሁ፣ ትእዛዛቴን ጠብቁ እናም የፅዮንን አስተሳሰብ ለማምጣት እና ለመመስረት እሹ

ጥበብን እንጂ ሀብትን አትሹ፣ እናም እነሆ፣ የእግዚአብሔር ሚስጥራት ይገለጡላችኋል፣ እናም ባለጠጋም ትሆናላችሁ። እነሆ፣ ዘለዓለማዊ ሕይወት ያለው እርሱም ባለጠጋ ነውና።

እውነት፣ እውነት፣ እላችኋለሁ፣ ላደርግላችሁ እንደምትሹ እንዲሁ ይሆንላችኋል፤ የምትሹ ከሆነም ካላችሁ፣ በዚህ ትውልድ ውስጥ ለብዙ መልካም ነገሮች መከናወን መሳሪያ ትሆናላችሁ።

ለዚህ ትውልድ ከንስሀ በቀር ሌላ ምንም አትናገሩ፤ ትእዛዛቴን ጠብቁ፣ እናም ስራዬን በትእዛዛቴ መሰረት ለማምጣት እርዱ፣ እናም ትባረካላችሁ።

እነሆ ስጦታ አላችሁ፣ እናም በስጦታችሁም የተነስ የተባረካችሁ ናችሁ። ይህም የተቀደሰ እና ከላይ የመጣ መሆኑን አስታውሱ—

፲፩ እናም ከጠየቅህ፣ ታላቅ እና ድንቅ የሆኑ ሚስጥራትን ታውቃለህ፤ ስለዚህም ሚስጥራትን ታውቅ ዘንድ፣ ብዙዎችንም ወደ እውነት እውቀት ታመጣ ዘንድ፣ አዎን፣ የተሳሳተ መንገዳቸውን ሁሉ እንዲተው ታሳምናቸውም ዘንድ ስጦታህን ትጠቀምበታለህ።

፲፪ በአንተ እምነት ውስጥ ካልሆኑ በስተቀር ስጦታህን ለማንም አታሳውቅ። በተቀደሱ ነገሮች አትቀልድ።

፲፫ መልካምን ካላደረግህ፣ እናም እስከ መጨረሻም በእምነት ከጸናህ ከእግዚአብሔር የስጦታዎች ሁሉ የበላይ በሆነው በእግዚአብሔር መንግስት ትድናለህ፤ ከደህንነት በላይ የሆነ ምንም ስጦታ የለምና።

፲፬ እውነት፣ እውነት፣ እልሀለሁ፣ ባደረግኸው የተባረክህ ነህ፤ ምክንያቱም እኔን ጠይቀኃል እናም በጠየቅኸው መጠን የመንፈሴን መመሪያ ተቀብለኃል። ይህ ባይሆን ኖሮ አሁን ያለህበት ስፍራ ባልደረስህ ነበር።

፲፭ እነሆ፣ እንደጠየቅኸኝ ታውቃለህ እናም አዕምሮህን አብርቻለሁ፤ እናም አሁን በእውነት መንፈስ መረዳትን እንዳገኘህ ታውቅ ዘንድ እነዚህን ነገሮች እነግርሀለሁ፤

፲፮ አዎን፣ ከእግዚአብሔር በስተቀር ማንም ሀሳብህንና የልብህን ፈቃድ እንደማያውቅ እንድታውቅ ዘንድ እነግርሀለሁ።

፲፯ እየጻፍህ ያለው ቃላት ወይም ስራ እውነት እንደሆነ—ለአንተ እንደምስክርነት እነዚህን ነገሮች እነግርሀለሁ።

፲፰ ስለዚህ ትጉህ ሁን፤ በታማኝነት፣ ለቃሉ ሲል በሚገጥመው በማንኛውም አስቸጋሪ ሁኔታ ከአገልጋዬ ከጆሴፍ ጎን ቁም

፲፱ በስህተቱም ገስጸው፣ እናም ከእርሱም ተግሳጽን ተቀበል። ትዕግስተኛ ሁን፤ የተረጋጋህ ሁን፣ ራስህን ግዛ፣ ትዕግስት፣ እምነት፣ ተስፋ እና ልግስና ይኑርህ።

እነሆ፣ አንተ ኦሊቭር ነህ፣ እናም በፈቃድህ ምክንያት ተናግሬሀለሁ፤ ስለዚህ እነዚህን ቃላት በልብህ አከማች። የእግዚአብሔርን ትእዛዝ በመጠበቅታማኝ እና ትጉህ ሁን፣ እናም በፍቅሬ እቅፍ ውስጥም አደርግሀለሁ።

፳፩ እነሆ፣ እኔ የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ነኝ። የእኔው ወደሆኑት የመጣሁት እናም የራሴም ያልተቀበሉኝ እኔው ነኝ። እኔ በጭለማም የማበራ ብርሀን ነኝ፣ እናም ጭለማውም አይገነዘበውም።

፳፪ እውነት፣ እውነት፣ እልሀለሁ፣ ተጨማሪ ምስክርነትን ከፈለግህ፣ ስለ እነዚህ ነገሮች እውነትነት ታውቅ ዘንድ በልብህ ወደ እኔ የጮህክበትን ምሽት አስታውስ።

፳፫ ይህንን ነገር በተመለከተ ለአምሮህ ሰላምን አልተናገርኩምን? ከእግዚአብሔር ከመጣ ምስክርነት ይልቅ ምን አይነት ምስክርነት ትፈልጋለህ?

፳፬ እናም አሁን፣ እነሆ፣ ምስክርነትን ተቀብለሀል፤ ሌላ ሰው የማያውቃቸውን ነገሮች ነግሬህ ምስክርነትን አልተቀበልክምን?

፳፭ እናም፣ እነሆ፣ ከእኔም የምሻ ከሆነ ልክ እንደ አገልጋዬ ጆሴፍ ትተረጉም ዘንድ ስጦታን እሰጥሀለሁ።

፳፮ እውነት፣ እውነት፣ እልሀለሁ፣ በሰዎች ኃጢአት የተነሳ ያስቀረኋቸው አብዛኛውን ወንጌሌን የያዙ ጽሁፎች አሉ።

፳፯ እናም አሁን አዝሀለሁ፥ ለራስህ ሀብትን በሰማይ የማከማቸት ፈቃድ የሆነ መልካም ፈቃድ ካለህ፣ ከዚያም፣ በኃጢአት የተነሳ ተደብቀው የነበሩትን ቅዱሳን መጻህፍቴን በስጦታህ ወደ ብርሀን በማምጣት ትረዳለህ።

፳፰ እናም አሁን፣ እነሆ፣ ለአንተ እና ለአገልጋዬ ለጆሴፍ ይህንን አገልግሎት ወደ ብርሀን የሚያመጣውን ስጦታ ቁልፍ እሰጣችኋለሁ፤ በሁለት ወይም በሶስት ምስክር አንደበት ሁሉም ቃል ይጸናል።

፳፱ እውነት፣ እውነት፣ እልሀለሁ፣ ቃሌን እና የዚህን የወንጌል ክፍል እናም አገልግሎቴን የማይቀበሉ ከሆኑ፣ የተባረካችሁ ናችሁ፣ ምክንያቱም በእኔ ላይ ካደረጉብኝ በላይ ሊያደርጉባችሁ አይችሉምና።

እናም በእኔ ላይ እንዳደረጉት እንዲሁ በእናንተ ላይ ቢያደርጉም እንኳን፣ የተባረካችሁ ናችሁ፣ ከእኔም ጋር በክብር ትኖራላችሁና

፴፩ ነገር ግን በሚሰጠው ምስክርነት የሚጸናውን ቃሌን ካልተቃወሙ፣ የተባረኩ ናቸው፣ እና ከዚያም በስራችሁ ፍሬ ትደሰታላችሁ።

፴፪ እውነት፣ እውነት፣ እልሀለሁ፣ ልክ ለደቀመዛሙርቴ እንደተናገርሁት፣ ሁለት ወይም ሶስት ሆነው በስሜ፣ አንድን ነገር በተመለከተ፣ በሚሰበሰቡበት፣ በዚያም በመካከላቸው እሆናለሁ፣ እንዲሁም በመካከላችሁ ነኝ።

፴፫ ልጆቼ፣ መልካምን ለማድረግ አትፍሩየዘራችሁትን ያንኑ መልሳችሁ ታጭዳላችሁ፤ ስለዚህ መልካምን ከዘራችሁ ያንኑ መልካም የሆነውን እንደ ደመወዝ ታጭዳላችሁ።

፴፬ ስለዚህ፣ አትፍሩ፣ እናንት ትንሽ መንጋዎች፣ መልካምን አድርጉ፤ ምድርና ገሀነም ቢቀናጁባችሁም፣ በእኔ ዐለት ላይ ከተገነባችሁ ሊቋቋሟችሁ አይችሉምና።

፴፭ እነሆ፣ አልኮንናችሁም፤ በመንገዳችሁ ሂዱ እናም ዳግምም ኃጢአትን አትስሩ፤ ያዘዝኳችሁን ስራ በርጋታ እከናውኑ።

፴፮ ባሰባችሁት ነገር ሁሉ ወደ እኔ ተመልከቱ፤ አትጠራጠሩ፣ አትፍሩ።

፴፯ ጎኔ ላይ የተወጋሁት ቁስል፣ እናም በእጄ እና በእግሬ ላይ ያሉትን የምስማር ምልክቶች አስቧቸው፤ እናም እምነት ይኑራችሁ፣ ትእዛዛቴን ጠብቁ፣ እናም መንግስተ ሰማያትን ትወርሳላችሁ። አሜን።