ለወጣቶች ጥንካሬ
ለወጣቶች ጥንካሬ፦ አዳኙ ለእናንተ ያለው መልእክት
መጋቢት 2024 (እ.አ.አ)


“ለወጣቶች ጥንካሬ፦ አዳኙ ለእናንተ ያለው መልእክት፣” ለወጣቶች ጥንካሬ፣ መጋቢት፣2024 (እ.አ.አ)

ወርኃዊ የ ለወጣቶች ጥንካሬ መልእክት፣ መጋቢት 2024 (እ.አ.አ)

ለወጣቶች ጥንካሬ፦ አዳኙ ለእናንተ ያለው መልእክት

ይህ መመሪያ ምርጫችሁን ከኢየሱስ ክርስቶስ እና ከትምህርቱ ጋር ማገናኘት እንድትችሉ ይረዳችኋል።

ምስል
ኢየሱስ ክርስቶስ

I Stand at the Door and Knock [ከበሩ ቆሜ አንኳኳለሁ]፣ በጄ. ከርክ ሪቻርድስ

ከ2,000 አመታት በፊት፣ በጥንቷ ገሊላ ውስጥ እየኖራችሁ እንደሆነ አስቡ። እናንተ እና ጓደኞቻችሁ በአካባቢው በሚገኘው ምኩራብ ውስጥ በሚደረገው በልዩ እንግዳ ተናጋሪው፣ በናዝሬቱ ኢየሱስ፣ በሚቀርበው የወጣቶች መንፈሳዊ ትምህርት ላይ እንድትገኙ ተጋብዛችኋል። እናም በመልዕክቱ አንድ የተወሰነ ነጥብ ላይ፣ ኢየሱስ ከአድማጮቹ መካከል ያሉት ወጣቶች ጥያቄ እንዲጠይቁት ጋበዛቸው።

ምን አይነት ጥያቄዎችን ልትሰሙ እንደምትችሉ ታስባላችሁ?

አንዳንድ ጥያቄዎች በጊዜው የነበረውን ባህልና ሁኔታ የሚያንፀባርቁ እንደሚሆኑ እገምታለሁ። ነገር ግን ብዙዎቹ ዛሬ ያሉንን ጥያቄዎች እንደሚመስሉ በእውነት አምናለሁ።

ለምሳሌ፣ በአዲስ ኪዳን ውስጥ፣ ሰዎች አዳኙን እንደእነዚህ አይነት ጥያቄዎችን ጠይቀውታል፦

  • የዘለአለም ህይወት ለማግኘት ምን ማድረግ አለብኝ? 1

  • ተቀባይነት አለኝ? የዚያ አካል ለመሆን ብቁ ነኝ?2

  • ወንድሜ ቢበድለኝ ስንት ጊዜ ይቅር ልለው ይገባኛል?3

  • ወደፊት ይህች አለም ምን ትሆናለች? ደህንነቴ የተጠበቀ ይህናል?4

  • የምወደውን ሠው ልትፈውስ ትችላለህ?5

  • እውነት ምንድን ነው?6

  • ወደ ትክክለኛው መንገድ እየሄድኩኝ እንደሆነየማውቀው እንዴት ነው?7

አልፎ አልፎ ተመሳሳዩን ነገር ሁላችንም አናስብምን? ባለፉት ክፍለ ዘመናት፣ ጥያቄዎቹ ብዙም አልተቀየሩም። አዳኙ ጥያቄዎቹን ለሚጠይቁ ያለው ርህራሄም አልተለወጠም። ህይወት ምን ያህል አስጨናቂ እና ግራ የሚያጋባ ሊሆን እንደሚችል ያውቃል። መንገዳችንን ማጣት ምን ያህል ቀላል እንደሆነ ያውቃል። አንዳንድ ጊዜ ስለ ወደፊቱ ጊዜ እንደምንጨነቅ ያውቃል። እናም ልክ ለጥንት ተከታዮቹ ከረዥም ጊዜ በፊት እንደተናገረው፣ ለእናንተ እና ለእኔ እንዲህ ይለናል፦

  • “ልባችሁ አይታወክ።”8

  • “እኔ መንገድ [እና] እውነት … ነኝ።”9

  • “ተከተ[ሉ]ኝ!”10

የምትመርጡት አስፈላጊ ምርጫዎች ሲኖራችሁ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ እና ዳግም የተመለሰው ወንጌሉ ምርጥ ምርጫዎች ናቸው። ጥያቄዎች ሲኖሯችሁ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ እና ዳግም የተመለሰው ወንጌሉ ምርጥ መልስ ናቸው።

ለወጣቶች ጥንካሬ፦ ምርጫዎችን የማድረግ መመሪያን የምወደው ለዚህ ነው። ሀይሉን መቀበል እንድንችል ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ያመለክተናል። ሁል ጊዜ አንድ ቅጂ ኪሴ ውስጥ አስቀምጣለሁ። እኛ እንደ የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን አባላት የምናደርጋቸውን ነገሮች ለምን እንደምናደርግ ለማወቅ የሚፈልጉ በአለም ዙሪያ ያሉ ሰዎችን ሳገኝ፣ ይህንን መመሪያ ለእነርሱ አካፍላቸዋለሁ።

ለወጣቶች ጥንካሬ ስለአዳኙ እና ስለመንገዱ ዘለአለማዊ እውነቶችን ያስተምራል። ይህም በእነዚያ እውነቶች ላይ የተመሰረቱ ምርጫዎችን እንድታደርጉ ይጋብዛችኋል። እንዲሁም ለሚከተሉት ሁሉ የሚሠጣቸውን ቃል የተገቡ በረከቶች ያጋራል። እባካችሁን ይህንን መመሪያ አንብቡት፣ አሰላስሉት እንዲሁም አካፍሉት!

ወደ ውስጥ ጋብዙት

ኢየሱስ ክርስቶስም ዘላቂ፣ በጥሩ እና በመጥፎ ጊዜ በየቀኑ የሚገኝ የህይወታችሁ አካል መሆን ይፈልጋል። እናንተ እርሱ ላይ እስክትደርሱበት ድረስ በመንገዱ መጨረሻ ላይ ቆሞ የሚጠብቅ አይደለም። በየእያንዳንዱ እርምጃ በመንገዱ ከእናንተ ጋር አብሯችሁ ይራመዳል። እርሱ መንገድ ነው!

ሆኖም እርሱ ወደ ህይወታቹ በግድ አይገባም። በምርጫዎቻችሁ አማካኝነት እሱን ወደ ውስጥ ትጋብዙታላችሁ። እንደ ለወጣቶች ጥንካሬ አይነት ምርጫዎችን የማድረግ መመሪያ በጣም ተወዳጅ የሚሆነው ለዚህ ነው። በአዳኙ ዘለአለማዊ እውነቶች ላይ ተመስርታችሁ የጽድቅ ምርጫን ባደረጋችሁ ቁጥር፣ እርሱን በህይወታችሁ እንደምትፈልጉት ታሳያላችሁ። እነዚያ ምርጫዎች የሰማይ ደጆችን ይከፍታሉ፣ እናም ጥንካሬው ወደ ህይወታችሁ እየፈሰሰ ይመጣል።11

ጠንካራ ግንኙነት ፍጠሩ

አዳኙ፣ ቃሉን ሰምቶ የሚያደርገው ሁሉ፣ “ቤቱን በአለት ላይ [ከሰራ]” ከልባም ሰው ጋ እንዳመሳሰለ ታስታውሱ ይሆናል። እንዲ ሲል አብራርቷል፦

“ዝናብም ወረደ ጎርፍም መጣ ነፋስም ነፈሰ ያንም ቤት ገፋው፣ በዓለት ላይም ስለ ተመሠረተ አልወደቀም።”12

አንድ ቤት በዐውሎ ነፋስ ጊዜ የሚተርፍበት ምክንያት ጠንካራ ስለሆነ አይደለም። ዓለቱ ጠንካራ ስለሆነ ብቻም አይተርፍም። ቤቱ ከአውሎ ነፋሱ የሚተርፈው ከጠንካራው ዓለት ጋር በጥብቅ የተቆራኘ ስለሆነ ነው። ከዓለቱ ጋር ያለው ግንኙነት ጥንካሬ ነው አስፈላጊው ነገር።

በተመሳሳይም፣ ህይወታችንን ስንገነባ፣ ጥሩ ምርጫዎችን ማድረግ አስፈላጊ ነው። እንዲሁም የአዳኙን ዘለአለማዊ እውነት መረዳት አስፈላጊ ነው። ነገር ግን የህይወት ማዕበሎችን ለመቋቋም የሚያስፈልገን ጥንካሬ የሚመጣው ምርጫዎቻችንን ከኢየሱስ ክርስቶስ እና ከትምህርቱ ጋር ስናገናኝ ነው። ለወጣቶች ጥንካሬ እንድናደርግ የሚረዳን ያንን ነው።

ለምሳሌ፣ ጓደኞቻችሁ፣ ሠዎችን የሚያስቀይሙ ወይም ጎጂ ቃላትን ላለመጠቀም እንደምትሞክሩ ሊያውቁ ይችላሉ። በትምህርት ቤት ውስጥ ብዙ ሰዎች ትኩረት የማይሰጡትን አልፎ ተርፎም የሚያበሽቁትን ልጅ ስትረዱ ሊያዩ ይችላሉ። ነገር ግን እነዚህን ምርጫዎች የምታደርጉት ኢየሱስ ክርስቶስ “ከእናንተም የተለዩ ሰዎችንም ጨምሮ፣ ሰዎች ሁሉ ወንድሞቻችሁና እህቶቻችሁ ናቸው”13 ብሎ ስላስተማረ እንደሆነ ያውቃሉ?

ጓደኞቻችሁ እሁድ እሁድ ወደ ቤተክርስቲያን እንደምትሄዱያውቁ ይሆናል። አንድን ዘፈንን ላለመስማት ስትዘጉ ወይም የተወሰነ ፊልምን እንድትመለከቱ የቀረበላቸሁን ግብዣ እምቢ ስትሉ ያስተውሉ ይሆናል። ነገር ግን እነዚህን ምርጫዎች የምታደርጉት “ከሰማይ አባት እና ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር አስደሳች የቃል ኪዳን ግንኙነት” ስላላችሁ እና አዳኙን ለመከተል የዚያ ቃል ኪዳን አካል እንደመሆናችሁ መጠን፣ “መንፈስ ቅዱስ የዘወትር አጋራችሁ [በመሆኑ]” አመስጋኞች ስለሆናችሁ እንደሆነ ያውቃሉ?14

ሰዎች እንደማትጠጡ ወይም እንደማታጨሱ ወይም ደግሞ ሌሎች ጎጂ እጾችን እንደማትጠቀሙ ሊያውቁ ይችላሉ። ነገር ግን እነዚህን ምርጫዎች የምታደርጉት “ሰውነታችሁ የተቀደሰ፣” በእርሱ አምሳያ የተሰራ “አስደናቂ የሰማይ አባታችሁ ስጦታ”15 ነው ብሎ ኢየሱስ ክርስቶስ ስላስተማረ እንደሆነ ያውቃሉ?

ጓደኞቻችሁ እንደማታጭበረብሩ ወይም እንደማትዋሹ እና ትምህርትን በቁም ነገር እንደምትወስዱ ያውቁ ይሆናል። ሆኖም እነኚህን የማታደርጉበት ምክንያት ኢየሱስ ክርስቶስ “እውነት አርነት ያወጣችኋል”16 ብሎ ስላስተማረ እንደሆነ ያውቃሉ?

ከሁሉም በላይ፣ ጓደኞቻችሁ እናንተ ከክርስቶስ መሥፈርቶች ጋር ለመስማማት አንዳንድ ጊዜ ተወዳጅነት የሌላቸውን ምርጫዎች የምታደርጉበት ምክንያት “ኢየሱስ ክርስቶስ ጥንካሬያችሁ መሆኑን”17 ስለምታውቁ እንደሆነ ያውቃሉ?

እርሱ ጥንካሬያችሁ ነው።

ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ብሩህ እና ታላቅ ህይወት— ወደ እናንተ ሕይወት የሚወስድ መንገድ እንደሆነ እርግጠኛ የሆነ ምስክርነቴን እሰጣችኋለሁ። እንዲሁም ደግሞ የአሁን ጊዜ ብሩህ እና ታላቅ መንገድ ነው። በመንገዱ ተራመዱ፣ እርሱም ከእናንተ ጋር ይራመዳል። ይህን ማድረግ ትችላላችሁ!

ውድ ወጣት ጓደኞቼ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ጥንካሬያችሁ ነው። ከእርሱ ጋር መራመዳችሁን ቀጥሉ፣ እናም እርሱ ወዳዘጋጀላችሁ ዘለአለማዊ ደስታ “እንደ ንስር በክንፍ እንድትወጡ”18 ይረዳችኋል።