ኢየሱስ ክርስቶስ
ህያው ክርስቶስ


ህያው ክርስቶስ

የሐዋርያት ምስክርነት

ኢየሱስ ክርስቶስ ከሁለት ሺህ አመት በፊት የተወለደበትን ስናከብር፣ ውድድር ስለሌለው የህይወቱን እውንነት እና ስለእርሱ ታላቅ የኃጢያት ክፍያ መስዋዕቱ ወሰን የለሽ በጎነት እንመሰክራለን። በምድር ላይ በኖሩት እና ገና በሚኖሩትም ላይ እንዲህ ያለ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳደረ ማንም የለም።

እርሱም የብሉይ ኪዳን ታላቁ ያህዌህ እና የአዲስ ኪዳን መሲህ ነበር። በአባቱ ትዕዛዝ መሠረት ምድርን የፈጠረው እርሱ ነበር። “ሁሉ በእርሱ ሆነ ከሆነውም አንዳች እንኳ ያለ እርሱ አልሆነም” (ዮሐንስ 1፥3)። ምንም እንኳን ኃጢያት የሌለበት ቢሆንም፣ ጽድቅን ሁሉ ይፈጽም ዘንድ ተጠመቀ። “መልካም እያደረገ ዞረ” (የሐዋርያት ስራ 10፥38)፣ ይሁን እንጂ በዚህም ተነቀፈ። ወንጌሉ የሠላም እና የበጎ ፈቃድ መልእክት ነበር። ሁሉም ሰው ምሳሌውን ይከተል ዘንድ አጥብቆ ጠየቀ። በሽተኞችን እየፈወሰ፣ ለእውሮች ብርሀንን እየሰጠ፣ እና ሙታንን እያስነሳ የፍልስጤም መንገዶችን ተራመደ። የዘለአለምነትን እውነታ፣ በቅድመ ምድር የመኖራችንን እውነታ፣ የምድራዊ ህይወታችንን ዓላማ፣ እና የእግዚአብሔር ወንዶች እና ሴቶች ልጆች በሚመጣው ህይወት ሊኖራቸው ስለሚችሉት እምቅ ችሎታ አስተምሯል።

ለታላቅ የኃጢያት ክፍያ የመስዋፅትነቱ ማስታወሻ ይሆን ዘንድ ቅዱስ ቁርባንን መሰረተ። እርሱም በሀሰት ክሶች ተይዞና ተወግዞ፣ ህገወጥ ሰዎች ደስ ይሰኙ ዘንድ ተፈርዶበት እና በቀራንዮ በመስቀል ላይ ይሞት ዘንድ ተፈርዶበት ነበር። ለሰው ዘር ሁሉ ኃጢያት ቤዛ ይሆን ዘንድ ህይወቱን ሰጠ። በምድር ላይ ለኖሩት እና ለሚኖሩት ሁሉ የተሰጠ የወኪልነት ስጦታ ነበር።

ለሰው ልጆች ሁሉ ታሪክ ማዕከል የሆነው ህይወቱ በቤተልሔም እንዳልተጀመረ እና በቀራንዮ እንዳላበቃ በክብር እንመሰከራለን። እርሱ የአብ የበኩር ልጅ፣ በስጋ የተገለጠ አንድያ ልጅ፣ የአለም አዳኝ ነበር።

“ላንቀላፋት በኩራት ሆኖ” ከመቃብር ተነስቷል (1 ቆሮንቶስ 15፥20)። ከሞት እንደተነሳም ጌታ፣ በህይወት ዘመኑ የወደዳቸውን ጎበኘ። ደግሞም በጥንታዊ አሜሪካ ውስጥ በእርሱ “ሌሎች በጎች” መሐል (ዮሐንስ 10፥16) አገለገለ። በዘመናዊው አለምም፣ እርሱ እና አባቱ ለረጅም ጊዜ ተስፋ የተደረገበትን “የዘመናት ፍጻሜን” (ኤፌሶን 1፥10) በማስተዋወቅ ለብላቴና ጆሴፍ ስሚዝ ተገለጡ።

ህያው ክርስቶስን በተመለከተ ጆሴፍ ስሚዝ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ዓይኖቹም እንደ እሳት ነበልባል ነበሩ፤ የራሱ ጠጕርም እንደ ንጹህ በረዶም ነጭ ነበር፤ ፊቱም ከብርቱ የጸሀይ ብርሀን በላይ የሚያበራ ነበር፤ ድምፁም እንዲህ የሚል እንደ ብዙ ውኃዎች ድምፅ፣ እንዲሁም የያህዌህ ድምፅ ነበር፥

“እኔ ፊተኛውና ኋለኛው ነኝ፤ እኔ ህያውም ነኝ፣ የተገደልኩትም እኔ ነኝ፤ እኔም በአብ ዘንድ አማላጃችሁ ነኝ” (ት. እና ቃ. 110፥3–4)።

ስለእርሱም ነቢዩ እንዲህ አውጇል፦ “እናም አሁን፣ ስለ እርሱ ከተሰጡት ብዙ ምስክሮች በኋላ፣ ይህም በመጨረሻ ስለ እርሱ የምንሰጠው ምስክርነት፥ እርሱ ህያው መሆኑን ነው!

“በእግዚአብሔር ቀኝ አይተነዋልና፤ እናም እርሱ የአብ አንድያ ልጅ እንደሆነም ሲመሰክርም ድምፅ ሰምተናል—

“አለማትም በእርሱ፣ እናም በእርሱም አማካይነት፣ እናም ከእርሱም ዘንድ ናቸው እናም ተፈጥረዋል፣ እናም ነዋሪዎችዋም የእግዚአብሔር ወንዶችና ሴቶች ልጆች ናቸው” (ት. እና ቃ. 76፥22–24)።

እኛም የእርሱ ክህነት እና ቤተክርስቲያኑ “በሐዋርያት እና በነቢያት መሠረት [ታንጸው]፣ የማዕዘኑም ራስ ድንጋይ ክርስቶስ ኢየሱስ [ሆኖ]” (ኤፌሶን 2፥20) በምድር ላይ በዳግም እንደተመለሱ በክብር እናውጃለን።

አንድ ቀን ወደ ምድር እንደሚመለስም እንመሠክራለን። “የእግዚአብሔር ክብር ይገለጣል፣ ሥጋ ለባሹም ሁሉ በአንድነት ያየዋል” (ኢሳይያስ 40፥5)። እንደ ነገስታት ንጉስ ይገዛል እናም እንደ ጌቶች ጌታ ይነግሳል፣ ጉልበትም ሁሉ ይንበረከካል ምላስም ሁሉ በእርሱ ፊት በአምልኮ ይናገራል። እያንዳንዳችንም እንደ ሥራችን እና እንደ ልባችን መሻት በእርሱ ይፈረድብን ዘንድ እንቆማለን።

በእርሱ በትክክል እንደተሾምን ሐዋርያት፣ ኢየሱስ ህያው ክርስቶስ፣ የእግዚአብሔር የማይሞት ልጅ እንደሆነ እንመሰክራለን። እርሱም ዛሬ በአባቱ ቀኝ የሚገኘው ታላቅ ንጉስ አማኑኤል ነው። እርሱም የዓለም ብርሃን፣ ህይወት እና ተሰፋ ነው። የእርሱም መንገድ በዚህ ዓለም ወደ ደስታ እና በሚመጣው አለም ወደ ዘለዓለማዊ ህይወት የሚመራ ነው። ወደር የለሽ ለሆነ መለኮታዊ ልጁ ስጦታ እግዚአብሔር ይመስገን።

ቀዳሚ አመራር

ምስል
ፊርማዎች

ጥር ፩ ቀን 2000 (እ.አ.አ)

የአሥራ ሁለቱ ሐዋርያት ሸንጎ

ምስል
ፊርማዎች
ምስል
ፊርማዎች