2014 (እ.አ.አ)
አገልግሎት እና ዘለአለማዊ ህይወት
ማርች 2014


የቀዳሚ አመራር መልእክት፣ መጋቢት 2014 (እ.አ.አ)

አገልግሎት እና ዘለአለማዊ ህይወት

ምስል
ፕሬዘደንት ሔንሪ ቢ. አይሪንግ

አዳኛ ራሰ ውዳድ ያልሆነ አገልግሎት በመስጠት የእኛ ምሳሌ ነው። ፍጹም የሆነው ህይወቱ የሰማይ አባትን እና ሁሉንም የአባቱን ልጆች ለማገልገል የተሰዋ ነበር። የአብ እና የወልድ የጋራ አላማ የህያውነትን ስጦታ እና የዘለአለማዊ ህይወት በረከትን ለሁላችንም ለመስጠት ነው (ሙሴ 1፥39)።

ለዘለአለማዊ ህይወት ብቁ ለመሆን፣ በኢየሱስ ክርስቶሰ የሀጢያት ክፍያ መለወጥ፣ እንደገና መወለድ እና ከሀጢያት መንጻት አለብን። ቢሆንም፣ ከስምንት አመት በታች ያሉ ህጻናት ያለ ሀጢያት ናቸው እናም በሀጢያት ክፍያው ተበዥተዋል (ሞዛያ 3፥16፣ 21ሞሮኒ 8፥10–12)።

በተጠያቂነት እድሜ ለደረስን ሁሉ ፣ ከሀጢያት ለመንጻት የሚያስችል እና ለዘለአለማዊ ህይወት የሚያዘጋጅ ድንቅ እቅድ አለ። ያም ዝግጅት በክህነት ስልጣን ጥምቀት እና መንፈስ ቅዱስን በመቀበል ይጀምራል። ከዛም ሁሌ አዳኝን ማስታወስ እና የሰጠንን ትእዛዛት መጠበቅ ይኖርብናል።

በኢየሱስ ክርስቶስ የሀጢያት ክፍያ አማካኝነት የሚመጣውን የይቅር መባል የደስታ ስሜት ንጉስ ቢንያም በመጽሐፈ ሞርሞን ውስጥ ለህዝቡ ነገራቸው። ከዚያም የሀጢያታቸውን ስርየት ይዘው ለመቆየት፣ ልጆቻቸውን እርስ በእርስ አገልግሎት እንዲሰጣጡ ማስተማር እንዳለባቸው እና በአከባቢያቸው ያሉትን ሰዎች ጊዜያዊ እና መንፈሳዊ ፍላጎታቸውን ለማሟላት በጎ አድራጊዎች መሆን እንዳለባቸው አስተማራቸው። (ሞዛያ 4፥11–16 ተመልከቱ።)

እንደዚህም አስተማራቸው፣ “እናም እነሆ፣ ጥበብን ትማሩ ዘንድ እነዚህን ነገሮች እናገራችኋለሁ፤ እናንተ ሰዎችን በምታገለግሉ ጊዜ እግዚአብሄርን እያገለገላችሁ እንደሆነ እርግጠኛ ትሆናላችሁ” (ሞዛያ 2፡17)

ኢየሱስ ወንጌሉን እያስተማረ እና መልካም እያደረገ ተጓዘ (የሐዋርያት ስራ 10፥38 ተመልከቱ)። ህሙማንን ፈወሰ። ሙታንን አስነሳ። በተራቡና ያለ ምግብ በሆኑ ጊዜ በሀይሉ ሺዎችን መገበ (የማቴዎስ ወንጌል 14፥14–21የዮሐንስ ወንጌል 6፥2–13)። ከትንሳኤው በኋላ ወደ ገሊላ ባህር ዳርቻ በደረሱ ጊዜ ለብዙ ሐዋርያቶቹ ምግብ ሰጣቸው (የዮሐንስ ወንጌል 21፥12–13)። በአሜሪካ፣ ህሙማንን ፈወሰ እና ልጆችን አንድ በአንድ ባረካቸው (3ኛ ኔፊ 17፥7–9፣21)።

ሌሎችን የማገልገል ፍላጎት ጌታ ለእኛ ላደረገው ነገር አመስጋኝ ከመሆን የሚመነጭ እንደሆነ ሐዋርያው ያዕቆብ አስተምሮናል።

“ነገር ግን ነጻ የሚያወጣውን ፍጹሙን ሕግ ተመልክቶ የሚጸናበት፣ ሥራንም የሚሰራ እንጂ ሰምቶ የሚረሳ ያልሆነው፣ በሥራው የተባረከ ይሆናል። …

“ንጹሕ የሆነ ነውርም የሌለበት አምልኮ በእግዚአብሔር አብ ዘንድ ይህ ነው፤ ወላጆች የሌላቸውን ልጆች፣ ባልቴቶችንም በመከራቸው መጠየቅ፣ በዓለምም ከሚገኝ እድፍ ሰውነቱን መጠበቅ ነው” (የያዕቆብ መልእክት 1፥25፣ 27)።

ቀጣይነት ያለው ሌሎችን ለአዳኝ የማገልገል ፍላጎት እየነጻችሁ እንደሆነ የሚያሳይ አንዱ ማረጋገጫ ነው። የቤት ለቤት ትምህርት እና የሴቶች የቤት ለቤት ጉብኝት የበለጠ የደስታ እና ያነሰ የድግግሞሽ ስራ ይሆናል። በአካባቢው ባለ ትምህርት ቤት ውስጥ ብዙ ጊዜ በፍቃደኝነት ስታገለግሉ ወይም በመንደራችሁ ውስጥ ያሉ ድሆችን በመንከባከብ ስትረዱ እራሳችሁን ታገኛላችሁ። አነስተኛ ላላቸው ሰዎች ለመስጠት ጥቂት ገንዘብ ቢኖራችሁም እንኳን፣ ብዙ መስጠት ትችሉ ዘንድ ብዙ እንዲኖራችሁ ትመኙ ነበር (ሞዛያ 4፥24 ተመልከቱ)። ልጆቻችሁን ለማገልገል እና ሌሎችን እንዴት ማገልገል እንዳለባቸው ለማሳየት ስትጓጉ እራሳችሁን ታገኛላችሁ።

ተፈጥሮአችሁ ሲቀየር፣ ካለ ታዋቂነት የበለጠ አገልግሎት ለመስጠት ፍላጎት ይሰማችኋል። ከእግዚአብሔር እና ከልጆቻቸው ውጪ ማንም ሳያውቅ ትልቅ የገንዘብ እና የአገልግሎት ስጦታዎችን ያበረከቱ የአዳኙን ደቀመዝሙሮች አውቃለው። በዚህ ህይወት ውስጥ እነሱን በመባረክ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ተቀብሏል፣ እና በሚመጣው ዘለአለማዊ ህይወትም ይባርካቸዋል (የማቴዎስ ወንጌል 6፥1–43ኛ ኔፊ 13፥1–4)።

ሌሎችን የማገልገል ትእዛዝን ስለጠበቃችሁ (የማቴዎስ ወንጌል 22፥39 ተመልከቱ)፣ የኩራተኝነት ስሜቶቻችሁ ውስጥ ለውጥ ተሰምቷችኋል። ሐዋርያቶቹ ከመካከላቸው ማን ታላቅ እንደሚሆን ሲከራከሩ አዳኙ እርምት ሰጣቸው። እንዲህም አለ፧

“ሊቃችሁ አንድ እርሱም ክርስቶስ ነውና፣ ሊቃውንት ተብላችሁ አትጠሩ።

“ከእናንተም የሚበልጠው አገልጋያችሁ ይሆናል” (የማቴዎስ ወንጌል 23፥10–11)።

ሌሎችን ለማገልገል እንዴት መማር እንደምንችል አዳኛችን ያስተምረናል። ፍጹም በሆነ መልኩ አገለገለ፣ እርሱ ቀስ በቀስ እንደተማረው እኛም ለማገልገል መማር አለብን (1. ት. እና ቃ. 93፥12–13)። እኛ በምንሰጠው አገልግሎት፣ የበለጠ እንደእርሱ መሆን እንችላለን። እሱ እንደሚወዳቸው ሁሉ እኛም ጠላቶቻችንን እንወድ ዘንድ በሙሉ የልቦቻችን አቅም እንጸልያለን (የማቴዎስ ወንጌል 5፥43–44ሞሮኒ 7፥48)። ከዛም በስተመጨረሻ ከእርሱ እና ከሰማይ አባታችን ጋር ለዘለአለማዊ ሕይወት ብቁ ለመሆን እንችል ይሆናል።

የአዳኛችንን ትምህርቶች እና ምሳሌ ስንከተል፣ የበለጠ ፍጹም በሆነ ሁኔታ እያገለገልን መምጣት እንደምንችል ቃል እገባለሁ።

ከዚህ መልእክት ማስተማር

የአስራ ሁለቱ ሐዋርያት ቡድን አባል የሆኑት ሽማግሌ ኤም. ራስል ባላርድ እንዲህ በማለት ለአገልግሎት እድሎችን ለማግኘት እንድንጸልይ አበረታተውናል፤ “በእያንዳንዱ አዲስ ቀን የጠዋት ጸሎታችሁ ላይ፣ የሰማይ አባት ውድ ልጆቹን የማገልገል እድልን ታስተውሉ ዘንድ እንዲመራችሁ ጠይቁ። ከዛም ቀኑን ሙሉ አንድን ሰው ለመርዳት እየፈለጋችሁ ሂዱ” (“Be Anxiously Engaged,” Ensign or Liahona, Nov. 2012, 31). የምታስተምሯቸውን ሰዎች በእየ ጠዋቱ ለማገልገል እድሎችን ለማግኘት እንዲጸልዩ እናም ከዛ አጋጣሚዎቹን ቀኑን ሙሉ ለመፈለግ እቅድ እንዲይዙ መጋበዝን አስቡበት።