ቅዱሳት መጻህፍት
፪ ኔፊ ፳


ምዕራፍ ፳

የአሶር መጥፋት ኃጢአተኞች በዳግም ምፅአት እንደሚጠፉት ምሳሌ ነው—ጌታ እንደገና ከመጣ በኋላ ጥቂት ሰዎች ይቀራሉ—የያዕቆብ ቅሪቶች በዚያን ቀን ይመለሳሉ—ኢሳይያስ ፲ን አነጻፅሩ። ከ፭፻፶፱–፭፻፵፭ ም.ዓ. ገደማ።

ጻድቅ ያልሆኑ ሕጎችን ለሚደነግጉ፣ የጻፉአቸውን የግፍን ትእዛዛት ለሚያዝዙ ወዮላቸው፤

ፍትህ የሚፈልጉትን ለመከልከል፣ እናም የድሃ ሕዝቦቼን መብት ለመውሰድ፣ መበለቶችንም ሰለባቸው እንዲሆኑላቸው፣ እናም አባት አልባዎችን ለመዝረፍ ዘንድ የግፍን ትእዛዛት አዝዘዋል!

እናም ከሩቅ በሚመጡት በመጎብኘታችሁና በመውደሚያችሁ ቀን ምን ታደርጋላችሁ? ለእርዳታስ ወደ ማን ትሸሻላችሁ? ክብራችሁንስ ወዴት ትተዋታላችሁ?

ከእኔ ውጭ ከእስረኞች በታች ይጎነበሳሉ፣ በሚገደሉትም መካከል ይወድቃሉ። በዚህም ሁሉ እንኳን ጌታ ቁጣው አልበረደችም፣ ነገር ግን አሁንም ገና እጁ ተዘርግታለች።

ሶርያ ሆይ፣ የቁጣዬ በትር፣ እናም በእጃቸው ያለው መሳሪያ ቁጣቸው ነው።

በግብዝ ሀገሮችም መካከል እልከዋለሁ፣ እናም ምርኮንና ብዝበዛውንም ይወስድ ዘንድ፣ እና እንደ አደባባይ ጭቃ የተረገጡ ይሆኑ ዘንድ በተቆጣሁአቸው ህዝብ ላይ እልከዋለሁ።

ነገር ግን እርሱ ይህን አላቀደውም፣ ልቡም ቢሆን እንደዚህ አያስብም፤ በልቡ ውስጥ ያለው ግን ብዙ ሀገሮችን ለማጥፋትና ለመቁረጥ ነው።

እንዲህ ይላል፥ መሳፍንቶቼ ሁሉ ነገሥታት አይደሉምን?

ካልኖ እንደ ከርከሚሽ አይደለችምን? ሐማትስ እንደ አርፋድ አይደለችምን? ሰማርያስ እንደ ደማስቆ አይደለችምን?

የተቀረፁ ምስሎቻቸው ከኢየሩሳሌምና ከሰማርያ ምስሎች የበለጡትን፣ የጣዖቶችን መንግስታት እጄ እንዳገኘች፤

፲፩ በሰማርያና በጣዖቶቿ እንደአደረግሁት በኢየሩሳሌምና በጣዖቶቿ አላደርግምን?

፲፪ ስለዚህ እንዲህ ይሆናል ጌታ ስራውን በሙሉ በፅዮን ተራራና በኢየሩሳሌም ሲፈፅም፣ የአሶርን ንጉስ የኩሩ ልብ ፍሬውን የዐይኑንም ከፍታ ትምክህት እቀጣለሁ።

፲፫ እርሱ እንዲህ ብሎአልና፤ በእጄ ጥንካሬና በጥበቤ እነዚህን ነገሮች አድርጌአለሁ፤ እኔ አስተዋይ ነኝና፤ የህዝቦችንም ድንበር ገፋሁ፣ ሀብታቸውንም ዘረፍኩ፣ እናም እንደ ጀግና ሆኜ ፍጥረታትን አጠቃሁ፤

፲፬ እናም እጄ የህዝብን ሀብት እንደ ወፍ ጎጆ አገኘች፤ እና በሰው የተተዉትን እንቁላሎች እንደሚሰበስብ እኔም ደግሞ ምድርን በሞላ ሰበሰብኩ፤ ክንፉን የሚያራግብ፣ ወይም አፉን የሚከፍትም ሆነ የሚጮህ ማንም የለም።

፲፭ ምሳር የሚጠቀምበትን ሰው እበልጣለሁ ብሎ ይመካልን? ወይስ መጋዝ በሚስበው ላይ እራሱን ያጎላልን? በትርስ በራሱ ያለእጅ እራሷን እንደምትነቀንቅ ወይንም ከዘራ እንጨት እንዳልሆነ ሁሉ እራሱን እንደሚያነሳ!

፲፮ ስለዚህ ጌታ፣ የሰራዊት ጌታ፣ በወፍራሞቹ ላይ መክሳትን ይልካል፣ ከክብሩም በታች እንደ እሳት መቃጠል የሆነ ቃጠሎን ያስነሳል።

፲፯ እናም የእስራኤል ብርሃን ለእሳት ይሆናል፣ ቅዱሷም ነበልባል ይሆናል፣ እሾሁንና ኩርንችቱንም በአንድ ቀን ያቃጥለዋል፣ ይበላዋልም፤

፲፰ እናም የዱሩንም፣ የፍሬያማውን ሜዳ፣ ክብሩንም፣ ነፍሱንና ስጋውንም ያቃጥለዋል፤ እነርሱ አርማ ተሸካሚው እንደ ወደቀ ይሆናሉ።

፲፱ እናም የተቀሩትም የዱር ዛፎቹ ህፃን መቁጠር እስኪችላቸው ድረስ ትንሽ ይሆናሉ።

እናም በዚያ ቀን እንዲህ ይሆናል፣ የእስራኤል ቅሪት፣ እናም ከያዕቆብ ቤት የዳኑት፣ ከእንግዲህ ወዲህ በዚያ በመታቸው ላይ አይቆዩም፣ ነገር ግን በጌታ በእስራኤሉ ቅዱስ በእውነት ይመካሉ።

፳፩ ቅሪቶች ይመለሳሉ፣ አዎን፣ የያዕቆብም ቅሪቶች ቢሆኑ እንኳ፣ ወደ ኃያሉ እግዚአብሔር ይመለሳሉ።

፳፪ እስራኤል ሆይ ህዝብሽ እንደ ባህር አሸዋ የበዛ ቢሆንም እንኳ፣ ቅሪቶቻቸው ይመለሳሉ፤ የተነገረውም ጥፋት በፅድቅ ይትረፈረፋል

፳፫ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር ያለቀ የተቈረጠ ነገርን በምድር ሁሉ መካከል ይፈጽማል።

፳፬ ስለዚህ፣ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል—በፅዮን የምትኖሩ ህዝቤ ሆይ፣ አሶርን አትፍራው፤ በበትር ይመታሀል፣ ግብፅም እንዳደረገው ዘንጉን ያነሳብሀል።

፳፭ ቁጣዬ እስኪፈፀም መዓቴም እስኪያጠፋቸው ጥቂት ጊዜ ቀርቷል።

፳፮ እናም የሰራዊት ጌታ ምድያምን በሔሬብ አለት በኩል እንደመታው ጅራፍ ያነሳበታል፣ በትሩም በባህር ላይ ይሆናል፣ በግብፅም እንዳደረገው ያነሳዋል።

፳፯ እናም እንዲህ ይሆናል፣ በዚያን ቀን ሸክሙ ከትከሻህ ላይ ይነሳል፣ ቀንበሩም ከአንገትህ ላይ ይወርዳል፣ ከቅባቱም የተነሳ ቀንበሩም ይጠፋል።

፳፰ ወደ አንጋይ መጥቷል፣ በሜጌዶን አልፏል፤ በማክማስም እቃውን አስቀምጧል።

፳፱ እነርሱ መተላለፊያውን አልፈዋል፤ ማረፊያቸውንም በጌባ አድርገዋል፤ ራማትም ፈርታለች፤ የሳኦል ጊብአም አምልጣለች።

የጋሊም ልጅ ሆይ፤ ደሀዋ አናቶት ሆይ፣ ለሌሳ እንኳን እስኪሰማ ድረስ ድምፅሽን ከፍ አድርጊ።

፴፩ መደቤና ሸሽታለች፤ የግቤር ህዝቦችም ሊያመልጡ እራሳቸውን ሰብስበዋል።

፴፪ ነገር ግን በዚያን ቀን በኖብ ላይ ይቀራል፤ በፅዮን ሴት ልጆች ተራራ በኢየሩሳሌም ኮረብታ ላይ እጆቹን ያነቃንቃል።

፴፫ እነሆ፣ ጌታ፣ የሰራዊት ጌታ ቅርንጫፎቹን በሚያስፈራ ኃይል ይቆርጣቸዋል፤ እናም በቁመናቸው ከፍ ያሉት ይቆረጣሉ፤ እብሪተኞቻቸው ዝቅ ይላሉ።

፴፬ ጥቅጥቅ ያለውንም ጫካ እርሱ በብረት ይቆርጠዋል፣ ሊባኖስም በኃይለኛው እጅ ትወድቃለች።