የሚስዮን ጥሪዎች
ምዕራፍ 3፥ ትምህርት 2—የሰማይ አባት የደህንነት እቅድ


“ምዕራፍ 3፥ ትምህርት 2—የሰማይ አባት የደህንነት እቅድ” ወንጌሌን ስበኩ፡ የኢየሱስ ክርስቶስን ወንጌል ለማካፈል መመርያ 2023 (እ.አ.አ)

“ምዕራፍ 3፥ ትምህርት 2” ወንጌሌን ስበኩ

ምዕራፍ 3፥ ትምህርት 2

የሰማይ አባት የደህንነት እቅድ

ምስል
ክርስተስ ሃውልት

ሰዎች ሊጠይቁ ይችላሉ

  • የህይወት አላማ ምንድን ነው?

  • ከየት ነው የመጣሁት?

  • ስለ እኔ የሚያስብ አምላክ አለ? እሱስ እንደሚያስብልኝ እንዴት ሊሰማኝ ይችላል?

  • ብዙ መጥፎ ነገሮች ሲከሰቱ በእግዚአብሄር እንዴት ማመን እችላለሁ?

  • አንዳንድ ጊዜ ሕይወት በጣም ከባድ የሚሆነው ለምንድነው? በእነዚህ ጊዜያት ጥንካሬን እንዴት ማግኘት እችላለሁ?

  • የተሻለ ሰው እንዴት መሆን እችላለሁ?

  • ከሞትኩ በኋላ ምን ይሆናል?

ዳግም የተመለሰው የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል ጠቃሚ የሆኑ የነፍስ ጥያቄዎችን እንድንመልስ ይረዳናል። በወንጌል አማካኘት፣ ስለ መለኮታዊ ማንነታችን እና እንደ የእግዚአብሔር ልጆች ስላለን ዘላለማዊ አቅም እንማራለን። ወንጌል ተስፋን ይሰጠናል እንዲሁም ሰላምን፣ ደስታን እና ትርጉም እንድናገኝ ይረዳናል። ወንጌልን መኖር የህይወት ፈተናዎችን በምንጋፈጥበት ጊዜ እንድናድግ እና ብርታት እንድናገኝ ይረዳናል።

እግዚአብሔር ለልጆቹ መልካሙን ይፈልጋል እንዲሁም የእርሱን ታላቅ በረከቶች ፣ እነሱም ያለመሞትን እና የዘላለም ህይወትን ሊሰጠን ይፈልጋል (ሙሴ 1፡39ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 14፡7 ተመልከቱ)። እርሱ ስለሚወደን፣ እነዚህን በረከቶች የምንቀበልበትን እቅድ አዘጋጅቶልናል። በቅዱሳት መጻህፍት ውስጥ፣ ይህ እቅድ የደህንነት እቅድ፣ ታላቁ የደስታ እቅድ እና የቤዛነት እቅድ ተብሎ ይጠራል (አልማ 42፡5፣ 8፣ 11፣ 13፣ 15፣ 16፣ 31 ተመልከቱ)።

በእግዚአብሔር እቅድ ውስጥ፣ እያንዳንዳችን በቅድመ ምድር ህይወት፣ በመወለድ፣ በምድራዊ ህይወት፣ በሞት እና ከሞት በኋላ ባለው ህይወት ውስጥ ጉዞ እናደርጋለን። ከሞትን በኋላ፣ ወደ እርሱ መገኘት እንድንመለስ እና የደስታን ሙላትን እንድናገኝ በዚህ ጉዞ ውስጥ እግዚአብሔር የሚያስፈልገንን ሰጥቶናል።

ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር እቅድ ዋና ክፍል ነው። በኃጢያት ክፍያው እና በትንሳኤው፣ ኢየሱስ እያንዳንዳችን ያለመሞትን እና የዘላለም ህይወትን እንድንቀበል አስችሎናል።

በምድር ላይ ባለንበት ጊዜ፣ የቅድመ ምድር ህይወታችንን አናስታውስም። ከሞት በኋላ ያለውን ሕይወትም በሙሉ አንረዳም። ሆኖም ግን፣ እግዚአብሔር ስለ እነዚህ የዘላለም ጉዟችን ክፍሎች ብዙ እውነቶችን ገልጧል። እነዚህ እውነቶች የህይወትን አላማ እንድንረዳ፣ ደስታን እንድናገኝ እና ወደፊት በሚመጡ መልካም ነገሮች ላይ ተስፋ እንዲኖረን በቂ እውቀት ይሰጡናል። ይህ እውቀት በምድር ሳለን የሚመራን ቅዱስ ሀብት ነው።

ለማስተማር የቀረቡ ሃሳቦች

ይህ ክፍል ለማስተማር ለመዘጋጀት የሚረዳችሁን ምሳሌዎች ዝርዝር ያቀርባል። እንዲሁም ልትጠቀሙባቸው የምትችሏቸው የጥያቄዎች እና የግብዣዎች ምሳሌዎችን ያካትታል።

ለማስተማር ስትዘጋጁ፣ የእያንዳንዱን ሰው ሁኔታ እና መንፈሳዊ ፍላጎቶች በጸሎት አስቡ። ለማስተማር በጣም ጠቃሚ የሚሆነውን ወስኑ። ሰዎች ሊረዷቸው የማይችሉትን ቃላት ለማብራራት ተዘጋጁ። ትምህርቶቹን አጭር ማድረግን በማስታወስ ምን ያህል ጊዜ እንደሚኖራችሁ አቅዱ።

በምታስተምሩበት ጊዜ የምትጠቀሙባቸውን ጥቅሶች ምረጡ። የትምህርቱ “ትምህርታዊ መሰረት” ክፍል ብዙ አጋዥ ጥቅሶችን ያካትታል።

በምታስተምሩበት ጊዜ የትኞቹን ጥያቄዎች መጠየቅ እንዳለባችሁ አስቡ። እያንዳንዱ ግለሠብ እርምጃ እንዲወስድ የሚያበረታታ ግብዣዎችን ለመጋበዝ አቅዱ።

እግዚአብሔር ስለገባቸው በረከቶች አጽንኦት ስጡ፣ እንዲሁም ስለምታስተምሩት ነገር ምስክርነታችሁን አካፍሉ።

ምስል
ሚስዮናውያን ቤተሰብን ሲያስተምሩ

በ15-25 ደቂቃ ውስጥ ለሰዎች ማስተማር የምትችሉት ነገር

ስለ ደህንነት እቅድ ለማስተማር ከሚከተሉት መርሆች አንዱን ወይም ከዚያ በላይ ምረጡ። የእያንዳንዱ መርህ ትምህርት መሠረት ከዚህ ዝርዝር በኋላ ቀርቧል።

የቅድመ ምድር ህይወት፥ እግዚአብሔር ለእኛ ያለው አላማ እና እቅድ

  • ሁላችንም የእግዚአብሔር የመንፈስ ልጆች ነን። እርሱ በራሱ አምሳል ፈጥሮናል።

  • በምድር ላይ ከመወለዳችን በፊት ከእግዚአብሔር ጋር ኖረናል። እኛ የእሱ ቤተሰብ አባላት ነን። እያንዳንዳችንን ያውቃል እንዲሁም ይወደናል።

  • በዚህ እና በዘላለማዊ ህይወት ውስጥ ለደስታችን እና ለእድገታችን እግዚአብሔር እቅድን አዘጋጅቷል።

  • በቅድመ ምድር ህይወታችን፣ የእግዚአብሔርን እቅድ ለመከተል መረጥን። ይህም ወደ ምድር በመምጣት ለዘላለማዊ እድገታችን ቀጣዩን እርምጃ መውሰድ ማለት ነው።

  • ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር እቅድ ዋና ክፍል ነው። እርሱ የማይሞት እና ዘላለማዊ ሕይወት እንዲኖረን ያደርገናል።

ፍጥረት

  • በእግዚአብሔር አመራር ኢየሱስ ክርስቶስ ምድርን ፈጠረ።

የአዳምና ሔዋን ውድቀት

  • አዳምና ሔዋን ወደ ምድር ከመጡት የእግዚአብሔር የመንፈስ ልጆች መካከል የመጀመሪያዎቹ ናቸው። እግዚአብሔር አካላቸውን ፈጠረ እንዲሁም በኤደን ገነት ውስጥ አኖራቸው።

  • አዳምና ሔዋን በመተላለፋቸው ምክንያት ከገነት ተባረሩ፣ ከእግዚአብሔርም መገኘት ተለዩ። ይህም ድርጊት ውድቀት ተብሎ ይጠራል።

  • ከውድቀቱ በኋላ አዳምና ሔዋን ሟች ሆኑ። እንደ ሟች፣ መማር፣ መሻሻል እና ልጆችን መውለድ ቻሉ። በተጨማሪም ሐዘን፣ ኃጢአትና ሞት ገጠማቸው።

  • ውድቀት ለሰው ልጆች ወደፊት አንድ እርምጃ ነበር። ውድቀት በምድር ላይ እንድንወለድ እና በሰማይ አባት እቅድ እንድናድግ አስችሎናል።

የምድር ላይ ህይወታችን

  • በእግዚአብሔር እቅድ ሥጋዊ አካልን ለመቀበል፣ ለመማር እና ለማደግ ወደ ምድር መምጣት አስፈለገን።

  • በምድር ላይ በእምነት መራመድን እንማራለን። ሆኖም ግን የሰማይ አባታችን ብቻችንን አልተወንም። ወደ እርሱ መገኘት እንድንመለስ የሚረዱን ብዙ ስጦታዎችን እና መመሪያዎችን ሰጥቷል።

የኢየሱስ ክርስቶስ የኃጢያት ክፍያ

  • እያንዳንዳችን ኃጢአት እንሠራለን እንዲሁም እያንዳንዳችን እንሞታለን። እግዚአብሔር ስለወደደን ከኃጢአትና ከሞት እንዲቤዠን ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን ወደ ምድር ልኮልናል።

  • በኢየሱስ የሃጥያት ክፍያ መስዋዕትነት ምክንያት፣ ምህረትን ማግኘት እና ከኃጢአታችን መንጻት እንችላለን። ንስሐ ስንገባ ልባችን ለመልካም ሊለወጥ ይችላል። ይህ ወደ እግዚአብሔር መገኘት እንድንመለስ እና የደስታ ሙላትን እንድንቀበል ያስችለናል።

  • በኢየሱስ ትንሳኤ ምክንያት፣ ከሞትን በኋላ ሁላችንም እንደገና እንነሳለን። ይህ ማለት የእያንዳንዱ ግለሠብ መንፈስ እና አካል እንደገና ይገናኛሉ እንዲሁም እያንዳንዳችን ፍፁም በሆነ በትንሣኤ አካል ለዘላለም እንኖራለን ማለት ነው።

  • ኢየሱስ ክርስቶስ መጽናናትን፣ ተስፋን እና ፈውስን ይሰጣል። የሃጢያት ክፍያ መስዋዕቱ የፍቅሩ የመጨረሻ መግለጫ ነው። በህይወት ፍትሃዊ ያልሆኑ ነገሮች በሙሉ በኢየሱስ ክርስቶስ የኃጢያት ክፍያ በኩል ሊስተካከሉ ይችላሉ።

የመንፈስ አለም

  • ሥጋዊ አካላችን ሲሞት መንፈሳችን በመንፈሳዊው ዓለም ውስጥ መኖር ይቀጥላል። ይህ ከትንሣኤ በፊት ጊዜያዊ የመማር እና የመዘጋጃ ሁኔታ ነው።

  • የኢየሱስ ክርስቶስን ወንጌል በመንፈሳዊው ዓለም እንማራለን እናም እያደግን እና እየተሻሻልን መቀጠል እንችላለን።

ትንሳኤ፣ መዳን እና ከፍ ከፍ መደረግ

  • በመንፈሳዊው ዓለም ከሚኖረን ጊዜ በኋላ፣ ትንሳኤ የዘላለም ጉዟችን ቀጣይ እርምጃ ነው።

  • ትንሳኤ የመንፈሳችን እና የአካላችን ዳግም መገናኘት ነው። እያንዳንዳችን ከሞት እንነሳለን እንዲሁም ፍጹም የሆነ ሥጋዊ አካል ይኖረናል። ለዘላለምም እንኖራለን። ይህ ሊሆን የቻለው በአዳኙ የሀጢያት ክፍያ እና ትንሳኤ አማካኝነት ነው።

ፍርድ እና የክብር መንግስታት

  • ከሞት ስንነሳ ኢየሱስ ክርስቶስ ፈራጃችን ይሆናል። ከጥቂቶች በስተቀር፣ ሁሉም የእግዚአብሔር ልጆች በክብር መንግሥት ውስጥ ቦታ ይኖራቸዋል።

  • ምንም እንኳን ሁላችንም ከሞት ብንነሳም ሁላችንም አንድ አይነት ዘላለማዊ ክብርን አንቀበልም። ኢየሱስ በስጋ እና በመንፈስ አለም በነበረን እምነታችን፣ ስራችን እና ንስሃ በገባነው መሰረት ይፈርድብናል። ታማኝ ከሆንን በእግዚአብሔር ፊት ለመኖር ዳግም መመለስ እንችላለን።

ሰዎችን ልትጠይቋቸው የምትችሏቸው ጥያቄዎች

የሚከተሉት ጥያቄዎች ሰዎችን ልትጠይቋቸው የምትችሏቸው ምሳሌዎች ናቸው። እነዚህ ጥያቄዎች ትርጉም ያለው ውይይቶችን እንድታደርጉ እና የአንድን ግለሠብ ፍላጎቶች እና አመለካከቶች እንድትረዱ ያግዛሉ።

  • የሕይወት ዓላማ ምን እንደሆነ ይሰማችኋል?

  • ደስታን የሚያመጣላችሁ ምንድነው?

  • እግዚአብሔር እንዲረዳችሁ የምትፈልጉት በየትኞቹ ፈተናዎቻችሁ ነው?

  • ካጋጠሟችሁ ፈተናዎች ምን ተማራችሁ?

  • ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ምን ታውቃላችሁ? የእርሱ ህይወት እና ተልዕኮ በህይወታችሁ ላይ ምን ተጽዕኖ አሳድሯል?

ልታቀርቧቸው የምትችሏቸው ግብዣዎች

  • ያስተማርነው እውነት መሆኑን እንድታውቁ እግዚአብሄርን በጸሎት ትጠይቃላችሁ? (በትምህርት 1 የመጨረሻ ክፍል ላይ ያለውን “ለማስተማር የሚሆን ሐሳብ፡ ጸሎት” ተመልከቱ።)

  • ስላስተማርነው ነገር የበለጠ ለማወቅ በዚህ እሁድ ከእኛ ጋር ወደ ቤተ ክርስቲያን ትሄዳላችሁ?

  • መፅሐፈ ሞርሞንን በማንበብ የእግዚአብሔር ቃል መሆኑን ለማወቅ ትጸልያላችሁ? (የተወሰኑ ምዕራፎችን ወይም ቁጥሮችን ልትጠቁሙ ትችላላችሁ።)

  • የኢየሱስን ምሳሌ በመከተል ትጠመቃላችሁ? (ከትምህርት 1 በፊት ያለውን “የጥምቀት እና የማረጋገጫ ግብዣ” ተመልከቱ።)

  • ለሚቀጥለው ጉብኝት ቀጠሮ መያዝ እንችላለን?

ምስል
የመዳን እቅድ ግራፊክ

የትምህርት መሰረት

ይህ ክፍል የወንጌልን እውቀት እና ምስክርነት ለማጠናከር እና ለማስተማር እንዲረዳችሁ ትምህርት እና ጥቅሶችን እንድታጠኑ ይሰጣችኋል።

ምስል
ጋላክሲዎች

የቅድመ ምድር ህይወት፥ እግዚአብሔር ለእኛ ያለው አላማ እና እቅድ

እኛ የእግዚአብሔር ልጆች ነን፣ ከመወለዳችን በፊት ከእርሱ ጋር ኖረናል።

እግዚአብሔር የመንፈሶቻችን አባት ነው። እኛ በእውነት በእርሱ አምሳል የተፈጠርን ልጆቹ ነን። እያንዳንዳችን እንደ እግዚአብሔር ልጅነታችን መለኮታዊ ተፈጥሮ አለን። ይህ እውቀት በአስቸጋሪ ጊዜያት ውስጥ ሊረዳን እንዲሁም የተሻልን እንድንሆን ሊያነሳሳን ይችላል።

በምድር ላይ ከመወለዳችን በፊት እንደ መንፈስ ልጆቹ ከእግዚአብሔር ጋር እንኖር ነበር። እኛ የእሱ ቤተሰብ አባላት ነን።

ምስል
በፕሬዘደንት ኤም. ራስል ባላርድ

“ሁላችንም አሁን እንዲሁም ለዘላለም የምንጋራው አንድ አስፈላጊ፣ መቼም ልንረሳው የማይገባ እና ልናመሰግን የሚገባን ማንነት አለ። ያ እናንተ በዘላለም ውስጥ ሁሌም መንፈሳዊ ስር ያላችሁ የእግዚአብሔር ወንድ ወይም ሴት ልጅ እንደሆናችሁ ነው።

“… ይህን እውነት መረዳት—በእርግጥም መረዳት እና መቀበል—ህይወትን የሚለውጥ ነው። ማንም ሊነጥቀው የማይችል ልዩ ማንነት ይሰጣችኋል። ነገር ግን ከዚያም በላይ፣ ትልቅ እና ገደብ የለሽ ዋጋ እንዳላችሁ እንዲሰማችሁ ሊያደርግ ይገባል። በመጨረሻም፣ መለኮታዊ፣ የከበረ እና ዋጋ ያለው የህይወት አላማ ይሰጣችኋል” (ኤም ራስል ባላርድ፣ “የሰማይ አባት ልጆች” [ብሪገም ያንግ ዩኒቨርሲቲ ጉባኤ መጋቢት 3፣2020 (እ.አ.አ)]፣ 2፣ speeches.byu.edu)።

ወደ ምድር ለመምጣት መረጥን

የሰማይ አባታችን ይወደናል እንዲሁም እርሱን እንድንመስል ይፈልጋል። እርሱ የከበረ አካል ያለው እና ከፍ ያለ ነው።

በቅድመ ምድር ሕይወታችን፣ እግዚአብሔር እርሱን እንድንመስል ለኛ እቅድ እንዳለው ተምረናል። የእቅዱ አንዱ አካል ሰማያዊውን ቤታችንን ትተን ወደ ምድር እንድንመጣና ሥጋዊ አካል እንዲኖረን ነው። በተጨማሪ ከእግዚአብሔር መገኘት በራቅንበት ጊዜ ልምድ ማግኘት እና እምነታችንን ማዳበር አስፈልጎናል። ከእግዚአብሔር ጋር መኖራችንን አናስታውስም። ነገር ግን፣ ከእርሱ ጋር ተመልሰን እንድንኖር የሚያስፈልገንን ይሰጠናል።

ነጻ ምርጫ ወይም የመምረጥ ነፃነት እና ችሎታ፣ የእግዚአብሔር እቅድ አስፈላጊ አካል ነው። በቅድመ ምድር ህይወታችን፣ በዘለአለማዊ እድገታችን ቀጣዩን እርምጃ እንድንወስድ እያንዳንዳችን የእግዚአብሄርን እቅድ ለመከተል እና ወደ ምድር ለመምጣት መረጥን። እዚህ ሳለን ለማደግ እና ደስታን ለማግኘት ብዙ አዳዲስ አጋጣሚዎች እንደሚኖሩን ተረድተናል። ተቃውሞ እንደሚገጥመንም ገብቶናል። ፈተና፣ መከራ፣ ሀዘን እና ሞትም ይገጥመናል።

ወደ ምድር ለመምጣት ስንመርጥ፣ በእግዚአብሔር ፍቅር እና እርዳታ ተማምነናል። ለመዳናችን በእርሱ እቅድ ታምነናል።

የሰማይ አባት ኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛችን እንዲሆን መረጠው።

ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር እቅድ ዋና ክፍል ነው። ወደ ምድር ከመምጣታችን በፊት፣ በራሳችን ወደ እግዚአብሔር መገኘት መመለስ እንደማንችል እናውቅ ነበር። የሰማይ አባት ወደ እርሱ እንድንመለስ እና የዘላለም ህይወት እንዲኖረን የበኩር ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን መረጠ።

ኢየሱስም በፈቃደኝነት ተቀበለው። ወደ ምድር ለመምጣት እንዲሁም በእርሱ የኃጢያት ክፍያ መስዋዕትነት ሊያነጻን ተስማማ። የእሱ የኃጢያት ክፍያ እና ትንሳኤ እግዚአብሄር ለእኛ ያለው ዓላማ እንዲፈጸም ያስችለዋል።

የቅዱስ መጽሀፍ ጥናት

የእግዚአብሔር ልጆች

የእግዚአብሔር አላማ

የቅድመ ምድር ህይወት

ስለዚህ መርህ የበለጠ ተማሩ

ምስል
በውቅያኖስ ላይ ፀሐይ ስትጠልቅ

ፍጥረት

የመንፈስ ልጆቹ ሥጋዊ አካላትን እና ልምድን የሚያገኙበትን ምድር ለመፍጠር የሰማይ አባት እቅድ አዘጋጀ። በምድር ላይ ያለን ህይወት እንድናድግ እና እግዚአብሔርን እንድንመስል አስፈላጊ ነው።

በሰማይ አባት መመሪያ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ምድርንና ሕያዋን ፍጥረታትን ሁሉ ፈጠረ። የሰማይ አባት በራሱ አምሳል ወንድን እና ሴትን ፈጠረ። ፍጥረት የእግዚአብሔር ፍቅር እና የማደግ እድል እንዲኖረን ያለውን ፍላጎት መግለጫ ነው።

የቅዱስ መጽሀፍ ጥናት

ስለዚህ መርህ የበለጠ ተማሩ

ምስል
ከኤደን ገነት መውጣት፣ በጆሴፍ ብሪኪ

የአዳምና ሔዋን ውድቀት

ከውድቀት በፊት

አዳም እና ሔዋን ወደ ምድር ከመጡ የሰማይ አባት የመንፈስ ልጆች የመጀመሪያዎቹ ነበሩ። እግዚአብሔር ሥጋዊ አካላቸውን በራሱ አምሳል ፈጥሮ በኤደን ገነት አኖራቸው። በገነት ውስጥ ንጹሐን ነበሩ፤ እግዚአብሔርም የሚያስፈልጋቸውን ይሰጣቸው ነበር።

አዳምና ሔዋን በገነት ሳሉ መልካምንና ክፉን ከሚያሳውቀው ዛፍ ፍሬ እንዳይበሉ እግዚአብሔር አዘዛቸው። ይህንን ትእዛዝ ከታዘዙ በገነት ውስጥ ሊቆዩ ይችላሉ። ሆኖም ግን፣ ከሟችነት ተቃውሞ እና ተግዳሮቶች በመማር መሻሻል አይችሉም ነበር። ሀዘንና ህመም ሊሰማቸው ስለማይችል ደስታን ማወቅ አይችሉም ነበር።

ሰይጣን አዳም እና ሔዋን የተከለከለውን ፍሬ እንዲበሉ ፈተናቸው፣ እናም ይህን ለማድረግ መረጡ። በዚህ ምርጫ ምክንያት ከገነት ተባረሩ እንዲሁም ከእግዚአብሔር መገኘት ተለዩ። ይህም ድርጊት ውድቀት ተብሎ ይጠራል።

ከውድቀት በኋላ

ከውድቀቱ በኋላ አዳምና ሔዋን ሟች ሆኑ። የዋህነታቸው ቀርቶ፣ መልካም እና ክፉን መረዳት ጀመሩ። ከነዚያም መካከል ለመምረጥ ነጻ ምርጫቸውን መጠቀም ይችላሉ። አዳምና ሔዋን ተቃውሞና ፈተናዎች ስለገጠሟቸው መማርና ማደግ ችለዋል። ሀዘን ገጥሟቸው ስለነበር ደስታን ሊያውቁ ቻሉ። ( 2 ኔፊ 2:22–25ን ተመልከቱ)

አዳምና ሔዋን መከራ ቢደርስባቸውም ሟች መሆን ታላቅ በረከት እንደሆነ ተሰምቷቸዋል። አንዱ በረከት ልጆችን መውለድ መቻላቸው ነበር። ይህም ሌሎች የእግዚአብሄር የመንፈስ ልጆች ወደ ምድር እንዲመጡና ሥጋዊ አካል እንዲቀበሉ መንገድ ከፍቷል።

የውድቀትን በረከቶች በተመለከተ አዳምና ሔዋን ተደስተዋል። ሄዋን “ባናጠፋ ኖሮ ዘርም አይኖረንም ነበር፣ እና መልካምና ክፉን፣ እናም የመዳንን ደስታ፣ እናም ለታዛዡ ሁሉ እግዚአብሔር የሚሰጠውን ዘለአለማዊ ህይወትን አናውቅም ነበር” (ሙሴ 5:11፣ በተጨማሪም ቁጥር 10ን ተመልከቱ) በማለት ተናግራለች።

የቅዱሳት መጻህፍት ጥናት

በገነት ውስጥ

ውድቀት

ስለዚህ መርህ የበለጠ ተማሩ

የምድር ህይወታችን

ብዙ ሰዎች “ለምንድነው እዚህ ምድር ላይ ያለሁት?” በማለት ይጠይቃሉ። በምድር ላይ ያለን ህይወት ለዘላለማዊ እድገታችን የእግዚአብሔር እቅድ ወሳኝ አካል ነው። ትልቁ አላማችን ወደ እግዚአብሔር መገኘት መመለስ እና የደስታ ሙላትን ለመቀበል መዘጋጀት ነው። የምድር ህይወት ለዚህ የሚያዘጋጅበት አንዳንድ መንገዶች ከዚህ በታች ተዘርዝረዋል።

ምስል
ትንሽ ልጅ ፈገግ እያለ

ስጋዊ አካልን መቀበል

ወደ ምድር የመጣንበት አንዱ ዓላማ መንፈሳችን የሚያድርበትን ሥጋዊ አካልን ለመቀበል ነው። ሰውነታችን የተቀደሰ ተአምራዊ የእግዚአብሔር ፍጥረት ነው። በሥጋዊ አካላችን፣ መንፈሳችን የማይችላቸውን ብዙ ነገሮችን ማድረግ፣ መማር እና መለማመድ እንችላለን። እንደ መንፈስ በማንችለው መንገድ ማደግ እንችላለን።

ሰውነታችን ሟች ስለሆነ ህመም፣በሽታ እና ሌሎች ፈተናዎች ያጋጥሙናል። እነዚህ ተሞክሮዎች ትዕግስትን፣ ርኅራኄን እና ሌሎች መለኮታዊ ባሕርያትን እንድንማር ይረዱናል። የደስታ መንገዳችን አካል ሊሆኑ ይችላሉ። ትክክለኛውን መምረጥ ከባድ በሚሆንበት ጊዜ ትክክለኛውን መምረጥ ብዙ ጊዜ እምነት፣ ተስፋ እና ልግስና የባህሪያችን አካል የሚሆኑበት መንገድ ነው።

ነጻ ምርጫን በጥበብ መጠቀምን መማር

ሌላው የምድራዊ ህይወት አላማ ትክክለኛውን ለመምረጥ ነጻ ምርጫን በጥበብ መጠቀምን መማር ነው። እግዚአብሄርን ለመምሰል ነጻ ምርጫን በጥበብ መጠቀምን መማር አስፈላጊ ነው።

የሰማይ አባት እና ኢየሱስ ክርስቶስ ትክክል የሆነውን ያስተምሩናል እንዲሁም ወደ ደስታ እንዲመሩን ትእዛዞችን ይሰጡናል። ሰይጣን እንደ እሱ ያዘንን እንድንሆን ስለሚፈልግ ክፉ እንድንሠራ ይፈታተነናል። በመልካም እና በክፉ መካከል ተቃርኖ ያጋጥመናል፣ ይህም ነጻ ምርጫ መጠቀምን እንድንማር አስፈላጊ ነው (2 ኔፊ 2፡11 ተመልከቱ)።

እግዚአብሔርን ስንታዘዝ፣ እናድጋለን እንዲሁም ቃል የገባውን በረከቶች እንቀበላለን። ሳንታዘዝ ስንቀር የኃጢአትን መዘዝ እንቀበላለን፣ ራሳችንንም ከእርሱ እናርቃለን፣ ። ምንም እንኳን አንዳንድ ጊዜ እንደዚያ ባይመስልም ኃጢአት ውሎ አድሮ ደስታን ወደ ማጣት ይመራል። ብዙ ጊዜ የመታዘዝ በረከቶች— እንዲሁም የኃጢአት ውጤቶች— ወዲያውኑ ግልጽ ወይም በውጪ የሚታዩ አይሆኑም። ነገር ግን እግዚአብሔር ትክክል ነውና የተረጋገጡ ናቸው ።

የምንችለውን ሁሉ ብናደርግም እንኳን፣ ሁላችንም ኃጢአት እንሠራለን ፣ “የእግዚአብሔርም ክብር [ይጎድለናል]” (ሮሜ 3፡23)። ይህንን በማወቅ፣ የሰማይ አባት ወደ እርሱ እንድንመለስ ንስሃ የምንገባበትን መንገድ አዘጋጅቶልናል።

ንስሐ የአዳኛችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ኃይል ወደ ሕይወታችን ያመጣል (ሄለማን 5፡11 ተመልከቱ)። ንስሐ ስንገባ፣ በኢየሱስ ክርስቶስ የኃጢያት ክፍያ መስዋዕት እና በመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ከኃጢአት እንነጻለን (3 ኔፊ 27፡16–20 ተመልከቱ)። በንስሐ ደስታን እናገኛለን። የሰማይ አባታችን መሃሪ ነውና ወደ እርሱ የምንመለስበት መንገድ ተከፍቶልናል። (በትምህርት 3 ላይ “ንስሃ” የሚለውን ተመልከቱ።)

በእምነት መራመድን መማር

የዚህ ህይወት ሌላው አላማ ከሰማይ አባት በመለየት ብቻ ሊመጣ የሚችለውን ልምድ ለማግኘት ነው። እርሱን ስለማናየው፣ በእምነት መራመድን መማር አለብን (2 ቆሮንቶስ 5፡6-7 ተመልከቱ)።

እግዚአብሔር በዚህ ጉዞ ላይ ብቻችንን አልተወንም። እኛን ለመምራት፣ ለማበርታት እና ለመቀደስ መንፈስ ቅዱስን ሰጥቶናል። በተጨማሪም ቅዱሳት መጻሕፍትን፣ ነቢያትን፣ ጸሎትን፣ እና የኢየሱስ ክርስቶስን ወንጌል አዘጋጅቷል።

እያንዳንዱ የምድራዊ ልምዳችን ክፍል—ደስታና ሀዘን፣ ስኬትና እንቅፋት—ወደ እግዚአብሔር ለመመለስ ስንዘጋጅ እንድናድግ ይረዱናል።

የቅዱስ መጽሀፍ ጥናት

እያደጉ የመቀጠል ጊዜ

ምርጫ

መልካም እና ክፉ

ኃጢያት

ከእግዚአብሔር ጋር ለመሆን ንጹህ መሆን አለብን

ስለዚህ መርህ የበለጠ ተማሩ

  • የቅዱሳት መጻህፍት መመሪያ፣ “ሟች፣”“መከራ

  • የወንጌል ርዕሶች ሟችነት”፣ “መከራ

የኢየሱስ ክርስቶስ የኃጢያት ክፍያ

በአዳምና በሔዋን ውድቀት ሁላችንም ለኃጢአትና ለሞት ተገዢ ነን። የኃጢአትንና የሞትን ውጤት በራሳችን ማሸነፍ አንችልም። በሰማይ አባታችን የመዳን እቅድ ውስጥ፣ ወደ እርሱ እንድንመለስ የውድቀትን ውጤት የምናሸንፍበትን መንገድ አዘጋጅቷል። አለም ከመፈጠሩ በፊት ኢየሱስ ክርስቶስ አዳኛችን እና ቤዛችን ይሆን ዘንድ መረጠው።

ከኃጢአትና ከሞት ሊቤዠን የሚችለው ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው። እርሱ እውነተኛ የእግዚአብሔር ልጅ ነው። ለአባቱ ፍጹም ታዛዥ በመሆን ከኃጢአት የነጻ ሕይወትን ኖረ። የሰማይ አባትን ፈቃድ ለማድረግ የተዘጋጀ እንዲሁም ፈቃደኛ ነበር።

የአዳኙ የኃጢያት ክፍያ የጌቴሴማኒ ስቃዩን፣ መከራውን እና የመስቀል ላይ ሞቱን በተጨማሪም ትንሳኤውን ያጠቃልላል። ከእያንዳንዱ ቀዳዳ እስኪደማ ድረስ (ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 19፡18ን ይመልከቱ) ከመረዳት በላይ የሆነን መከራን ተቀበለ።

የኢየሱስ ክርስቶስ የኃጢያት ክፍያ በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ እጅግ የከበረ ክስተት ነው። በስርየት መስዋዕቱ፣ ኢየሱስ የአብን እቅድ ተግባራዊ አድርጓል። ራሳችንን ከኃጢአት እና ከሞት ማዳን ስለማንችል ያለ ኢየሱስ ክርስቶስ የኃጢያት ክፍያ ደካሞች እንሆን ነበር (አልማ 22፡12–15 ተመልከቱ)።

የአዳኛችን መስዋዕትነት ለአባቱ እና ለእኛ ያለው ከፍ ያለ የፍቅር መግለጫ ነበር። የክርስቶስ ፍቅር “ስፋቱ፣ ርዝመቱ፣ ከፍታው፣ ጥልቅነቱ፣ ” ከእኛ መረዳት በላይ ነው (ኤፌሶን 3፡18፣ እንዲሁም ቁጥር 19 ተመልከቱ)።

ምስል
ስቅለት፣ በሃሪ አንደርሰን

ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትን ለሁሉም አሸነፈ

ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ሲሞት መንፈሱ ከስጋው ተለይቶ ነበር። በሦስተኛው ቀን፣ መንፈሱና ስጋው ዳግም ላይለላዩ እንደገና ተገናኙ። ለብዙ ሰዎች ተገልጦ የማይሞት ሥጋና አጥንት ያለው አካል እንዳለው አሳያቸው። ይህ የመንፈስ እና የአካል ዳግም መገናኘት ትንሳኤ ይባላል።

እንደ ምድራዊነታችን፣ እያንዳንዳችን እንሞታለን። ነገር ግን ኢየሱስ ሞትን ድል ስለነሳ በምድር ላይ የተወለደ እያንዳንዱ ግለሠብ ከሞት ይነሳል። ትንሳኤ በአዳኙ ምህረት እና የማዳን ጸጋ ለሁሉም የተሰጠ መለኮታዊ ስጦታ ነው። የእያንዳንዱ ግለሠብ መንፈስ እና አካል ዳግም ይገናኛል፣ እያንዳንዳችንም ፍጹም በሆነ፣ በትንሳኤ አካል ለዘላለም እንኖራለን። በኢየሱስ ክርስቶስ ምክንያት ባይሆን ኖሮ ሞት ከሰማይ አባት ጋር የመኖር ተስፋን ሁሉ እንዲያበቃ ያደርግ ነበር (2 ኔፊ 9፡8–12 ተመልከቱ)።

ኢየሱስ ከኃጢአታችን እንድንነጻ ያስችለናል

በክርስቶስ በኩል የምናገኘውን ተስፋ ለመረዳት የፍትህ ህግን መረዳት አለብን። ይህ ለድርጊታችን ውጤቶችን የሚያመጣ የማይለወጥ ህግ ነው። ለእግዚአብሔር መታዘዝ መልካም ውጤትን ያመጣል፣ አለመታዘዝ ደግሞ አሉታዊ ውጤቶችን ያመጣል። ( አልማ 42፥14-18 ተመልከቱ።) ኃጢአት ስንሠራ፣ በመንፈስ እንረክሳለን፣ ምንም እርኩስ ነገር ደግሞ በእግዚአብሔር ፊት መገኘት አይችልም (3 ኔፊ 27፡19 ተመልከቱ)።

ምስል
ኢየሱስ በጌቴሴማኒ እየጸለየ፣ በሃሪ አንደርሰን

በኢየሱስ ክርስቶስ የኃጢያት ክፍያ መስዋዕትነት ጊዜ በእኛ ቦታ በመሆን ተሰቃየ እንዲሁም ለኃጢአታችን ቅጣት ዋጋ ከፈለ (3 ኔፊ 27፡16–20 ተመልከቱ)። የእግዚአብሔር እቅድ ኢየሱስ ክርስቶስ በእኛ እና በፍትህ መካከል በመቆም እንዲማልድልን ኃይልን ይሰጠዋል (ሞዛያ 15፡9 ተመልከቱ)። በኢየሱስ የኃጢያት ክፍያ መስዋዕትነት ምክንያት፣ ለንስሀ እምነትን ስንለማመድ እርሱ ለእኛ ሲል ምሕረት መጠየቅ ይችላል (ሞሮኒ 7፡27ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 45፡3–5 ተመልከቱ)። “እናም ምሕረት የፍትህ ፍላጎት ሊያሟላ ይችላል፣ እናም በጠባቂ ክንዶቹ [ይከበናል]” (አልማ 34፡16)።

ከእግዚአብሔር ጋር ለመኖር መመለስ የምንችለው በአዳኙ የሀጢያት ክፍያ ስጦታ እና በንስሀ ብቻ ነው። ንስሐ ስንገባ ይቅር እንባላለን እንዲሁም በመንፈስ እንነጻለን። ከኃጢአታችን የበደለኝነት ሸክም እንገላገላለን። የቆሰለ ነፍሳችን ይፈወሳሉ። በደስታም እንሞላለን (አልማ 36፡24 ተመልከቱ)።

ፍጽምና የጎደለን ብንሆንም እንዲሁም እንደገና ልንወድቅ ብንችልም፣ በእኛ ውስጥ ካለው ውድቀት፣ ጉድለት ወይም ኃጢአት በኢየሱስ ክርስቶስ ውስጥ ያለው ጸጋ፣ ፍቅር እና ምሕረት ይበልጣል። ወደ እርሱ ስንመለስ እና ንስሃ ስንገባ እግዚአብሔር እኛን ለመቀበል ሁል ጊዜ ዝግጁ እና ጉጉ ነው (ሉቃስ 15፡11–32 ተመልከቱ)። ምንም እና ማንም “በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን ካለ ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊለየን [አይችልም]” (ሮሜ 8፡ 39)

ኢየሱስ ሕመማችንን፣ ችግሮቻችንን እና ድክመቶቻችንን በራሱ ላይ ወሰደ

በኃጢያት ክፍያ መስዋዕቱ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ህመማችንን፣ ስቃያችንን እና ድካማችንን በራሱ ላይ ወስዷል። በዚህ ምክንያት፣ “በሥጋ ሕዝቡን ከድካማቸው እንዴት እንደሚረዳ” ያውቃል (አልማ 7፥12፤ እንዲሁም ቁጥር 11 ተመልከቱ)። “ወደኔ ኑ” ሲል ጋብዞናል፣ እናም ያን ስናደርግ፣ እረፍትን፣ ተስፋን፣ ጥንካሬን፣ እይታን እና ፈውስን ይሰጠናል (ማቴዎስ 11፡28፤ እንዲሁም ቁጥር 29–30 ተመልከቱ)።

በኢየሱስ ክርስቶስ እና በኃጢያት ክፍያው ስንደገፍ ችግሮቻችንን፣ በሽታችንን እና ስቃያችንን እንድንቋቋም ሊረዳን ይችላል። በደስታ፣ በሰላም፣ እና በመፅናናት መሞላት እንችላለን። በህይወት ፍትሃዊ ያልሆኑ ነገሮች በሙሉ በኢየሱስ ክርስቶስ የኃጢያት ክፍያ በኩል ትክክል መሆን ይችላሉ።

የቅዱስ መጽሀፍ ጥናት

የአዳኙ የኃጢያት ክፍያ

ትንሳኤ

ስለዚህ መርህ የበለጠ ተማሩ

ምስል
ቤተሰብ መቃብር እየጎበኘ

የመንፈስ አለም

ብዙ ሰዎች “ከሞትኩ በኋላ ምን ይሆናል?” ብለው ያስባሉ። የደህንነት እቅድ ለዚህ ጥያቄ አንዳንድ ጠቃሚ መልሶችን ይሰጣል።

ሞት የእግዚአብሔር “ምህረት የተሞላበት … እቅድ” አካል ነው (2 ኔፊ 9፡6)። ሞት የእኛ የመኖር ፍጻሜ ከመሆን ይልቅ የዘላለም እድገታችን ቀጣይ እርምጃ ነው። እግዚአብሄርን ለመምሰል ሞትን መቅመስ፣ በኋላም ፍጹም የሆነ ትንሣኤ ያደረገ አካል ማግኘት አለብን።

ሥጋዊ አካላችን ሲሞት መንፈሳችን በመንፈሳዊው ዓለም ውስጥ መኖር ይቀጥላል። ይህ ከትንሣኤ እና ከመጨረሻው ፍርድ በፊት ጊዜያዊ የመማር እና የመዘጋጀት ሁኔታ ነው። የምድራዊ ሕይወት ዕውቀታችን ከእኛ ጋር ይኖራል።

በመንፈሳዊው ዓለም፣ የኢየሱስ ክርስቶስን ወንጌል የተቀበሉ እና የኖሩ ሰዎች “ገነት ተብላ ወደምትጠራው … የደስታ ሁኔታ” (አልማ 40፡12) ይገባሉ። ትናንሽ ልጆችም ሲሞቱ ወደ ገነት ይገባሉ።

በገነት ያሉ ነፍሳት ከችግራቸው እና ከሀዘናቸው ሰላም ይሆናሉ። የእግዚአብሔርን ሥራ በመሥራት እና ሌሎችን በማገልገል መንፈሳዊ እድገታቸውን ይቀጥላሉ። በምድራዊ ህይወታቸው ወንጌልን ላልተቀበሉ ወንጌልን ያስተምራሉ (ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 138፡32–37፣ 57–59 ተመልከቱ)።

በመንፈስ ዓለም፣ ወንጌልን በምድር ላይ መቀበል ያልቻሉ፣ ወይም ትእዛዛትን ላለመከተል የመረጡ ሰዎች፣ አንዳንድ ገደቦች ይገጥሟቸዋል (ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 138፡6–37አልማ 40፡6–14 ተመልከቱ)። ነገር ግን እግዚአብሔር ጻድቅ እና መሐሪ ስለሆነ፣ የኢየሱስ ክርስቶስን ወንጌል ለመማር እድል ያገኛሉ። ከተቀበሉት እና ንሰሃ ከገቡ ከኃጢአታቸው ይዋጃሉ (ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 138፡58 ተመልከቱ፣ እንዲሁም 138፡31–35128፡22 ተመልከቱ)። ወደ ገነት ሰላምም ይቀበላሉ። በመጨረሻ በምድር እንዲሁም በመንፈስ አለም ባደረጉት ምርጫ መሰረት በክብር መንግስት ውስጥ ቦታ ይቀበላሉ።

ከሞት እስከምንነሳ ድረስ በመንፈስ አለም ውስጥ እንቆያለን።

የቅዱስ መጽሀፍ ጥናት

ስለዚህ መርህ የበለጠ ተማሩ

  • የቅዱሳት መጻህፍት መመሪያ፣ “ገነት።”

ትንሳኤ፣ መዳን እና ከፍ ከፍ መደረግ

ትንሳኤ

የእግዚአብሔር እቅድ እንድናድግ እና ዘላለማዊ ህይወት እንድንቀበል ያስችለናል። በመንፈስ ዓለም ካለን ቆይታ በኋላ፣ ትንሳኤ የዚያ እድገት ቀጣይ እርምጃችን ነው።

ትንሳኤ የአካላችን እና የመንፈሳችን ዳግም መገናኘት ነው። እያንዳንዳችን ከሞት እንነሳለን። ይህ ሊሆን የቻለው በአዳኙ የሀጢያት ክፍያ እና ትንሳኤ አማካኝነት ነው። (አልማ 11:42–44ን ተመልከቱ)

ከሞት ስንነሳ እያንዳንዳችን ከህመምና ከበሽታ የጸዳ ፍጹም የሆነ ሥጋዊ አካል ይኖረናል። ለዘላለምም በመኖር የማንሞት እንሆናለን።

ደህንነት

ሁላችንም ትንሳኤ ስለምናደርግ ከሥጋዊ ሞት እንድናለንወይም ድህነት እናገኛለን። ይህ ስጦታ የተሰጠን በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ነው።

የፍትህ ህግ ለኃጢአታችን ከሚጠይቀው ክፍያ መዳን ወይም ደህንነትን ማግኘት እንችላለን። ንስሐ ስንገባ ይህ ስጦታ በኢየሱስ ክርስቶስ ቸርነት እና ምሕረትየሚቻል ይሆናል። (አልማ 42:13–15፣ 21–25ን ተመልከቱ)

ከፍ ከፍ መደረግ

ከፍ ከፍ መደረግ ወይም የዘላለም ህይወት፣ በሰለስቲያል መንግስት ውስጥ ከፍተኛው የደስታ እና የክብር ሁኔታ ነው። ከፍ ከፍ መደረግ በሁኔታዎች የሚወሰን ስጦታ ነው። ፕሬዘደንት ራስል ኤም. ኔልሰን “እነዚህ ብቁ የሚያደርጉ መስፈርቶች በጌታ ማመን፣ ንስሃ፣ ጥምቀት፣ መንፈስ ቅዱስን መቀበል፣ እና ለቤተመቅደስ ሥርዓቶች እና ቃልኪዳኖች ታማኝ ሆኖ መቆየት ናቸው” በማለት አስተምረዋል። (“መዳን እና ከፍ ከፍ መደረግ፣” ኢንዛይን ወይም ሊያሆና፣ ግንቦት 2008(እ.አ.አ)፣ 9)።

ከፍ ከፍ መደረግ ከእግዚአብሔር ጋር ለዘላለም በዘለአለማዊ ቤተሰብ መኖር ማለት ነው። ይህም እግዚአብሔርን እና ኢየሱስ ክርስቶስን ማወቅ፣ እነርሱን መምሰል እና የሚኖሩት ህይወት ተካፋይ መሆን ነው።

የቅዱስ መጽሀፍ ጥናት

ስለዚህ መርህ የበለጠ ተማሩ

  • የቅዱሳት መጻህፍት መመሪያ፣ “ትንሳኤ።”

  • የወንጌል ርዕሶች ትንሳኤ”፣ መዳን

ምስል
የጸሃይ ጨረር በደመናዎች አልፎ ሲያበራ

ፍርድ እና የክብር መንግስታት

ማሳሰቢያ፡ በመጀመሪያ ስለ ክብር መንግስታት ስታስተምሩ፣ እንደ ግለሰቡ ፍላጎት እና ግንዛቤ በመሰረታዊ ደረጃ አስተምሩ።

ከሞት ስንነሳ ኢየሱስ ክርስቶስ ጻድቅ እና መሐሪ ፈራጃችን ይሆናል። ከጥቂቶች በስተቀር፣ እያንዳንዳችን በክብር መንግሥት ውስጥ ቦታ ይኖረናል። ምንም እንኳን ሁላችንም ከሞት ብንነሳም ሁላችንም አንድ አይነት ዘላለማዊ ክብር አንቀበልም (ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 88፡22–24፣ 29–34130፡20–21132፡5 ተመልከቱ)።

በምድር ሕይወታቸው የእግዚአብሄርን ሕጎች ሙሉ በሙሉ የመረዳትና የመታዘዝ ዕድል ያላገኙ ግለሰቦች በመንፈስ ዓለም ውስጥ ያ ዕድል ይሰጣቸዋል። ኢየሱስ እያንዳንዱ ግለሠብ በምድር እና በመንፈስ አለም በነበረው እምነት፣ ስራ፣ ፍላጎት እና ንስሃ መሰረት ይፈርዳል (ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 138፡32–34፣ 57–59 ተመልከቱ)።

ቅዱሳት መጻህፍት ስለ ሰለስትያል፣ ተረስትያል እና የቴሌስቲያል የክብር መንግስታት ያስተምራሉ። እያንዳንዳቸው የእግዚአብሔር ፍቅር፣ ፍትህ እና ምሕረት መገለጫ ናቸው።

በክርስቶስ እምነታቸውን የሚያሳድጉ፣ ከኃጢአታቸው ንስሃ የገቡ፣ የወንጌል ሥርአቶችን የተቀበሉ፣ ቃል ኪዳናቸውን የጠበቁ፣ መንፈስ ቅዱስን የተቀበሉ እንዲሁም እስከ መጨረሻው የጸኑ በሰለስቲያል መንግስት ይድናሉ። ይህ መንግሥት በምድራዊ ሕይወታቸው ወንጌልን የመቀበል ዕድል ያላገኙ ነገር ግን “በሙሉ ልባቸው ይቀበሉ የነበሩ” በመንፈሳዊውም ዓለም የተቀበሉ ሰዎችን ያጠቃልላል (ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 137፡8፤ እንዲሁም ቁጥር 7 ተመልከቱ) )። የተጠያቂነት ዕድሜ (ስምንት ዓመት) ሳይሞላቸው የሞቱ ህጻናት በሰለስቲያል መንግሥት ይድናሉ (ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 137፡10 ተመልከቱ)።

በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ፣ የሰለስቲያል መንግሥት ከፀሐይ ክብር ወይም ብርሃን ጋር ተነጻጽሯል። (ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 76፡50–70 ተመልከቱ።)

የተከበረ ኑሮ የኖሩ ሰዎች “በሥጋ ያልተቀበሉ የኢየሱስን ምስክር ፣ ነገር ግን በኋላ የተቀበሉት” በቴረስትያል መንግሥት ውስጥ ቦታ ያገኛሉ (ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 76፡74)። በኢየሱስ ምሥክርነት ጀግኖች ላልነበሩም ተመሳሳይ ነው። ይህም መንግስት ከጨረቃ ክብር ጋር ይመሳሰላል። (ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 76፥71-80 ተመልከቱ።)

በኃጢአታቸው የቀጠሉና በዚህ ህይወት ንስሃ ያልገቡ ወይም የኢየሱስ ክርስቶስን ወንጌል በመንፈስ አለም ያልተቀበሉ ሽልማታቸውን በቴለስቲያል መንግስት ይቀበላሉ። ይህም መንግስት ከጨረቃ ክብር ጋር ይመሳሰላል። (ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 76፥81-86 ተመልከቱ።)

የቅዱስ መጽሀፍ ጥናት

ስለዚህ መርህ የበለጠ ተማሩ

ከአጭር እስከ መካከለኛ የትምህርት መዘርዝር

የሚከተለው ንድፍ አጭር ጊዜ ካላችሁ ለአንድ ሰው ልታስተምሩ የምትችሉት ነገር ምሳሌ ነው። ይህንን ንድፍ ስትጠቀሙ ለማስተማር አንድ ወይም ተጨማሪ መርሆችን ምረጡ። ለእያንዳንዱ መርህ የትምህርት መሰረት ቀደም ብሎ በትምህርቱ ውስጥ ቀርቧል።

ስታስተምሩ ጥያቄዎችን ጠይቁ እንዲሁም አዳምጡ። ሰዎች እንዴት ወደ እግዚአብሄር መቅረብ እንደሚችሉ እንዲማሩ የሚያግዙ ግብዣዎችን አቅርቡ። አንድ አስፈላጊ ግብዣ ግለሰቡ እንደገና ከእናንተ ጋር እንዲገናኝ መጋበዝ ነው። የትምህርቱ ቆይታ የሚወሰነው በምትጠይቋቸው ጥያቄዎች እና በአደማመጣችሁ ላይ ነው።

ከ3-10 በሚሆኑ ደቂቃዎች ውስጥ ሰዎችን ልታስተምሯቸው የምትችሏቸው ነገሮች

  • ሁላችንም የእግዚአብሔር የመንፈስ ልጆች ነን። እኛ የእሱ ቤተሰብ አባላት ነን። እያንዳንዳችንን ያውቃል እንዲሁም ይወደናል።

  • በዚህ እና በዘላለማዊ ህይወት ውስጥ ለደስታችን እና ለእድገታችን እግዚአብሔር እቅድን አዘጋጅቷል።

  • በእግዚአብሔር እቅድ ሥጋዊ አካልን ለመቀበል፣ ለመማር እና ለማደግ ወደ ምድር መምጣት አስፈለገን።

  • ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር እቅድ ዋና ክፍል ነው። እርሱ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረን ያስችለናል።

  • ኢየሱስ በእግዚአብሄር መሪነት ምድርን ፈጠረ።

  • በምድር ላይ ያሉን ተሞክሮዎች ወደ እግዚአብሔር መገኘት ለመመለስ እንድንዘጋጅ ለመርዳት የታሰቡ ናቸው።

  • እያንዳንዳችን ኃጢአት እንሠራለን እንዲሁም እያንዳንዳችን እንሞታለን። እግዚአብሔር ስለወደደን ከኃጢአትና ከሞት እንዲቤዠን ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን ወደ ምድር ልኮልናል።

  • በህይወት ፍትሃዊ ያልሆኑ ነገሮች በሙሉ በኢየሱስ ክርስቶስ የኃጢያት ክፍያ በኩል ሊስተካከሉ ይችላሉ።

  • ሥጋዊ አካላችን ሲሞት መንፈሳችን መኖሩን ይቀጥላል። በመጨረሻ ሁላችንም ከሞት እንነሳለን። ይህ ማለት የእያንዳንዱ ግለሠብ መንፈስ እና አካል እንደገና ይገናኛሉ እንዲሁም እያንዳንዳችን ፍፁም በሆነ በትንሣኤ አካል ለዘላለም እንኖራለን ማለት ነው።

  • ከሞት ስንነሳ ኢየሱስ ክርስቶስ ፈራጃችን ይሆናል። ከጥቂቶች በስተቀር፣ ሁሉም የእግዚአብሔር ልጆች በክብር መንግሥት ውስጥ ቦታ ይኖራቸዋል። ታማኝ ከሆንን በእግዚአብሔር ፊት ለመኖር ዳግም መመለስ እንችላለን።