የሚስዮን ጥሪዎች
ምዕራፍ 3፥ ትምህርት 3—የኢየሱስ ክርስቶስን ወንጌል


“ምዕራፍ 3፥ ትምህርት 3—የኢየሱስ ክርስቶስን ወንጌል” ወንጌሌን ስበኩ፡ የኢየሱስ ክርስቶስን ወንጌል ለማካፈል መመርያ (2023 (እ.አ.አ))

“ምዕራፍ 3፥ ትምህርት 3” ወንጌሌን ስበኩ

ምዕራፍ 3፥ ትምህርት 3

የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል

ምስል
ምፅዓት፣ በሃሪ አንደርሰን

ሰዎች ሊጠይቁ ይችላሉ

  • ኢየሱስ ክርስቶስ ማነው? እኔን እና ቤተሰቤን እንዴት ሊረዳ ይችላል?

  • በኢየሱስ ክርስቶስን ማመን ምን ማለት ነው? በእርሱ ማመን ህይወቴን እንዴት ሊባርክ ይችላል?

  • ንስሀ መግባት ማለት ምን ማለት ነው?

  • መጥፎ ምርጫዎችን ካደረኩኝ በኋላ የእግዚአብሔር ሰላምና ይቅርታ እንዴት ሊሰማኝ ይችላል?

  • የጥምቀት አላማ ምንድን ነው?

  • የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ምንድን ነው?

  • እስከመጨረሻ መፅናት ምን ማለት ነው?

ወደ ክርስቶስ የምንመጣው በኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል አማካኝነት ነው። በጣም ቀላል ስለሆነ ትንሽ ልጅ እንኳን ሊረዳው ይችላል። ይህ ትምህርት በክርስቶስ ማመንን፣ንሰሃን፣ ጥምቀትን፣ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታን እና እስከመጨረሻ መፅናትን ባካተተ የወንጌል እና የክርስቶስ አስተምሮቶች ላይ ያተኩራል። በተጨማሪም ወንጌል ሁሉንም የእግዚአብሄር ልጆችን እንዴት እንደሚባርክ ያሳያል።

ወንጌል የሚለው ቃል በቀጥታ ሲተረጎም “የምስራች” ማለት ነው። የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል ወደ እርሱ ለመቅረብ እና ለመዳን የሚያስፈልገንን ትምህርት—ዘላለማዊውን እውነት— ስለሚሰጥ የምስራች ነው (1 ኔፊ 15፡14 ተመልከቱ)። ወንጌሉ መልካም፣ ትርጉም ያለው ሕይወት እንዴት መኖር እንዳለብን ያስተምረናል። የወንጌል የምሥራች ለኃጢያት ምህረትን እንድናገኝ፣ እንድንቀደስ እና ወደ እግዚአብሔር መገኘት እንድንመለስ መንገድ ያዘጋጃል።

ለማስተማር የቀረቡ ሃሳቦች

ይህ ክፍል ለማስተማር ለመዘጋጀት የሚረዳችሁን ምሳሌዎች ዝርዝር ያቀርባል። እንዲሁም ልትጠቀሙባቸው የምትችሏቸውን የጥያቄዎች እና የግብዣዎች ምሳሌዎችን ያካትታል።

ለማስተማር ስትዘጋጁ፣ የእያንዳንዱን ግለሠብ ሁኔታ እና መንፈሳዊ ፍላጎቶች በጸሎት አስቡ። ለማስተማር በጣም ጠቃሚ የሚሆነውን ወስኑ። ሰዎች ሊረዷቸው የማይችሉትን ቃላት ለማብራራት ተዘጋጁ። ትምህርቶቹን አጭር ማድረግን በማስታወስ ምን ያህል ጊዜ እንደሚኖራችሁ አቅዱ።

በምታስተምሩበት ጊዜ የምትጠቀሙባቸውን ጥቅሶች ምረጡ። የትምህርቱ “ትምህርታዊ መሰረት” ክፍል ብዙ አጋዥ ጥቅሶችን ያካትታል።

በምታስተምሩበት ጊዜ የትኞቹን ጥያቄዎች መጠየቅ እንዳለባችሁ አስቡ። እያንዳንዱ ሰው እርምጃ እንዲወስድ የሚያበረታታ ግብዣዎችን ለማቅረብ አቅዱ።

እግዚአብሔር ስለገባቸው በረከቶች አጽንኦት ስጡ፣ እንዲሁም ስለምታስተምሩት ነገር ምስክርነታችሁን አካፍሉ።

ምስል
ሚስዮናውያን ቤተሰብን እያስተማሩ

ከ15-25 ባለው ደቂቃ ውስጥ ለሰዎች ማስተማር የምትችሉት ነገር

ለማስተማር ከሚከተሉት መርሆዎች ውስጥ አንዱን ወይም ተጨማሪ ምረጡ። የእያንዳንዱ መርህ ትምህርት መሠረት ከዚህ ዝርዝር በኋላ ቀርቧል።

የኢየሱስ ክርስቶስ መለኮታዊ ተልዕኮ

  • እግዚአብሔር ስለወደደን ከኃጢአትና ከሞት እንዲቤዠን የሚወደውን ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን ወደ ምድር ልኮልናል።

  • በኢየሱስ የስርየት መስዋዕትነት ምክንያት፣ ንስሀ ስንገባ ከኃጢአታችን ልንነጻ እና ልንቀደስ እንችላለን።

  • ኢየሱስ ከተሰቀለ በኋላ ከሞት ተነስቷል። በእርሱ ትንሳኤ ምክንያት፣ ከሞትን በኋላ ሁላችንም እንደገና እንነሳለን። ይህ ማለት የእያንዳንዱ ግለሠብ መንፈስ እና አካል እንደገና ይገናኛሉ እንዲሁም እያንዳንዳችን ፍፁም በሆነ በትንሣኤ አካል ለዘላለም እንኖራለን ማለት ነው።

በኢየሱስ ክርስቶስ ማመን

  • እምነት የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል የመጀመሪያ መርህ ነው።

  • በኢየሱስ ክርስቶስ ማመን እርሱ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ እና እንደ አዳኛችን እና ቤዛችን በእርሱ መታመንን ያካትታል።

  • በኢየሱስ ክርስቶስ ማመን የተግባር እና የሃይል መርህ ነው።

  • በጸሎት፣ ቅዱሳት መጻህፍትን በማጥናት እና ትእዛዛትን በመጠበቅ እምነታችንን እናጠነክራለን።

ንስሀ መግባት

  • በኢየሱስ ክርስቶስ ማመን ወደ ንስሐ ያመራናል። ንስሐ ወደ እግዚአብሔር የመመለስ እና ከኃጢአት የመራቅ ሂደት ነው። ንስሃ ስንገባ፣ ተግባራችን፣ ምኞታችን እና ሀሳባችን ከእግዚአብሔር ፈቃድ ጋር ይበልጥ የሚስማማ ይሆናል።

  • ከልብ ንስሐ ስንገባ እግዚአብሔር ይቅር ይለናል። ኢየሱስ ክርስቶስ ለኃጢአታችን ዋጋ ስለከፈለ ስርየት እንዲቻል አድርጓል።

  • ንስሃ ስንገባ፣ በደላችን እና ሀዘናችን ሲፈወስ ሰላም ይሰማናል።

  • ንስሃ የዕድሜ ልክ ሂደት ነው። እግዚአብሔር ንስሐ በገባን ቁጥር እንደገና ይቀበለናል። በእኛ ፈጽሞ ተስፋ አይቆርጥም።

ጥምቀት፡- ከእግዚአብሔር ጋር የመጀመሪያው ቃል ኪዳናችን

  • ጥምቀት በመጀመሪያ ከእግዚአብሔር ጋር የቃል ኪዳን ግንኙነት ውስጥ የምንገባበት መንገድ ነው።

  • ጥምቀት ሁለት ክፍሎች አሉት፡ በውሃ መጠመቅ እና በመንፈስ መጠመቅ ስንጠመቅ እና ማረጋገጫ ስንወስድ ከኃጢአታችን በመንጻት ህይወትን እንደ አዲስ እንጀምራለን።

  • የኢየሱስን ምሳሌ በመከተል በመጥለቅ እንጠመቃለን።

  • ልጆች ስምንት ዓመት እስኪሞላቸው ድረስ አይጠመቁም። ከዚያ እድሜ በፊት የሚሞቱ ህጻናት በኢየሱስ ክርስቶስ የኃጢያት ክፍያ አማካኝነት ይድናሉ።

  • የኢየሱስን መስዋዕትነት በማስታወስ እና ከእግዚአብሔር ጋር የገባነውን ቃል ኪዳን ለማደስ በየሳምንቱ ቅዱስ ቁርባንን እንካፈላለን።

የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ

  • መንፈስ ቅዱስ የአምላክ ሶስተኛው አባል ነው።

  • ከተጠመቅን በኋላ፣ የመንፈስ ቅዱስን ስጦታ በማረጋገጫ ሥርዓት እንቀበላለን።

  • የመንፈስ ቅዱስን ስጦታ ስንቀበል፣ ታማኝ ከሆንን በህይወታችን ሙሉ የእርሱን አጋርነት ማግኘት እንችላለን።

  • መንፈስ ቅዱስ ይቀድሰናል፣ ይመራናል፣ ያጽናናል እንዲሁም እውነትን እንድናውቅ ይረዳናል።

እስከመጨረሻ መፅናት

  • መጽናት በየእለቱ በክርስቶስ በማመን መቀጠልን ይጨምራል። ከእግዚአብሔር ጋር የገባነውን ቃል ኪዳናችንን መጠበቅ ፣ ንስሐ መግባት፣ የመንፈስ ቅዱስን አጋርነት መፈለግ፣ እና ቅዱስ ቁርባንን ማካፈል እንቀጥላለን።

  • በታማኝነት ኢየሱስ ክርስቶስን ለመከተል ስንፈልግ፣ እግዚአብሔር የዘላለም ሕይወት እንደሚኖረን ቃል ገብቷል።

የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል የእግዚአብሔርን ልጆች ሁሉ ይባርካል

  • ወንጌልን መኖር ደስታችንን ጥልቅ ያደርጋል፣ ድርጊቶቻችንን ያነሳሳል እንዲሁም ግንኙነታችንን ያበለጽጋል።

  • በኢየሱስ ክርስቶስ ትምህርቶች ስንኖር—በግልም ሆነ በቤተሰብ ደረጃ—ደስተኞች እንሆናለን።

  • በኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል አማካኝነት፣ ቤተሰቦች በዚህ ህይወት ይባረካሉ በተጨማሪም አንድ ላይ በመሆን ለዘለአለም በእግዚአብሔር ፊት ሊኖሩ ይችላሉ።

ሰዎችን ልትጠይቋቸው የምትችሏቸው ጥያቄዎች

የሚከተሉት ጥያቄዎች ሰዎችን ልትጠይቋቸው የምትችሏቸው ምሳሌዎች ናቸው። እነዚህ ጥያቄዎች ትርጉም ያለው ውይይቶችን እንድታደርጉ እና የአንድን ግለሠብ ፍላጎቶች እና አመለካከቶች እንድትረዱ ያግዛሉ።

  • ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ምን ታውቃላችሁ?

  • በኢየሱስ ክርስቶስ ማመን ለእናንተ ምን ማለት ነው?

  • በህይወታችሁ ውስጥ ምን ለውጦችን ማድረግ ትችላላችሁ?

  • ስለ ንስሐ ያላችሁ ግንዛቤ ምንድን ነው?

  • ስለ ጥምቀት ያላችሁ ግንዛቤ ምንድን ነው? አሁን ለጥምቀት ለመዘጋጀት ምን ማድረግ ትችላላችሁ?

  • ወደ እግዚአብሔር መገኘት ለመመለስ በምታደርጉት ጉዞ መንፈስ ቅዱስ እንዴት ሊረዳችሁ ይችላል?

  • እናንተ ወይም ቤተሰቦቻችሁ እያጋጠመው ያለው ፈተና ምንድን ነው? የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል ሊረዳ የሚችልባቸውን አንዳንድ መንገዶች እናካፍል?

ልታቀርቧቸው የምትችሏቸው ግብዣዎች

  • ያስተማርነው እውነት መሆኑን እንድታውቁ እግዚአብሄርን በጸሎት ትጠይቃላችሁ? (በመጨረሻው የመማሪያ ክፍል ውስጥ ያለውን “ለማስተማር የሚሆን ሐሳብ፡ ጸሎትን ተመልከቱ።)

  • ስለ አስተማርነው የበለጠ ለማወቅ በአሁኑ እሁድ ቤተክርስቲያን ትገኛላችሁ?

  • መፅሐፈ ሞርሞንን አንብባችሁ የእግዚአብሔር ቃል መሆኑን ለማወቅ ትጸልያላችሁ? (የተወሰኑ ምዕራፎችን ወይም ቁጥሮችን ልትጠቁሙ ትችላላችሁ።)

  • የኢየሱስን ምሳሌ በመከተል ትጠመቃላችሁ? (ከትምህርት 1 በፊት ያለውን “የጥምቀት እና የማረጋገጫ ግብዣ” ተመልከቱ።)

  • ለሚቀጥለው ጉብኝት ቀጠሮ መያዝ እንችላለን?

የትምህርት መሰረት

ይህ ክፍል የወንጌልን እውቀት እና ምስክርነት ለማጠናከር እና ለማስተማር እንዲረዳችሁ እንድታጠኑ ትምህርት እና ጥቅሶችን ይሰጣል።

ምስል
እነዚህ አሥራ ሁለቱን ኢየሱስ ላካቸው፣ በዋልተር ራኔ

የኢየሱስ ክርስቶስ መለኮታዊ ተልዕኮ

በዚህ አለም ደስታን፣ በሚመጣው አለም ደግሞ የዘላለም ህይወት እንድናገኝ የሰማይ አባት የሚወደውን ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን ወደ ምድር ላከ። “እንዲሁም ኢየሱስ፣ ለአለም ሊሰቀልና የአለም ኃጢአቶችን ሊሸከም፣ እናም አለምንም ሊቀድስና፣ ከርኩሳትም ሊያጸዳ ወደ አለም እንደመጣ፣ የሰማያት ድምፅ የመሰከረልን ምስራች ይህ ነው” (ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 76፡40–42)።

ሟች እንደመሆናችን መጠን ሁላችንም ኃጢአት እንሠራለን፣ ሁላችንም እንሞታለን። የሚቤዠን ከሌለን ኃጢአት እና ሞት ከእግዚአብሔር ጋር የዘላለም ሕይወት እንዳይኖረን ይከለክሉናል (2 ኔፊ 9 ተመልከቱ)። ዓለም ከመፈጠሩ በፊት፣ የሰማይ አባት ያድነን ዘንድ ኢየሱስ ክርስቶስን መረጠ። ከፍ ባለ የፍቅር መግለጫው፣ ኢየሱስ ወደ ምድር መጥቶ ይህን መለኮታዊ ተልእኮ ፈጽሟል። ከኃጢአታችን እንድንድን አስችሎናል፣ እናም ሁላችንም ከሞትን በኋላ እንደምንነሳ አረጋግጧል።

ኢየሱስ ያለ ኃጢአት ኖረ። በምድራዊ አገልግሎቱ መጨረሻ፣ በጌቴሴማኒ በተሰቃየ እና በተሰቀለ ጊዜ ኃጢአታችንን በራሱ ላይ ወስዷል (1 ኔፊ 11፡33 ተመልከቱ)። የኢየሱስ መከራ በጣም ትልቅ ከመሆኑ የተነሳ “ከስቃዩ የተነሳ እን[ዲ]ንቀጠቀጥ እናም ከእያንዳንዱ ቀዳዳ እን[ዲ]ደማ (ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 19፡18) አድርጎታል። ኢየሱስ ከተሰቀለ በኋላ፣ ሞትን ድል አድርጎ ተነሥቷል። እነዚህ ክስተቶች በአንድነት የኢየሱስ ክርስቶስ የኃጢያት ክፍያ ናቸው።

ኃጢአታችን በመንፈስ እንድንረክስ ያደርገናል፣ እናም “ምንም እርኩስ ነገር ከእግዚአብሔር ጋር ሊኖር አይቻለውም” (1 ኔፊ 10፥21)። በተጨማሪም የፍትህ ህግ ለኃጢአታችን ዋጋ ይፈልጋል።

የኢየሱስ የሃጢያት ክፍያ መስዋዕት ከኃጢአት እንድንነጻ እና ንስሐ ስንገባ የምንቀደስበትን መንገድ ያዘጋጅልናል። እንዲሁም የፍትህ ጥያቄዎችን ለማርካት መንገዱን ያቀርባል (አልማ 42፡15፣ 23–24 ተመልከቱ)። አዳኙ እንዲህ አለ፣ “እኔ… ንስሃ ከገቡ እንዳይሰቃዩ … እነዚህን ነገሮች ተሰቃይቻለሁ፤ ነገር ግን ንስሐ ካልገቡ እኔ እንደተሰቃየሁት መሰቃየት አለባቸው” (ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 19፡16–17)። በኢየሱስ ክርስቶስ ምክንያት ባይሆን ኖሮ ኃጢአት ወደፊት ከሰማይ አባት ጋር የመኖር ተስፋን ሁሉ ያጠፋ ነበር።

ኢየሱስ ራሱን ለእኛ መሥዋዕት አድርጎ ሲያቀርብ የግል ኃላፊነታችንን አላስቀረም። በእርሱ ማመን፣ ንስሐ መግባት እና ትእዛዛትን ለመጠበቅ መጣር አለብን። ንስሐ ስንገባ፣ ኢየሱስ ስለእኛ አባቱን ምሕረት ይጠይቃል (ሞሮኒ 7፡27–28 ተመልከቱ)። በአዳኙ ምልጃ ምክንያት፣ የሰማይ አባት ይቅር ይለናል፣ ከኃጢአታችን ሸክም እና ከጥፋተኝነት ነፃ ያወጣናል (ሞዛያ 15፡7–9 ተመልከቱ)። በመንፈስ ንጹህ እንሆናለን፣ በመጨረሻም ወደ እግዚአብሔር መገኘት መመለስ እንችላለን።

የኢየሱስ መለኮታዊ ተልእኮ እኛን ከሞት ማዳንም ጭምር ነበር። እርሱ ስለተነሳ ሁላችንም ከሞትን በኋላ እንነሣለን። ይህ ማለት የእያንዳንዱ ግለሠብ መንፈስ እና አካል እንደገና ይገናኛሉ እንዲሁም እያንዳንዳችን ፍፁም በሆነ በትንሣኤ አካል ለዘላለም እንኖራለን ማለት ነው። በኢየሱስ ክርስቶስ ምክንያት ባይሆን ኖሮ ኃጢአት ወደፊት ከሰማይ አባት ጋር የመኖር ተስፋን ሁሉ ያጠፋ ነበር።

የቅዱሳት መጻህፍት ጥናት

እግዚአብሔር ልጁን ላከ

በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት መዳን

ስለዚህ መርህ የበለጠ ተማሩ

በኢየሱስ ክርስቶስ እምነት

ከወንጌል መሰረታዊ መርሆች የመጀመሪያው በኢየሱስ ክርስቶች ማመን ነው። እምነት ለሌሎች የወንጌል መርሆች ሁሉ መሠረት ነው።

በኢየሱስ ክርስቶስ ማመን እርሱ የእግዚአብሔር አንድያ ልጅ እንደሆነ መተማመንን ይጨምራል። እሱም እንደ አዳኛችን እና ቤዛችን፣ ወደ እግዚአብሔር መገኘትም የምንመለስበት ብቸኛው መንገድ እንደሆነ ማመንን ያካትታል (የሐዋርያት ስራ 4፡10–12ሞዛያ 3፡174፡6–8 ተመልከቱ)። “ለማዳን ኃያል በሆነው በእርሱ መልካም ስራ ሙሉ በሙሉ [እንድንተማመን]” ያስፈልገናል (2 ኔፊ 31፥19)።

በኢየሱስ ክርስቶስ ማመን በእርሱ የኃጢያት መስዋዕትነት ስለ ኃጢአታችን እንደተሰቃየ ማመንን ያካትታል። በእርሱ መስዋዕትነት ምክንያት ንስሀ ስንገባ ልንነጻ እና ልንድን እንችላለን። ይህ መንጻት በዚህ ህይወት ሰላም እና ተስፋ እንድናገኝ ይረዳናል። ከሞትንም በኋላ የደስታ ሙላትን እንድንቀበል ያስችለናል።

በኢየሱስ ክርስቶስ ማመን በእርሱ ምክንያት ሁላችንም ከሞትን በኋላ እንደምንነሳ መታመንን ይጨምራል። ይህ እምነት በምናጣ ጊዜ ሊደግፈንና ሊያጽናናን ይችላል። በትንሣኤ ቃል የሞት ሀዘን ሊወገድ ይችላል።

በኢየሱስ ክርስቶስ ማመን መከራችንን እና ድካማችንን በራሱ ላይ እንደወሰደ መተማመንን ያካትታል (ኢሳይያስ 53፡3–5 ተመልከቱ)። በህይወት ፈተናዎች ውስጥ እንዴት በምሕረት እንደሚረዳን ካለው ልምድ ያውቃል (አልማ 7፡11–12ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 122፡8 ተመልከቱ)። እምነትን ስንለማመድ፣ እርሱ በመከራ ውስጥ ወደፊት እንድንቀጥል ይረዳናል።

በእርሱ ላይ ባለን እምነት፣ ኢየሱስ በስጋም ይሁን በመንፈስ ሊፈውሰን ይችላል። የእርሱን “ባሰባችሁበት ነገር ሁሉ ወደ እኔ ተመልከቱ፣ አትጠራጠሩ አትፍሩ” (ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 6፡36) የሚለውን ግብዣ ስናስታውስ እርሱ ሊረዳን ሁል ጊዜ ዝግጁ ነው።

የተግባር እና የኃይል መርህ

በኢየሱስ ክርስቶስ ማመን ወደ ተግባር ይመራል። ትእዛዛትን በማክበር እና በየቀኑ መልካም በማድረግ እምነታችንን እንገልፃለን። ለኃጢአታችን ንስሐ እንገባለን። ለእርሱ ታማኝ ነን። የበለጠ እርሱን ለመምሰል እንጥራለን።

እምነትን ስንለማመድ የኢየሱስን ኃይል በዕለት ተዕለት ሕይወታችን ልናይ እንችላለን። ከሁሉ የተሻለ ጥረታችንን ያጎላል። እንድናድግ እና ፈተናዎችን እንድንቋቋም ይረዳናል።

እምነታችንን ማጠናከር

ነቢዩ አልማ እምነትን መገንባት በቀላሉ “ለማመን በመፈለግ” ሊጀመር እንደሚችል አስተምሯል አልማ 32:27)። ከዚያም፣ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ያለን እምነት እንዲያድግ፣ ቃሉን በመማር፣ ትምህርቱን በመተግበር እና ትእዛዙን በማክበር መንከባከብ አለብን። አልማ በትዕግስት፣ እምነታችንን እንዲያጠናክር የእግዚአብሔርን ቃል በልባችን ውስጥ የምንንከባከብ ከሆነ “ሥር ያወጣል፣ ይህም ወደ ዘለአለማዊ ሕይወት የሚያድግ ዛፍ ይሆናል” (አልማ 32፡41ቁጥር 26- 43 ተመልከቱ) በማለት አስተምሯል።

የቅዱሳት መጻህፍት ጥናት

እምነት፣ ሀይል፣ እና ደህንነት

የእምነት አስተምሮት

የእምነት ምሳሌ

ስራዎች እና ታዛዥነት

እምነት እና ንስሀ መግባት

ስለዚህ መርህ የበለጠ ተማሩ

ንስሀ መግባት

ንስሃ ምንድን ነው?

ንስሐ መግባት ሁለተኛው የወንጌል መርህ ነው። በኢየሱስ ክርስቶስ ማመን እና ለእርሱ ያለን ፍቅር ወደ ንስሃ ይመራናል (ሄለማን 14፡13 ተመልከቱ)። ንስሐ ወደ እግዚአብሔር የመመለስ እና ከኃጢአት የመራቅ ሂደት ነው። ንስሃ ስንገባ፣ ተግባራችን፣ ምኞታችን እና ሀሳባችን ከእግዚአብሔር ፈቃድ ጋር ይበልጥ የሚስማማ ይሆናል። የኃጢአት ስርየትን ያስቻለው ኢየሱስ ክርስቶስ እና የኃጢያት ክፍያው መስዋዕት ነው።

ንስሀ መግባት ባህሪን ለመለወጥ ወይም ድክመትን ለማሸነፍ ፍቃደኝነትን ከማሳየት በላይ ነው። ንስሐ በቅንነት በልባችን ውስጥ “ታላቅ ለውጥ” እንድንለማመድ ኃይልን ወደሚሰጠው ወደ ክርስቶስ መመለስ ነው (አልማ 5፡12–14)። ይህን የልብ ለውጥ ስንለማመድ፣ በመንፈስ ዳግም እንወለዳለን (ሞዛያ 27፡24–26 ተመልከቱ)።

በንስሐ አማካኝነት፣ ስለ እግዚአብሔር፣ ስለራሳችን እና ስለ ዓለም አዲስ አመለካከት እናዳብራለን። እንደ ልጆቹ የእግዚአብሔር ፍቅር—አዳኛችን ለእኛ ያለው ፍቅር ዳግም ይሰማናል። እግዚአብሔር በልጁ በኩል ከሰጠን ታላቅ በረከቶች አንዱ የንስሐ እድል ነው።

የንስሐ ሂደት

ንስሐ ስንገባ ኃጢአታችንን እንገነዘባለን፣ እውነተኛም ጸጸት ይሰማናል። ኃጢአታችንን ለእግዚአብሔር ተናዘን ምህረትን እንጠይቃለን። እንዲሁም ንስሃ ስንገባ ለሚረዱን ስልጣን ለተሰጣቸው የቤተክርስትያን መሪዎች በጣም ከባድ ኃጢአቶችን እንናዘዛለን። ለመካስ የምንችለውን እናደርጋለን ይህም ማለት ድርጊታችን ያስከተለውን ችግር ለማስተካከል መሞከር ማለት ነው። እውነተኛ ንስሐ በይበልጥ የሚገለጠው በጊዜ ሂደት በሚደረግ የጽድቅ ሥራ ነው።

ንስሐ በሕይወታችን ውስጥ የዕለት ተዕለት ሂደት ነው። “ሁሉ ኃጢአትን ሠርተዋል የእግዚአብሔርም ክብር ጎድሎአቸዋል” (ሮሜ 3፡23)። “ኃይልን በሚሰጠ[ን] በክርስቶስ ሁሉን ማድረግ [እንደምንችል]” በማስታወስ ያለማቋረጥ ንስሐ መግባት አለብን (ፊልጵስዮስ 4፥13)። “ህዝቤ ንስሃ እንደገባው መጠን በእኔ ላይ ያደረጉትን መተላለፍ ይቅር እላቸዋለሁ” (ሞዛያ 26፡30) በማለት ጌታ አረጋግጦልናል።

የንስሐ በረከት

ንስሐ ደስታን እና ሰላምን የሚያመጣ አዎንታዊ መርህ ነው። ንስሐ “ህዝቡን ወደማዳን ስልጣን እንዲሁም ወደ ነፍሳ[ችን] ደህንነትን“ ያመጣል (ሄለማን 5፡11 ተመልከቱ)።

ንስሃ ስንገባ ጥፋተኝነታችን እና ሀዘናችን በጊዜ ሂደት ይድናል። የመንፈስ ተፅዕኖ በብዛት ይሰማናል። እግዚአብሔርን ለመከተል ያለን ፍላጎት እየጠነከረ ይሄዳል።

ምስል
ፕሬዘደንት ራስል ኤም. ኔልሰን

“በጣም ብዙ ሰዎች ንስሐ መግባትን እንደ ቅጣት—መራቅ እንዳለብን ነገር አድርገው ይቆጥራሉ። … ነገር ግን ይህ ቅጣት ያስከትላል የሚለው ሰይጣን የሚያነሳሳው ስሜት ነው፡፡፡፡ ሊያድነን፣ ይቅር ሊለን፣ ሊያጸዳን፣ ሊያነጻን እና ሊቀድሰን እየፈለገ እና ተስፋ እያደረገ እጆቹን ከፍቶ ወደ ቆመው ወደ ኢየሱስ ክርስቶሰ እንዳንመለከት ሊገድበን ይሞክራል።”(ሳስል ኤም ኔልሰን “We Can Do Better and Be Better፣” ኢንዛይን ወይም ሊያሆና፣ ግንቦት 2019 (እ.አ.አ.) 67)

የቅዱስ መጽሀፍ ጥናት

ንስሀ መግባት

ቤዛነት እና ምህረት

ንስሃ ለሚገቡ ምህረት

ስለዚህ መርህ የበለጠ ተማሩ

ምስል
ወጣት ሴት ልጅ እየተጠመቀች

ጥምቀት፡- ከእግዚአብሔር ጋር የመጀመሪያው ቃል ኪዳናችን

በኢየሱስ ክርስቶስ ማመን እና ንስሀ መግባት ለጥምቀት እና ለማረጋገጫ ሥርዓቶች ያዘጋጁናል። ጥምቀት የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል የመጀመሪያው የማዳን ሥርዓት ነው። ይህንን አስደሳች የተስፋ ሥርዓት ስንቀበል፣ ከእግዚአብሔር ጋር የመጀመሪያውን ቃል ኪዳን እንገባለን።

ሥርዓት በክህነት ስልጣን የሚከናወን የተቀደሰ ተግባር ወይም አከባበር ነው። እንደ ጥምቀት ያሉ አንዳንድ ሥርዓቶች ለደህንነታችን አስፈላጊ ናቸው።

በሥርዓቶች አማካኝነት፣ ከእግዚአብሄር ጋር ቃል ኪዳን እንገባለን። እነዚህ ቃል ኪዳኖች በእኛ እና በእግዚአብሔር መካከል የተቀደሱ ኪዳኖች ናቸው። ከእርሱ ጋር የገባነውን ቃል ስንጠብቅ እንደሚባርከን ቃል ገብቷል። ከእግዚአብሔር ጋር የገባነውን ቃል ኪዳን ለመጠበቅ ጠንካራ ቁርጠኝነት ሊኖረን ይገባል።

እግዚአብሔር ወደ እርሱ እንድንመጣ እና የዘላለም ሕይወት እንዲኖረን የሚረዱ ሥርዓቶችን እና ቃል ኪዳኖችን አዘጋጅቷል። የክህነት ሥርዓቶችን ስንቀበል እና ተዛማጅ ቃል ኪዳኖችን ስንጠብቅ፣ በህይወታችን ውስጥ “የአምላክ አይነት ኃይል” ልንለማመድ እንችላለን (ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 84፡20)።

የጥምቀት ቃል ኪዳን

አዳኙ ወደ መንግሥተ ሰማያት ለመግባት ጥምቀት አስፈላጊ መሆኑን አስተምሮአል (ዮሐንስ 3፡5 ተመልከቱ)። የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን አባላት መሆንም አስፈላጊ ነው። አዳኛችን በመጠመቅ ምሳሌ ሆኗል (ማቴዎስ 3፡13–17 ተመልከቱ)።

ስንጠመቅ እና ቃል ኪዳናችንን ስንጠብቅ፣ እግዚአብሔር ኃጢአታችንን ይቅር ሊለን ቃል ገብቷል (የሐዋርያት ስራ . 22፡163 ኔፊ 12፡1–2 ተመልከቱ)። ይህ ታላቅ በረከት የተቻለው “[በ]ወደደን ከኃጢአታችንም በደሙ [ባ]ጠበን” (ራዕይ 1፡5) በኢየሱስ ክርስቶስ የስርየት መስዋዕትነት ነው ። ይቀድሰን፣ ይመራን እና ያጽናናን ዘንድ እግዚአብሔር በመንፈስ ቅዱስ አጋርነት እንደሚባርከን ቃል ገብቷል።

በእኛ የጥምቀት ቃል ኪዳን ክፍል፣ የኢየሱስ ክርስቶስን ስም በራሳችን ላይ ለመውሰድ ፈቃደኛ መሆናችንን እንመሰክራለን። እንዲሁም እርሱን ሁል ጊዜ ለማስታወስ እና ትእዛዛቱን ለመጠበቅ ቃል እንገባለን። ስንጠመቅ ሌሎችን ለመውደድ እና ለማገልገል “ከሚያዝኑት ጋር ለማዘን፤ መፅናናትን ለሚፈልጉም [ለማፅናናት፣] እናም በሁሉም ጊዜ በሁሉም ነገርና፣ በም[ንኖር]በት ቦታዎች ሁሉ … የእግዚአብሔር ምስክር በመሆን [ለመቆም]” ቃል ገብተናል (ሞዛያ 18፥9)። ኢየሱስ ክርስቶስን እስከ ሕይወታችን ፍጻሜ ድረስ ለማገልገል ቁርጠኝነትን እንገልጻለን (ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 20፡37ሞዛያ 2፡17 ተመልከቱ)።

ከጥምቀት ጋር የተያያዙ ቃል ኪዳኖቻችን ትልቅ ኃላፊነት ናቸው። በተጨማሪም አነሳሽ እና አስደሳች ናቸው። የሰማይ አባት ፍቅሩን በቋሚነት የሚሰጥበትን፣ በእኛ እና በእርሱ መካከል ልዩ ግንኙነት ይፈጥራሉ።

በመጥለቅ መጠመቅ

ለኃጢአታችን ስርየት ውሃ ውስጥ በመጥለቅ መጠመቅ እንደሚያስፈልገን ኢየሱስ አስተምሯል (ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 20፡72–74 ተመልከቱ)። በመጥለቅ መጠመቅ የኢየሱስ ክርስቶስ ሞት፣ መቀበር እና ትንሳኤ ምሳሌ ነው (ሮሜ 6፡3–6 ተመልከቱ)።

በተጨማሪም በመጥለቅ መጠመቅ ለእኛ በግላችን ኃይለኛ ምሳሌ አለው። ያም የአሮጌው ህይወታችን መሞት፣መቀበር እና በመንፈስ ዳግም መወለድን ይወክላል። ስንጠመቅ እንደገና የመወለድ ሂደት እንጀምራለን እንዲሁም የክርስቶስ የመንፈስ ወንዶች እና ሴቶች ልጆች እንሆናለን (ሞዛያ 5፥7–8ሮሜ 8፥14–17 ተመልከቱ)።

ልጆች

ልጆች የተጠያቂነት ዕድሜ፣ ስምንት አመት እስኪሞላቸው ድረስ አይጠመቁም(ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 68፡27 ተመልከቱ)። ከዚያ እድሜ በፊት የሚሞቱ ልጆች በኢየሱስ ክርስቶስ የኃጢያት ክፍያ ይድናሉ (ሞሮኒ 8፡4–24ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 137፡10 ተመልከቱ)። ልጆች ከመጠመቃቸው በፊት፣ በሕይወታቸው አስፈላጊ ለሆነው፣ ከእግዚአብሔር ጋር ቃል ኪዳን ለሚገቡበት እርምጃ ዝግጁ እንዲሆኑ ወንጌልን መማር አለባቸው።

ቅዱስ ቁርባን

የሰማይ አባታችን ከእርሱ ጋር ለገባናቸው ቃል ኪዳኖች ታማኝ እንድንሆን ይፈልጋል። ይህንን ለማድረግ እንዲረዳን፣ ቅዱስ ቁርባንን ለመካፈል በየጊዜው እንድንገናኝ አዞናል። ቅዱስ ቁርባን ኢየሱስ ከኃጢያት ክፍያው በፊት ለሐዋርያቱ ያስተዋወቀው የክህነት ሥርዓት ነው።

በየሳምንቱ ቅዱስ ቁርባንን መካፈል የቅዱስ ቁርባን ስብሰባ ዋና ዓላማ ነው። ዳቦ እና ውኃ ተባርኮ ለጉባኤው ይተላለፋል። ዳቦው አዳኙ ስለኛ የሰዋውን ስጋውን ይወክላል። ውሃው ደግሞ ስለ እኛ ያፈሰሰውን ደሙን።

የአዳኙን መስዋዕትነት ለማስታወስ እና ከእግዚአብሔር ጋር የገባነውን ቃል ኪዳን ለማደስ ይህን እንደ ምሳሌ እንካፈላለን። መንፈስ ከእኛ ጋር እንደሚሆን የገባውን ቃል ዳግም እንቀበላለን።

የቅዱስ መጽሀፍ ጥናት

የክርስቶስ ምሳሌ

የጥምቀት ቃል ኪዳን

ለጥምቀት ብቁነት መለኪያ

ቃል የተገባላቸው የጥምቀት በረከቶች

የስልጣን አስፈላጊነት

ኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ቁርባንን አቋቋመ

የቅዱስ ቁርባን ጸሎቶች

ቅዱስ ቁርባንን መቀበል

ስለዚህ መርህ የበለጠ ተማሩ

ምስል
ክርስቶስ በአንዲት ሴት ላይ እጁን ጭኖ

የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ

የመንፈስ ቅዱስ ስጦታን መቀበል

ጥምቀት ሁለት ክፍሎች አሉት። ኢየሱስ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ለመግባት “ከውኃ ከመንፈስ [መወለድ]” እንደሚያስፈልገን አስተምሯል (ዮሐንስ 3፡5፤ አጽንዖት ተጨምሯል)። ጆሴፍ ስሚዝ “በውኃ ጥምቀት ግማሽ ጥምቀት ብቻ ነው፣ ያለ ሌላኛው ግማሽ ማለትም ያለ መንፈስ ቅዱስ ጥምቀት ምንም አይጠቅምም” (ትምህርቶች ጆሴፍ ስሚዝ፣[2007 (እ.አ.አ)] 95) በማለት አስተምሯል።

ሙሉ እንዲሆን የመንፈስ ጥምቀት የውሀ ጥምቀትን መከተል አለበት። ሁለቱንም ጥምቀቶች ስንቀበል ከኃጢአታችን ነጽተን በመንፈስ ዳግም እንወለዳለን። ከዚያም አዲስ መንፈሳዊ ህይወትን እንደ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቶች እንጀምራለን።

የመንፈስን ጥምቀት የምንቀበለው ማረጋገጫ በሚባል ሥርዓት ነው። ይህ ሥርዓት የሚፈጸመው አንድ ወይም ብዙ የክህነት ተሸካሚዎች እጃቸውን በጭንቅላታችን ላይ ሲጭኑ ነው። በመጀመሪያ የቤተክርስቲያኑ አባል መሆናችንን ያረጋግጣሉ፣ ከዚያ የመንፈስ ቅዱስን ስጦታ ይሰጡናል። ይህ በአዲስ ኪዳን እና በመፅሐፈ ሞርሞን ውስጥ የተጠቀሰው ተመሳሳይ ስርዓት ነው (የሐዋርያት ሥራ 8፡14–173 ኔፊ 18፡36–37 ተመልከቱ)።

መንፈስ ቅዱስ የአምላክ ሶስተኛው አባል ነው። ከሰማይ አባት እና ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር በአንድነት ይሰራል። የመንፈስ ቅዱስን ስጦታ ስንቀበልና ታማኝ ስንሆን በህይወታችን ሙሉ የእርሱን አጋርነት ማግኘት እንችላለን።

መንፈስ ቅዱስ እንዴት ይባርከናል

የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ከሰማይ አባታችን ታላቅ ስጦታዎች መካከል አንዱ ነው። መንፈስ ቅዱስ ያነጻናል፣ይቀድሰናል፣ የበለጠ ቅዱሳን እና ፍጹማን፣ የበለጠ እንደ እግዚአብሔር እንድንሆን ያደርገናል (3 ኔፊ 27፡20 ተመልከቱ)። የእግዚአብሔርን ትእዛዛት ለመከተል ስንፈልግ በመንፈሳዊ እንድንለወጥ እና እንድናድግ ይረዳናል።

መንፈስ ቅዱስ እውነትን እንድንማር እና እንድናውቅ ያግዘናል (ሞሮኒ 10:5ን ተመልከቱ)። በተጨማሪም እውነትን ለልባችን እና ለአዕምሮአችን ያረጋግጣል። መንፈስ ቅዱስ እውነትን እንድናስተምርም ይረዳናል (ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 42፡14 ተመልከቱ)። በመንፈስ ቅዱስ ኃይል እውነትን ስንማር እና ስናስተምር፣ ወደ ልባችን ያደርሰዋል (2 ኔፊ 33፡1 ተመልከቱ)።

በትህትና ከመንፈስ ቅዱስ ምሪትን ስንፈልግ እርሱ ይመራናል (2 ኔፊ 32፡5 ተመልከቱ)። ይህ ሌሎችን እንዴት ማገልገል እንዳለብን መነሳሳትንም ይጨምራል።

መንፈስ ቅዱስ ድካምን ለማሸነፍ የሚረዳንን መንፈሳዊ ጥንካሬ ይሰጣል። ፈተናን እንድንቋቋም ይረዳናል። እርሱ ስለ መንፈሳዊ እና ስጋዊ አደጋ ሊያስጠነቅቀን ይችላል።

መንፈስ ቅዱስ በህይወት ፈተናዎች ውስጥ ይረዳናል። በፈተና ወይም በሀዘን ጊዜ በተስፋ በመሙላት ያጽናናል (ሞሮኒ 8፡26 ተመልከት)። በመንፈስ ቅዱስ በኩል፣ እግዚአብሔር ለእኛ ያለው ፍቅር ሊሰማን ይችላል።

የቅዱስ መጽሀፍ ጥናት

የመንፈስ ቅዱስ ተፈጥሮ

የመንፈስ ቅዱስ በረከቶች እና ተፅዕኖ

የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ አስፈላጊነት

ስለዚህ መርህ የበለጠ ተማሩ

ምስል
ኢየሱስ ልጆችን ተሸክምሞ

እስከመጨረሻ መፅናት

ስንጠመቅ እና ማረጋገጭ ስንቀበል ከእግዚአብሔር ጋር ቃል ኪዳን እንገባለን። ከሌሎች ነገሮች በተጨማሪ፣ ትእዛዛቱን ለመጠበቅ እና በቀሪው ህይወታችን እርሱን ለማገልገል ቃል እንገባለን (ሞዛያ 18፡8–10፣ 13ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 20፡37 ተመልከቱ)።

በጥምቀት እና በማረጋገጫ ወደ ወንጌል መንገድ ከገባን በኋላ፣ በዚያ መንገድ ላይ ለመቆየት የተቻለንን ሁሉ ጥረት እናደርጋለን። ትንሽም ቢሆን ከመንገድ ስንወጣ፣ ንስሃ ለመግባት በክርስቶስ ማመንን እንለማመዳለን። የንስሐ በረከቶች ወደ ወንጌል መንገድ እንድንመለስ እና ከእግዚአብሔር ጋር የገባነውን የቃል ኪዳኖች በረከቶች እንድናቆይ ያስችለናል። ከልባችን ንስሐ ስንገባ እግዚአብሔር ሁል ጊዜ ይቅር ሊለን እና ሊቀበለን ፈቃደኛ ነው።

እስከ መጨረሻው መጽናት ማለት እስከ ሕይወታችን ፍጻሜ ድረስ—በጥሩም በአስቸጋሪ፣ በብልጽግናም በችግር ጊዜ ለእግዚአብሔር ታማኝ መሆን ማለት ነው። ክርስቶስ እንዲቀርጸን እና እሱን እንድንመስል በትህትና እንፈቅዳለን። በህይወታችን ምንም ቢከሰት በእምነት እና በተስፋ ወደ ክርስቶስ እንመለከታለን።

እስከ መጨረሻው መጽናት ማለት እስክንሞት ድረስ እንዲሁ መጠበቅ ማለት አይደለም። ይልቁንም ሕይወታችንን፣ ሀሳባችንን እና ተግባራችንን በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ማተኮር ማለት ነው። በየእለቱ በክርስቶስ እምነትን መለማመድ መቀጠል ነው። ቃል ኪዳናችንን መጠበቅ፣ ንስሐ መግባት፣ የመንፈስ ቅዱስን አጋርነት መፈለግም እንቀጥላለን።

እስከ ፍጻሜው ድረስ መጽናት “ፍጹም የሆነ የተስፋ ብርሃን፣ እናም የእግዚአብሔርና የሰዎች ሁሉ ፍቅር እየኖራችሁ በክርስቶስ ባላችሁ ፅኑነት መቀጠል[ን]” ያካትታል። የሰማይ አባታችን እስከ መጨረሻው ከጸናን “የዘላለም ሕይወት” እንደሚኖረን ቃል ገብቷል።(2 ኔፊ 31፥20)።

የቅዱሳት መጻህፍት ጥናት

እስከመጨረሻ መፅናት

ለሚጸኑት የሚሰጡ በረከቶች

ስለዚህ መርህ የበለጠ ተማሩ

  • የወንጌል ርዕሶች “መከራ

  • የቅዱሳት መጻህፍት መመሪያ፣ “መጽናት፣ “መከራ

ምስል
ቤተሰብ እየሳቀ

የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል የእግዚአብሔርን ልጆች ሁሉ ይባርካል

የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል ለሁሉም የእግዚአብሔር ልጆች ነው። አስተዳደጋችን ወይም ሁኔታችን ምንም ይሁን ምን ቅዱሳት መጻህፍት “ሁሉም ለእግዚአብሔር አንድ” እንደሆኑ ያስተምራሉ። “ከቸርነቱ ይካፈሉ ዘንድ ሁሉም ወደ እርሱ እንዲመጡ ይጋብዛል እናም ወደ እርሱ የሚመጡ ማንንም … አይክድም” (2 ኔፊ 26፥33)።

ወንጌል በምድራዊ ህይወታችን በሙሉ እንዲሁም በዘለአለም ይባርከናል። በኢየሱስ ክርስቶስ ትምህርቶች ስንኖር—በግልም ሆነ በቤተሰብ ደረጃ— ደስተኛ የመሆን ዕድላችን ከፍተኛ ነው (ሞዛያ 2፡41፤ “ቤተሰብ፡ ለአለም የተላለፈ አዋጅ፣” ChurchofJesusChrist.org)። ወንጌልን መኖር ደስታችንን ጥልቅ ያደርጋል፣ ድርጊቶቻችንን ያነሳሳል እንዲሁም ግንኙነታችንን ያበለጽጋል።

የኢየሱስ ክርስቶስን ወንጌል መኖር ስጋዊም ሆነ መንፈሳዊ ጉዳት ሊያደርሱ የሚችሉ ምርጫዎችን እንዳንመርጥ ይጠብቀናል። በፈተና እና በሀዘን ጊዜ ጥንካሬ እና መጽናናትን እንድናገኝ ይረዳናል። ደስታ ወደተሞላ የዘላለም ሕይወት መንገዱን ያዘጋጃል።

ዳግም የተመለሰው ወንጌል አንዱ ታላቅ መልእክት ሁላችንም የእግዚአብሔር ቤተሰብ አካል መሆናችን ነው። እኛ የተወደድን ወንድና ሴት ልጆቹ ነን። በምድር ላይ ያለን የቤተሰብ ሁኔታ ምንም ቢሆን እያንዳንዳችን የእግዚአብሔር ቤተሰብ አባላት ነን።

ሌላው የመልእክታችን ታላቅ ክፍል ቤተሰቦች ለዘለአለም አንድ መሆን መቻላቸው ነው። ቤተሰብ በእግዚአብሔር የተሰጠ ነው። የሰማይ አባት የደስታ እቅድ የቤተሰብ ግንኙነቶች ከመቃብር በላይ እንዲቀጥሉ ያስችላል። የተቀደሱ የቤተመቅደስ ሥርዓቶች እና ቃል ኪዳኖች ቤተሰቦች ለዘለአለም አብረው እንዲሆኑ ያስችላቸዋል።

በወንጌል ብርሃን፣ ቤተሰቦች አለመግባባቶችን፣ ክርክሮችን እና ተግዳሮቶችን መፍታት ይችላሉ። ባለመስማማት የተጎዱ ቤተሰቦች በንስሐ፣ በይቅርታ እና በኢየሱስ ክርስቶስ የኃጢያት ክፍያ ኃይል በማመን ይፈወሳሉ።

የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል ጠንካራ የቤተሰብ ግንኙነቶችን እንድንገነባ ይረዳናል። ቤት የወንጌልን መርሆች ለማስተማር እና ለመማር ምርጡ ቦታ ነው። በወንጌል መርሆዎች ላይ የተመሰረተ ቤት የመሸሸጊያና የደህንነት ቦታ ይሆናል። የጌታ መንፈስ የሚኖርበት ቦታ ይሆናል።

የቅዱስ መጽሀፍ ጥናት

ስለዚህ መርህ የበለጠ ተማሩ

ከአጭር እስከ መካከለኛ የትምህርት መዘርዝር

የሚከተለው ንድፍ አጭር ጊዜ ካላችሁ ለአንድ ሰው ልታስተምሩ የምትችሉት ነገር ምሳሌ ነው። ይህንን ንድፍ ስትጠቀሙ ለማስተማር አንድ ወይም ተጨማሪ መርሆችን ምረጡ። ለእያንዳንዱ መርህ የትምህርት መሰረት ቀደም ብሎ በትምህርቱ ውስጥ ቀርቧል።

ስታስተምሩ ጥያቄዎችን ጠይቁ እንዲሁም አዳምጡ። ሰዎች እንዴት ወደ እግዚአብሄር መቅረብ እንደሚችሉ እንዲማሩ የሚያግዙ ግብዣዎችን አቅርቡ። አንድ አስፈላጊ ግብዣ ግለሰቡ እንደገና ከእናንተ ጋር እንዲገናኝ መጋበዝ ነው። የትምህርቱ ቆይታ የሚወሰነው በmtጠይቋቸው ጥያቄዎች እና በአደማመጣችሁ ላይ ነው።

ምስል
ሚስዮናውያን ሴቶችን ሲያስተምሩ

ከ3–10 በሚሆኑ ደቂቃዎች ውስጥ ሰዎችን ልታስተምሯቸው የምትችሏቸው ነገሮች

  • እግዚአብሔር ስለወደደን ከኃጢአትና ከሞት እንዲቤዠን የሚወደውን ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን ወደ ምድር ልኮልናል።

  • በኢየሱስ ክርስቶስ ማመን የተግባር እና የሃይል መርህ ነው። እምነት የአዳኙን የሚያበረታ ሀይል በህይወታችን እንድንለማመድ ይረዳናል።

  • በኢየሱስ ክርስቶስ ማመን ወደ ንስሐ ይመራናል። ንስሐ ወደ እግዚአብሔር የመመለስ እና ከኃጢአት የመራቅ ሂደት ነው። ንስሃ ስንገባ፣ ተግባራችን፣ ምኞታችን እና ሀሳባችን ከእግዚአብሔር ፈቃድ ጋር ይበልጥ የሚስማማ ይሆናል።

  • ንስሃ ስንገባ እግዚአብሔር ይቅር ይለናል። ኢየሱስ ክርስቶስ ለኃጢአታችን ዋጋ ስለከፈለ ስርየት እንዲቻል አድርጓል።

  • ጥምቀት ሁለት ክፍሎች አሉት፡ በውሃ መጠመቅ እና በመንፈስ መጠመቅ ስንጠመቅ እና ማረጋገጫ ስንቀበል ከኃጢአታችን በመንጻት ህይወትን እንደ አዲስ እንጀምራለን።

  • በውኃ ከተጠመቅን በኋላ፣ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታን በማረጋገጫ ሥርዓት እንቀበላለን።

  • እስከ ህይወታችን መጨረሻ ድረስ የወንጌልን መንገድ በታማኝነት ከተከተልን፣ እግዚአብሔር የዘላለም ህይወት እንደሚኖረን ቃል ይገባል።