ቅዱሳት መጻህፍት
ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች ፴፮


ክፍል ፴፮

ታህሳሥ ፱፣ ፲፰፻፴ (እ.አ.አ.) በፈየት፣ ኒው ዮርክ አቅራቢያ በነቢዩ ጆሴፍ ስሚዝ አማካይነት ለኤድዋርድ ፓርትሪጅ የተሰጠ ራዕይ (የክፍል ፴፭ ርዕስን ተመልከቱ)። የጆሴፍ ስሚዝ ታሪክ ስለኤድዋርድ ፓርትሪጅ እንደገለጸው “የቅድስና ምሳሌ፣ እና ከጌታ ታላላቅ ሰዎች አንዱ ነው።”

፩–፫፣ በስድኒ ሪግደን አማካይነት ጌታ እጁን በኤድዋርድ ፓርትሪጅ ላይ ጭኗል፤ ፬–፰፣ ወንጌልንና ክህነትን የሚቀበል ወንድ ሁሉ እንዲሄድ እና እንዲሰብክ ይጠራል።

የእስራኤል ኃያል የሆነው፣ ጌታ አምላክ እንዲህ ይላል፥ እነሆ፣ አገልጋዬ ኤድዋርድ እንዲህ እልሀለሁ፣ አንተ የተባረክህ ነህ፣ እናም ኃጢአትህም ተሰርዮልሀል፣ እንዲሁም እንደመለከት ድምጽ ወንጌሌን እንድትሰብክ ተጠርተሀል፤

እናም በአገልጋዬ በስድኒ ሪግደን እጄን በአንተ ላይ እጭናለሁ፣ እናም የመንግስትን የሰላም ነገሮች የሚያስተምርህን አጽናኝ የሆነውን መንፈሴን፣ መንፈስ ቅዱስን ትቀበላለህ።

እናም ሆሳዕና፣ ልዑል እግዚአብሔር የተባረከ ይሁን በማለት፣ ከፍ ባለ ድምጽም ታውጀዋለህ።

እናም አሁን ሰዎችን ሁሉ በተመለከተ፣ ይህን ጥሪና ትእዛዝ እሰጥሀለሁ—

በአገልጋዮቼ በስድኒ ሪግደን እና በጆሴፍ ስሚዝ፣ ዳግማዊ ፊት ይህንን ጥሪና ትእዛዝ ተቀብለው የሚመጡት ሁሉ፣ ይሾማሉ እናም በአህዛብ መካከል ዘለአለማዊ ወንጌሌን እንዲሰብኩ ይላካሉ—

ንስሀንም በመጮህ፣ እንዲህ ይበሉ፥ ከዚህ ጠማማ ትውልድ ራሳችሁን አድኑ፣ እናም ከእሳት ውስጥም ተነጥቃችሁ ውጡ፣ በረከሰ ስጋ የተበከለውንም ልብስ ተጸየፉ።

እኔ እንደተናገርኩት በአንድ ልብ ይህን የሚቀበል ሁሉ እንዲሾምና እንዲላክ ይህ ትእዛዝ ለቤተክርስቲያኔ ሽማግሌዎች ይሰጣል።

እኔ የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ነኝ፤ ስለዚህ ወገባችሁን እሰሩ እናም በድንገትም ወደ ቤተመቅደሴ እመጣለሁ። እንዲህም ይሁን። አሜን።