ቅዱሳት መጻህፍት
ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች ፶፫


ክፍል ፶፫

በሰኔ ፰፣ ፲፰፻፴፩ (እ.አ.አ.)፣ በከርትላንድ ኦሀዮ ውስጥ፣ በነቢዩ ጆሴፍ ስሚዝ በኩል ለአልጀርኖን ስድኒ ጊልበርት የተሰጠ ራዕይ። በስድኒ ጊልበርት ጥያቄ ምክንያት፣ ነቢዩ ስለወንድም ጊልበርት የቤተክርስቲያን ስራና ሀላፊነት ጌታን ጠየቀ።

፩–፫፣ የስድኒ ጊልበርት የቤተክርስቲያን ጥሪ እና ምርጫ እንደ ሽማግሌ እንዲሾም ነው፤ ፬–፯፣ እርሱም እንደ ኤጲስ ቆጶስ ወኪል እንዲያገለግልም ነው።

እነሆ፣ አገልጋዬ ስድኒ ጊልበርት፣ እንዲህ እልሀለሁ፣ ጸሎቶችህን ሰምቼአለሁ፤ እኔ ጌታ በኋለኛው ቀናት ባነሳኋት በዚህች ቤተክርስቲያን ውስጥ ያለህን ጥሪና ምርጫ እውቀት ይሰጥህ ዘንድ እኔ፣ ጌታ አምላክህን፣ ጠይቀሀል።

እነሆ፣ ለአለም ኃጢአት የተሰቀልኩ እኔ ጌታ አለምን እንድትተው ትእዛዝን እሰጥሀለሁ።

በቃሌ በኩል፣ እምነትን እና ንስሀ መግባትን እና ለኃጢአቶች ስርየት እና እጆችን በመጫን መንፈስ ቅዱስን መቀበልን ለመስበክ፣ የሽማግሌነት ሹመቴን በራስህ ላይ ተቀበል፤

እናም ከዚህ በኋላ በሚሰጠው ትእዛዝ፣ ኤጲስ ቆጶሱ በሚመድብበት ስፍራም ለዚህች ቤተክርስቲያን ወኪል እንድትሆንም ነው።

እና ደግሞም፣ በእውነት እልሀለሁ፣ ከአገልጋዮቼ ጆሴፍ ስሚዝ፣ ዳግማዊ፣ እና ከስድኒ ሪግደን ጋር ተጓዝ።

እነሆ፣ እነዚህም የምትቀበላቸው የመጀመሪያ ስነ ስርዓቶች ናቸው፤ እና በወይን ስፍራዬ ውስጥ ባገለገልክ መጠን፣ ቅሪቶቹም በሚመጣው ጊዜ ይገለጣሉ።

እና ደግሞም፣ እስከ ፍጻሜው የሚጸና እርሱ ብቻ እንደሚድን እንድትማርም እፈልጋለሁ። እንዲህም ይሁን። አሜን።