ቅዱሳት መጻህፍት
ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች ፹፫


ክፍል ፹፫

በሚያዝያ ፴፣ ፲፰፻፴፪ (እ.አ.አ.) በእንድፐንደንስ ሚዙሪ ውስጥ በነቢዩ ጆሴፍ ስሚዝ በኩል የተሰጠ ራዕይ። ይህን ራዕይ የተቀበለው ነቢዩ ከወንድሞች ጋር ለመምከር እንደተቀመጠ ነው።

፩–፬፣ ሴቶች እና ልጆች በባሎቻቸው እና በአባቶቻቸው የመደገፍ መብት አላቸው፤ ፭–፮፣ ባልቴቶች እና የሙት ልጆች በቤተክርስቲያኗ ላይ የመደገፍ መብት አላቸው።

በእውነትም፣ ስለሴቶች እና ስለልጆች፣ ባሎቻቸውን እና አባቶቻቸውን ስላጡት የቤተክርስቲያኗ አባላት፣ ቤተክርስቲያኗ ካላት ህግጋት በተጨማሪ ጌታ እንዲህ ይላል፥

ሴቶች፣ ባሎቻቸው እስከሚወሰዱ ድረስ፣ በባሎቻቸው የመደገፍ መብት አላቸው፤ እናም የሚተላለፉ ሆነው እስካልተገኙ ድረስ በቤተክርስቲያኗ ውስጥ ህብረት ይኖራቸዋል።

እናም ታማኝ ካልሆኑም በቤተክርስቲያኗ ውስጥ ህብረት አይኖራቸውም፣ ነገር ግን በምድር ህግ መሰረት በውርሳቸው ላይ ለመቆየት ይችላሉ።

ለእድሜ እስኪደርሱ ድረስ ሁሉም ልጆች በወላጆቻቸው ላይ የመደገፍ መብት አላቸው።

እናም ከዚያም በኋላ፣ ወላጆቻቸው ለውርስ የሚሰጧቸው ከሌላቸው፣ በቤተክርስቲያኗ ላይ፣ ወይም በሌላ አባባል በጌታ ጎተራ ላይ መብት አላቸው።

እናም ጎተራውም በቤተክርስቲያኗ ቅድስና ይጠበቃል፤ እናም ባልቴቶች እና የሙት ልጆችም፣ እናም ድሆች፣ ይረዳሉ። አሜን።